አሻጋሪዉ መንገድ

0
20

እ.አ.አ በ2050 የዓለም ሕዝብ የምግብ ፍላጎት አሁን ካለበት በ70 በመቶ እንደሚጨምር የዓለም ባንክ ትንበያ ያሳያል:: ይህን ደግሞ ዝናብ ላይ በተመሠረተ ግብርና ብቻ ማሳካት አይቻልም::

ዓለም አሁናዊ 60 በመቶ የምግብ ፍላጎቷን እያሳካች ያለችው ዝናብ ላይ ጥገኛ በሆነ የግብርና ሥራ (መደበኛ የእርሻ ሥራ) ነው:: 40 በመቶ የሚሸፈነው ደግሞ ከመስኖ ልማት በሚገኝ ምርት እንደሆነ የዓለም ባንክ የ2025 እ.አ.አ መረጃ ያመላክታል::

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የዓለም ሀገራት የውኃ አጠቃቀምን በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነታቸውን ለማሳካት እና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማቅረብ መስኖን በዋናነት እየሠሩበት ይገኛሉ:: እስራኤል ደግሞ ውጤታማ የውኃ አጠቃቀምን በመተግበር መስኖን ለምርታማነት ቀዳሚ መፍትሔ አድርገው ለመሥራት ላቀዱ ሀገራት በተሞክሮነት የምትነሳ ሀገር ሆናለች::

ምንም እንኳን ሀገሪቱ የተትረፈረፈ የውኃ ሀብት ባይኖራትም በውኃ ሀብት አጠቃቀም እና  በምርታማነት አርዓያ ናት፤ በሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሎጂ መምህር የነበሩት እና የዘርፉ (በዋናነት መስኖ ልማት) ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጆን ላንግፎርድ “እስራኤል በደረቃማ አካባቢዎች መኖር እንደሚቻል ያሳየች ሀገር ናት” በማለት ነበር ምስክርነታቸውን የሰጡት:: የጠብታ መስኖ ቴክኖሎጂ ደግሞ ለዚህ መፍትሔ ስለመሆኑ ፕሮፌሰሩ መናገራቸውን የጥናት ውጤቶችን ይፋ የሚያደርገው ሪሰርች ጌት የተባለው ድረ ገጽ መረጃ ያመላክታል::

እስራኤል በቆዳ ስፋቷ ከኢትዮጵያ በ50 እጥፍ የምታንስ ሀገር ናት:: የሀገሪቱ የግብርና እና ምግብ ዋስትና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል ካላት አጠቃላይ መሬት ውስጥ ለእርሻ ተስማሚ የሆነው 20 በመቶ ብቻ ነው:: ከዚህ ውስጥም 54 በመቶ በዝናብ ታግዞ በመስኖ ይለማል::

የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያመላክተው ሀገሪቱ ያላት የእርሻ መሬት አነስተኛ ነው፤ ይህም በዝናብ ላይ በተመሠረተ እርሻ የምግብ ዋስትናዋን ማረጋገጥ አያስችላትም:: በመሆኑም ለመስኖ ልማት ትኩረት ሰጥታለች::

አብዛኛው ክፍሏ በረሃማ መሆኑ ግን በመስኖ ልማት ውጤታማ እንዳትሆን አስግቷት ነበር፤ ይሁን እንጂ ለስጋቱ መፍትሔን በመተግበር በዘርፉ በትኩረት መሥራቷን ቀጠለች፤ በረሃማ አካባቢዎችን በማልማት ምርታማነትን ሊያሳድግ የሚችል ቴክኖሎጂን ተግባራዊ አደረገች::

እስራኤል በውኃ አያያዝ በተለይም በረሃማ አካባቢዎችን ለልማት በማዋል የዓለም መሪ ናት። የሀገሪቱ የግብርና ፈጠራ መገለጫ የሆነው ጠብታ መስኖ ደግሞ በዓለም የተሞክሮ ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል:: የጠብታ መስኖ ልማት ሥርዓት ተንሳፋፊ መስኖ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ውኃው በመንጠባጠብ ወደ ታች እየወረደ የተክሎችን ሥር እና በአቅራቢያቸው ያለን ደረቅ መሬት ያረሰርሳል::

