የምድርን ሁለት በመቶ ወይም ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ስኩዌር ማይል የሚሸፍነው የአማዞን ደን በ”ፎቶ ሲንተሲስ” 20 በመቶ ኦክስጂንን ያመርታል፡፡ በዚህም የምድር ሳንባ በሚል ስያሜ ተሰጥቶታል::
በጀርመን የሚገኘው የአየር ንብረት ተጽእኖን የሚያጠናው የፓስትዳም ተቋም ተመራማሪዎች ባካሄዱት ምርምር በብራዚል ደቡብ ምስራቅ ክፍል የሚገኘው ከፊል የአማዞን ደን “ካርበንን” ከሚያሰርገው የሚለቀው መርዛማነት እንደጨመረ ደርሰውበታል::
ከተቋሙ ተማሪማሪዎች አንዱ ቦሪስ ሳክሴቢሺኪ በደኑ ክልል የሰዎች አጥፊ ግፊት እየጨመረ መሄዱ ዘላቂነቱን አሳሳቢ እንዳደረገው ነው የገለጹት።
በአማዞን ደን ላይ የሚደርስ ውድመት እና የሚያስከትለው የከፋ ችግር በቀጣናው ብቻ ተገድቦ የሚቀር አለመሆኑን የገለፁት ተመራማሪው ወደ ሌሎች ጫፍ እንደሚዛመትም ነው የጠቆሙት::
“ሚቴን” መርዛማ ትነት የተቀመጠውን የመጨረሻ ገደብ ወይም ጫፍ ካለፈ በስነ ምህዳር እና በነዋሪዎች ላይ መቆጣጠር የማይቻል ተጽእኖ ያደርሳል:: ከዚህ ውስጥ የአማዞን ደን ውድመት ለሚፈራው የከፋ ችግር መንስኤ ይሆናል ተብሎ ነው – በተመራማሪዎች የተነገረው።
የመጨረሻውን የከፋ ተጽእኖ ከወዲሁ ከሚያመላክቱ ፍንጮች መካከል ለአብነት በግሪንላንድ እና በምዕራብ አንታርክቲክ የግግር በረዶ ንጣፎች መቅለጥ፣ የውቅያኖስ መሞቅ እና የባህር ዳርቻ ዛጐሎች መጥፋት ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው::
የአማዞን ደን በክልሉ ከሚፈሱ ወንዞች ባሻገር በስሮቹ ከመሬት ውስጥ ርጥበትን ስቦ በቅጠሎቹ ለከባቢ አየር የሚያበርክተው ርጥበት ይቋረጣል:: ይህ ለደቡብ አሜሪካ እና አጐራባች ቀጣና የዝናብ መንስኤ መሆኑ እንደሚገታም ነው ተመራማሪው ያመላከቱት::
ዓለም አቀፉ የተመራማሪዎች ቡድን የአማዞንን የመቋቋም አቅም ለመጠበቅ የአየር ንብረት እና የመሬት አጠቃቀም ገደቦችን አመላክተዋል:: ከነዚህ መካከል አማካይ አመታዊ ዝናብ ከ 1 ሺህ 800 ሚሊ ሜትር እንዳይቀንስ፣ በደኑ ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ እና ቃጠሎን ማመናመን፣ የደን መራቆትን መግታት እንዲሁም ደኑን መልሶ የማቋቋም ተግባራት በቅንጅት መሰራት እንደሚኖርባቸው ነው የጠቆሙት።
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም