“ሰዎች የወደፊት ህልማቸው የሚወሰነው በልጅነት ዕድሜያቸው በሚያዩት ነገር ነው:: በብዙዎች ልምድ መሰረት ግን ራስን ፈልጎ ለማግኘት ጊዜ ይወስዳል” በማለት የሕይወት ጉዟቸውን የነገሩን ወ/ሮ ብርቱካን ጌትነት ናቸው:: ትውልዳቸው በደቡብ ጎንደር ዞን ርብ ኪዳነምህረት፤ እድገታቸው ደግሞ ወረታ አካባቢ ነው:: ባለታሪካችን እንደሚሉት በልጅነታቸው ከሚሰሙት እና ከሚያዩት ተነስተው ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ዶክተር፣ መምህር …የመሆን ፍላጎት ነበራቸው:: 11ኛ ክፍል ሲደርሱ ግን ወደ ማህበራዊ ትምህርት ዘርፍ ገቡ:: የዩኒቨርሲቲ ምርጫቸውም ሳይኮሎጂ (ሥነ ልቦና) የትምህርት ዘርፍ ሆነ::
“በአካባቢያችን በተለይም በልጅነት ጊዜ ከምናየው ሰው በመነሳት እንጂ የእውነት የውስጣችንን መክሊት ይሄ ነው ብለን አስበን ባናድግም በሂደት ግን ራሳችንን የምናገኝበት አጋጣሚ የሚፈጠርበት ሁኔታ ብዙ ነው”በማለት የራሳቸውን ገጠመኝ ተናግረዋል::
ወ/ሮ ብርቱካን ያጠኑት የትምህርት ዘርፍ ከማንም በፊት የለወጠው የራሳቸውን ባሕሪ እንደ ነበር ያስታውሳሉ:: የሳይኮሎጂ (ሥነ ልቦና) ትምህርት ከሌሎች በፊት ራስን ለመፈተሽ እና ራስ ላይ ለመሥራት ያግዛል:: ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ዐይን አፋር፣ ራስን ለመግለፅ የሚቸገሩ እና ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ዝቅተኛ እንደሆነ እንዲረዱ እድል ሰጥቷቸዋል:: “የመረጥሁት የትምህርት ዘርፍ ጠንካራ ጎኔ ምንድን ነው? ደካማ ጎኔ ምንድን ነው? የሚለውን በዛ እድሜ ክልል ላይ እያለሁ መለየት ስላስቻለኝ በቀጣይ ስመረቅ ሕፃናት እና ሴቶች በተለይም እናቶች ላይ ብሠራ የሚል ሀሳብ እንዲፈጠርልኝ አነሳሳኝ” ይላሉ::
ትምህርታቸውን በ2009 ዓ.ም ያጠናቀቁት ወ/ሮ ብርቱካን፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሙያ ተመድበው ማስተማር ጀመሩ:: ይሁን እንጅ በኮሌጅ ማስተማር ሂደት የተማሩትን ሳይንስ ከመድገም የዘለለ በትውልድ ለውጥ ላይ የሚኖረው የመለወጥ ሂደት (ፋይዳ) ዝቅተኛ መሆኑን በማመን እና ህልማቸውም ስላልሆነ ብዙ ሳይሠሩ ወደ አዲስ አበባ አቀኑ::
በዛው ዓመት በአዲስ አበባ መኖር እንደ ጀመሩ ያገኙት እድልም በአድማስ ኮሌጅ የማስተማር ሥራ ነበር:: የሚፈልጉትን የሙያ ዘርፍ በቀላሉ ማግኘት ያልቻሉት ወ/ሮ ብርቱካን ጊዜ ሳያጠፉ ኮሌጁን ለቀው ሆለን በተሰኘ የሕፃናት አካዳሚ በካውንስሊንግ (ምክክር) ባለሙያ የሥራ ዘርፍ ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ::
ህልማቸውም በሆለን አካዳሚ እንደሚሰምር ተስፋ ጣሉ:: ሰዎችን የመለወጥ እና ጥሩ ማንነትን የመገንባት አጋጣሚ የሚሠራው ገና በሕፃንነት በተለይም ከአንድ እስከ ሰባት ዓመት ባለው እድሜ ክልል በመሆኑ በዛ እድሜ ካሉ ወላጆች እና ልጆች ጋር መሥራቱ ትልቅ የአዕምሮ እርካታ እና ፋይዳ እንዳለው ይገልፃሉ::
