አስሩ ዝንፈቶች

0
9

ሳይኮሎጂ ቱ ዴይ ገጽ “የሰብእና መዛባት (Personality Disorder) ማለት አንድ ግለሰብ የሚያስበው፣ የሚሰማው እና ባህሪውን የሚገልጽበት መንገድ ከማህበረሰቡ የባህል ወግና ልማድ በእጅጉ ያፈነገጠ ሲሆን ነው” ይላል። ይህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሲሆን፣ የግለሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ፣ ሥራ እና ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በእጅጉ ይጎዳል። አስር የሰብእና መዛባቶች እንዳሉም ጽፏል። እነዚህ መዛባቶች በሶስት ምድቦች  ይከፈላሉ።

ምድብ አንድ እንግዳ ወይም ያልተለመደ ባህሪ ነው። ይህ ምድብ ሦስት የሰብእና መዛባቶችን የያዘ ነው። ቀጥሎ ከቁጥር አንድ እስከ ሦስት ቀርበዋል። በዚህ ምድብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ለሌሎች “እንግዳ” ወይም “ከሰው የተለዩ” ሆነው ይታያሉ። በዚህ ምድብ ውስጥ የመጀመርያው የበዛ ጥርጣሬ ነው።

  1. ፓራኖይድ የሰብእና መዛባት (ከልክ ያለፈ ጥርጣሬ)

ዋና መገለጫው በሌሎች ሰዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ እምነት ማጣትና መጠራጠር ነው። ይህ መዛባት ምልክቶችም አሉት። ሰዎች ሊጎዱኝ ነው ብሎ ማሰብ፣ የሰዎችን ቅንነት መጠራጠር እና በቀላሉ ቂም መያዝ ናቸው። ሰዎች የትዳር አጋራቸው እንደሚከዳቸው ያለ ምክንያት ይጠራጠራሉ።

  1. ስኪዞይድ የሰብእና መዛባት

ዋና መገለጫው ከማህበራዊ ግንኙነት መነጠል እና ስሜትን አለማሳየት ነው። ብቸኝነትን መምረጥ፣ ለወሲባዊ ግንኙነት ፍላጎት ማጣት፣ ለምስጋና ወይም ለሂስ ስሜት አለማሳየት፣ እና ደንዝዞ  መታየት ምልክቶቹ  ናቸው።

  1. ስኪዞታይፓል የሰብእና መዛባት

በጣም እንግዳ የሆነ አስተሳሰብ፣ አነጋገር እና አለባበስ ማሳየት ዋና መግለጫዎች ናቸው። እንግዳ እምነቶች (ለምሳሌ “ሰዎች የሚያስቡትን ማንበብ እችላለሁ” ብሎ ማሰብ)፣ ያልተለመደ የንግግር ዘይቤ፣ እና ከቅርብ ዘመድ ውጪ ጓደኛ መያዝ አለመቻል ምልክቶቹ ናቸው።

ምድብ ሁለት  ከስሜታዊነት እና ድራማዊ ባህሪ ጋር የሚገናኙ ናቸው። ከቁጥር አራት እስከ ሰባት ያሉትን ያካትታሉ። እነዚህ ግለሰቦች ስሜታቸውን መቆጣጠር ይቸገራሉ። እንዲሁም ባህሪያቸው ተለዋዋጭ ነው።

  1. ጸረ-ማህበረሰብ የሰብእና መዛባት

ለሌሎች መብት ግድ አለመስጠት እና ህግን መጣስ የዚህ ሰብእና መዛባት ዋና መገለጫ ነው። መዋሸት፣ ማታለል፣ ጠበኛ መሆን፣ ለሰራው ስህተት ፀፀት ወይም ርህራሄ አለመሰማት ምልክቶቹ ናቸው። ይህ ችግር ብዙውን ጊዜ ከልጅነት ጀምሮ ይታያል።

