አሳሳቢ ደረጃ የደረሰዉ   በሽታ

0
20

በዓለማችን በ2023 እ.አ.አ ሥር ለሰደደ የኩላሊት በሽታ ከተዳረጉ 800 ሚሊዮን ሰዎች አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዬን የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::

በአሜሪካ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ  ከ “ኤንዋይዩ ላንጐን ሄልዝ” እና ከ “ሄልዝ ሜትሪክስ ኤንድ ኢቫሉዌሽን” ከተሰኙ ተቋማት ከተውጣጡ ምሁራን ጋር ባደረጉት ምርምር የኩላሊት በሽታ  ኩላሊት ከደም ውስጥ ቆሻሻ እና አላስፈላጊ ፈሳሽ የማጽዳት ዓቅም ሲያጣ የሚከሰት መሆኑን ነው ያሰመሩበት::

በ2023 እ.አ.አ በ133 ሀገራት ከተሰበሰበ መረጃ እና ከሁለት ሺህ በላይ ከቀረቡ የምርምር ጽሑፎች ግምገማም የኩላሊት ህመም ከልብ ህመም ጋር እንደሚገናኝ ተመላክቷል:: በተጨማሪም ከዓለም ለሞት መንስኤ ከሆኑ በሽታዎች 12 በመቶውን የኩላሊት በሽታ መያዙን ነው መገንዘብ የቻሉት::

ስር የሰደደ የኩላሊት በሽታ ተባብሶ ለ “ዲያለሲስ” ማፅዳት ወይም ንቅለ ተከላ ለማድረግ በታዳጊ ሀገራት  የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ፣ ተደራሽነቱም አስቸጋሪ መሆኑን – ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል::

ባለፉት አምስት ዓመታት በተደረጉ ጥረቶች በሽታው ተባብሶ የልብ ድካም፣  “ስትሮክ” የደም መፍሰስ እንዳያስከትል መከላከል የሚያስችሉ አዳዲስ መድሃኒቶች ቢመረቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ጊዜ ወሳጅ መሆኑን ነው ያሰመሩበት- ተመራማሪዎቹ::

የጥናት እና ምርምሩ ተባባሪ መሪ ዶክተር ሞርጋን ግራምስ በሽታው የከፋ ደረጃ ሳይደርስ በየጊዜው ቀድሞ መመርመር ከማንኛውም የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ነው አፅንኦት ሰጥተው ያስታወቁት::

በመጨረሻም በየጊዜው ምርመራ በማድረግ የኩላሊት በሽታ ስር ሳይሰድ፣  ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ለመወሰን እንደሚያስችል ጠቅሰው በሽታው በመጀመሪያ ደረጃ ላይ መሆኑ ከተረጋገጠም ለባለሙያዎች ጣልቃ ለመግባት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው ያደማደሙት – ተመራማሪዎቹ::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የሕዳር 22 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here