ባለሙያዋ እንደሚሉት የተመደቡበት የሥራ ዘርፍ ሕፃናት ጥሩ ስብዕና እንዲያዳብሩ በራሳቸው እንዲተማመኑ ወላጆች ትክክል ነው ብለው የሚያምኑትን ማህበራዊ አስተዳደግ ከሳይንሱ ጋር በማጣጣም ለመሥራት እድል ሰጥቷቸዋል:: በሥራ ቦታቸው የነበረው ነፃነት ከልጆች አልፎ ወላጆችንም አግኝቶ ለማነጋገር እና አብሮ ለመሥራት ዕድል ነበረው::
ወ/ሮ ብርቱካን ከዓመታት በኋላ የሚወዱትን ሙያ ትተው በወሊድ ምክንያት ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር አቀኑ:: ወደ ባሕር ዳር ሲመጡም በሙያቸው ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው:: በተለይም በልጆች ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በኤስ ኦ ኤስ መንደር በመቀጠር ለመሥራት ቢሞክሩም ወቅቱ ኮሮና ቫይረስ የተከሰተበት በመሆኑ ሳይሳካላቸው እንደ ቀረ ያስታውሳሉ::
ወ/ሮ ብርቱካን በባሕር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ በተለይም በዝቅተኛ ንግድ እና ኑሮ ሕይወታቸውን የሚገፉ እናቶች ልጆቻቸው የሚያድጉበት ነባራዊ ሁኔታ በስብዕናቸው ላይ ያለውን ጉዳት ለመታዘብ ዕድል እንደሰጣቸው ይገልፃሉ:: ልጆች መልካም ነገርን ሊመለከቱበት እና ሊነገሩበት በሚገባው እድሜያቸው በመንገድ (ምቹ ባልሆነ) ቦታ ክፉ እና ደግ፣ ስድብ እና ጠብ …እያዩ ሲያድጉ የሚኖረው ተፅኖ ከባድ እንደሆነ ያምናሉ::
ልጆችን በመልካም ሥነ ምግባር እና በተሟላ ሥብዕና ለማሳደግ ወላጅ የመጀመሪያ ተመራጭ ቢሆንም በማያውቁት ሞግዚት ቤት ጥሎ ከመሄድ ሕጋዊነት ባለው ሕፃናት ማዋያ ማዋል ጥሩ አማራጭ እንደሆነ በማሰብ እና ለሙያው ባላቸው ፍቅር ለጥቂት ጊዜያት ሠርተዋል::
በአሁኑ ወቅት ግን ሥራ የጀመሩበት ቦታ አመቺ ባለመሆኑ ሌላ ሥራ ጀምረዋል:: የሥነ ልቦና ትምህርቱ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የሚተገበር ፣ ሥራን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል በመሆኑ አሁን ለሚሠሩበት የሙያ ማሰልጠኛ ተቋም እየረዳቸው መሆኑን ይገልፃሉ:: በቀጣይም በተለይ ለሕፃናት መዋያ (ዴይ ኬር) የመክፈት ህልማቸውን ለማሳካት ጥረታቸው እንዳልተቋረጠ ነግረውናል::
በተለይ ደግሞ ችግረኛ ባለቤታቸውን በተለያየ ምክንያት ያጡ እናቶች ልጆቻቸውን በነፃ የሚያቆዩበት የሕፃናት መዋያ ለመክፈት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በተለያየ ምክንያቶች ባይሳካላቸውም ተቋሙ እውን አስኪሆን ጥረታቸው እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል:: ወይዘሮዋ ባሁኑ ወቅት ከገቢ ማስገኛ ሥራቸው በተጨማሪ የጤና፣ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች እና ሌሎች ጋር ናዳል የተሰኘ ድርጅት በማቋቋም የምክክር /ካውንስሊንግ/ አገልግሎት፣ሕይወት ክህሎት ሥልጠና ፣ ከትዳር በፊት ፣በኋላ እና የትዳር ላይ ምክክር፣ ልጆች ጤና ላይ… የተለያዩ ጥናታዊ ፅሑፎችን (ሞጂሎች) በማዘጋጅት እንዲሁም በማሠልጠን እየሠሩ እንደሆነ ገልፀዋል::
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም