በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ከአሜሪካን (ሰሜን እና ደቡብ) በእጥፍ የሚሰፋ “ሳርጋሰም” የተሰኘ ቡናማ ቀለም ያለው የባህር አረም ከጠፈር ሊታይ በሚችል መጠን መንሰራፋቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
አረሙ ለመጀመሪያ ጊዜ በተመራማሪዎች በጠባብ ቀጣና የታየው በ2011 እ.አ.አ ሲሆን ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ 8850 ኪሎ ሜትር ርዝመት መንሰራፋቱ ነው የተጠቆመው፡፡ቀጣናውም ከምዕራብ አፍሪካ እስከ ሜክሲኮ ባህረ ሰላጤ መዝለቁን አረጋግጠዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡
ለአረሙ መስፋፋትም የሙቀት፣ የ “ናይትሮጂንን እና “ ፎስፈረስ” መጠን መጨመር ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረለት ነው ተመራማሪዎቹ ያብራሩት፡፡
ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ግዛቱን በዕጅጉ እያስፋፋ ለመምጣቱ በውቅያኖስ ዳርቻ ከእርሻ መሬት ተጠርገው ፍሳሽ አረም፣ ውጋጆች ወደ ባህር ውስጥ መግባት የ “ናይትሮጂን” እና “ፎስፈረስ” መጠን እንዲጨምር ማድረጋቸው ለአረሙ መስፋፋት ገፊ ኃይል መሆኑን ነው የገለጹት -ተመራማሪዎቹ፡፡
የአረሙ በውቅያኖሱ ላይ መንሰራፋት በውስጡ ለሚገኙት የዓሳ ዝርያዎች፣ ዔሊዎች፣ የተለያየ ስነ ምህዳር እንዲኖር ቢያደርግም በተቃራኒው የተለያዩ ጉዳቶች ሊያደርስ እንደሚችልም ነው የጠቆሙት – ተመራማሪዎቹ፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት “ሳርጋሶ” በተሰኘው የባህር ቀጣና ተወስኖ ይታይ የነበረው አረም በብክለቶች መስፋፋት ሁኔታዎች ተመቻችተውለት ወደ ሰፊው ፓስፊክ መግባቱን ነው ባለሙያዎች ያስረዱት፡፡
በማጠቃለያነት ግዙፍ አረም በካይ ትነት በመልቀቅ የሙቀት መጨመርን ሊያባብስ፣ እንዲሁም በባሕር ዳርቻዎች የሚኖር የቱሪዝም እንቅስቃሴን ሊገታ እና በኒውክሊዬር ኃይል ማመንጫዎች ላይም ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል በማሳሰብ ነው የድረ ገጹ ጽሁፍ ያደማደመው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