  1. ቦርደርላይን የሰብእና መዛባት

ዋና መገለጫው በራስ መተማመን፣ በስሜት እና በግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ መዋዠቅ ናቸው። ምልክቶቹም  ዛሬ የወደዱትን ሰው ነገ መጥላት፣ ብቻዬን እቀራለሁ ብሎ ከመጠን በላይ መፍራት፣ ድንገተኛ ቁጣ እና ራስን የመጉዳት ዝንባሌ ናቸው።

  1. ሂስትሪዮኒክ የሰብእና መዛባት

ዋና መገለጫው ከመጠን በላይ ትኩረት የመሻት እና ስሜታዊ የመሆን ባህሪ ነው። ምልክቶቹ የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ሲባል አሳሳች አለባበስ መልበስ ወይም ድራማዊ መሆን፣ በቀላሉ በሌሎች ተጽዕኖ ስር መውደቅ፣ እና ግንኙነቶችን ከሆኑት በላይ አጋንኖ ማሰብ (ለምሳሌ ትውውቅን እንደ ጥልቅ ጓደኝነት ማየት) ሊሆን ይችላል።

  1. ናርሲሲስቲክ የሰብእና መዛባት

ይህ የሰብእና መዛባት ዋና መገለጫው ራስን ከልክ በላይ ማጋነን እና የሌሎችን አድናቆት መፈለግ ነው። ምልክቶቹም እኔ ልዩ ነኝ ብሎ ማሰብ፣ የሌሎችን ስሜት አለመረዳት (ርህራሄ አልባነት)፣ ሰዎች እንዲያገለግሏቸው መጠበቅ፣ እና በሌሎች ስኬት መቅናት ናቸው።

ምድብ ሶስት  ጭንቀት ወይም ፍርሃት የተሞላበት ባህሪን የሚያሳዩ ናቸው። በዚህ ምድብ ያሉ ሰዎች በብዛት በፍርሃት እና በጭንቀት ይኖራሉ። ቀጥሎ ያሉት ስምንት፣ ዘጠኝ እና አስር በዚህ ውስጥ ይካተታሉ።

  1. አቮይዳንት (ከሰው መሸሽ) የሰብእና መዛባት

ዋና መገለጫው በማህበራዊ ግንኙነት ላይ የበታችነት ስሜት እና “ይተቹኛል” የሚል ፍርሃት ነው። ሰዎች እንደሚወዱን እርግጠኛ ካልሆንን በስተቀር ለመቀራረብ መፍራት፣ አዲስ ግንኙነት ለመፍጠር መጨነቅ፣ እና ራስን እንደማይረባ አድርጎ ማሰብ ምልክቶቹ ተብለው ይጠቀሳሉ።

  1. ዲፔንደንት (ጥገኛ) የሰብእና መዛባት

ዋና መገለጫው ከመጠን በላይ የሌሎችን እንክብካቤ መፈለግ እና መጠበቅ ነው። ያለሌሎች እርዳታ የዕለት ተዕለት ውሳኔዎችን መወሰን አለመቻል፣ ብቻን ለመሆን መፍራት እና አንድ ግንኙነት ሲያበቃ ወዲያውኑ ሌላ ሰው ላይ መጣበቅ ጉልህ ምልክቶቹ ናቸው።

  1. ኦብሴሲቭ ኮምፐልሲቭ የሰብእና መዛባት

ለሥርዓት፣ ህግ እና ለፍጹምነት ከመጠን በላይ መጨነቅ ዋና መገለጫው ተደርጎ ይወሰዳል። ምልክቶችም ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከመጠን በላይ በማተኮር ዋናውን ሥራ መርሳት፣ ሥራን ለሌሎች ማካፈል አለመፈለግ (እነሱ እኔ የምፈልገውን ያህል ጥራት አይሰሩም ብሎ ማሰብ) እና በገንዘብ እና በጊዜ ላይ እጅግ በጣም ንፉግ መሆን ነው።

የሰብእና መዛባት መንስኤዎች

የሳይኮሎጂ ቱዴይ እና የሜዮ ክሊኒክ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ለሰብእና መዛባት ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ አንድ እና ብቸኛ መንስኤ የለም። ይልቁንም የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው። ዋና ዋናዎቹ መንስኤዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

ሀ. የዘር ውርስ ወይም ጂኔቲክስ ሳይንቲስቶች አንዳንድ የሰብእና መዛባቶች በዘር ሊተላለፉ እንደሚችሉ አረጋግጠዋል። ለምሳሌ ወላጆች ወይም የቅርብ ዘመዶች ፀረ-ማህበረሰብ  ወይም የቦርደርላይን መዛባት ካለባቸው ልጆችም ለዚህ የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው። አንዳንድ ጂኖች አንድን ሰው ለጭንቀት ወይም ለጥቃት ተጋላጭ ያደርጉታል፤ ይህም ከሌሎች አካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር ሲደመር ችግሩን ይፈጥራል።

ለ. የልጅነት ጊዜ ጠባሳ እና አስተዳደግ

ይህ በስነ-ልቦና ባለሙያዎች ዘንድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነጥብ ነው። በልጅነት ጊዜ የሚደርስ አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ስሜታዊ ጥቃት  ትልቅ መንስኤ ነው። ያልተረጋጋ የቤተሰብ ሁኔታ፣ ከወላጅ መነጠል፣ ወይም በልጅነት ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ማደግ ለችግሩ መፈጠር ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። (በተለይ ለቦርደርላይን የሰብእና መዛባት ዋነኛ መንስኤ ነው ተብሎ ይታመናል)።

ሐ. የአንጎል አወቃቀር እና ኬሚስትሪ

የነርቭ ሳይንስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የሰብእና መዛባት ያለባቸው ሰዎች የአንጎል አወቃቀር በተወሰነ መልኩ ከሌሎች ሰዎች ሊለይ ይችላል። ስሜትን በሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል (አሜግድላ) እና ውሳኔን በሚመራው ክፍል (ፕሪፎንታል ኮርቴክስ-የፊተኛው ክፍል) ላይ የሚታይ የአሠራር ልዩነት ሰዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዲሳናቸው ያደርጋል።

መፍትሔዎች እና የሕክምና አማራጮች

እንደ አሜሪካን ሳይኮሎጂካል አሶሴሽን ገለጻ የሰብእና መዛባት “ሊታከም የሚችል” ችግር ነው። ሆኖም ህክምናው የረጅም ጊዜ ትዕግስትን ይጠይቃል።

የንግግር ህክምና ዋናው እና ተመራጩ የህክምና ዘዴ ነው። ቀጥሎ ዲያሌክቲካል ቢሄቪየራል ቴራፒ በተለይ ለቦርደርላይን የሰብእና መዛባት እና ራስን የመጉዳት አባዜ ላለባቸው ሰዎች ውጤታማ ነው። ስሜትን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ያስተምራል። ኮግኒቲቭ ቢሄቪየራል ቴራፒ ደግሞ ግለሰቡ ስለ ራሱ እና ስለ ዓለም ያለውን አሉታዊ ወይም የተዛባ አስተሳሰብ  በመለወጥ ባህሪን ለማስተካከል ይረዳል። ሳይኮዳይናሚክ ቴራፒ ከልጅነት ጀምሮ የተጠራቀሙ ንቃተ-ህሊና ውስጥ ያሉ (ድብቁ ህሊና) ጉዳዮችን በመመርመር ፈውስን ለማምጣት ይሞክራል።

የሰብእና መዛባትን በቀጥታ የሚያድን መድሃኒት እስካሁን አልተፈጠረም። ነገር ግን ከችግሩ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ምልክቶች ሐኪሞች መድሃኒት ሊያዙ ይችላሉ።

ምናልባትም እንደ ሀገር ላሉብን ችግሮች እነዚህ የሰብእና መዛባቶች በአንዳንዶቻችን ላይ ኖረው ሳይረብሹን ይቀራሉ?።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የታህሣስ  6  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here