የጠብታ መስኖ ውኃን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ ፋይዳ አለው:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የመሐንዲሶችን፣ ሳይንቲስቶችን እና ሌሎች ባለሙያዎችን ሥራዎች በተመለከተ መረጃዎችን የሚያጋራው ፍሉየንስ ኮርፕ የተባለው ገጽ (www.fluencecorp.com) እንዳስነበበው እስራኤል በአሁኑ ጊዜ 90 በመቶ የሚሆነውን ጥቅም ላይ የዋለ ውኃ እንደ ገና በመጠቀም በምሳሌነት የምትነሳ ሀገር ናት:: ይህ ደግሞ ጨዋማነትን በማስወገድ ምርታማነትን ማሳደግ ተጨማሪ ጠቀሜታን ያስገኛል::

በተመሳሳይ የጠብታ መስኖ ልማት ከፍተኛ እና ጥራት ያለው ምርት በመስጠት፣ የውኃ ትነትን በማስቀረት፣ ኃይል በመቆጠብ እና በዝቅተኛ የውኃ ግፊት በመሥራት፣ የአፈር ማዳበሪያን እና የሰብል ጥበቃን ውጤታማ በማድረግ፣ የአፈር መሸርሸርን በማስቀረት፣ በማንኛውም የመሬት አቀማመጥ እና የአፈር ዓይነት ውስጥ ውጤታማ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) አስታውቋል:: ቴክኖሎጂው የውኃ አጠቃቀምን እስከ 50 በመቶ ይቀንሳል፤ የሰብል ምርታማነትንም እስከ 30 በመቶ ይጨምራል::

እስራኤል በብዛት የምታመርተው የዓለም ገበያን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሲሆን በዋናነት ደግሞ የፍራፍሬ ዘርፍ ነው:: ለአብነትም እስራኤል የፍራፍሬ ምርትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ በዓመት በአማካኝ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ያሳወቀው ሳይንስ ዳይሬክት (www.ScienceDirect.com) የተባለው ድረ ገጽ ነው::

ቬትናምን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የግብርና ዘርፋቸውን ለማዘመን፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡትን ምርት ለማሳደግ የእስራኤልን የመስኖ ቴክኖሎጂ በመቅዳት እያስፋፉ ነው:: ቬትናም ያጋጠማትን የውኃ እጥረት ለመፍታት እና በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋልባትን ውጤታማ ያልሆነ የመስኖ ልማት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የእስራኤልን የጠብታ መስኖ እ.ኤ.አ ከ2023 ጀምሮ እየተገበረች ነው:: ውጤታማ እንደሆነችም ነው የተነገረው::

በሌላ በኩል ከፍተኛ የውኃ ሀብት እንዲሁም ለግብርና ሥራ የተመቸ ሰፊ መሬት ያላት አፍሪክ አብዛኛው ሕዝብ በከፋ ድህት ውስጥ የሚገኝ ነው፤ ለአብነትም ከአራት ሰዎች አንዱ ለረሃብ የተጋለጠ እንደሆነ   መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ለዚህ ደግሞ ያልዘመነ የግብርና ሥራ፣ የውኃ ሀብት አጠቃቀም እና የመስኖ ልማት ላይ የሚታይ ዝቅተኛ ግንዛቤ በዋና ምክንያትነት ተነስተዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግብጽ የውኃ አጠቃቀም ክፍተት ቢስተዋልባትም በመስኖ ልማት በአርዓያነት የምትጠቀስ ሌላኛዋ ሀገር ናት፤ በሰብል፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ውጤታማ የሆነችው ሀገሪቱ ለዓለም ገበያ በማቅረብም ከፍ ያለ ገቢ ታገኛለች::

ሲ ጂ ቲ ኤን አፍሪካ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው ለግብጽ ስልጣኔ መስኖ የጎላ ድርሻ አለው፤ የመስኖ ገንዳዎች (Basin Irrigation) ደግሞ ዋናው የጥንት የመስኖ ዘዴያቸው ነው። ይህም የውኃ መጥለቅለቅን ለመቆጣጠር ያስችላል።

ከፍተኛ የውኃ ብክነትን ግን መቆጣጠር አልቻለችም በሚልም ትተቻለች። ችግሩን ለማስቀረት ታዲያ ቴክኖሎጂን በፖሊሲ አስደግፋ (ስማርት ቴክኖሎጂዎች) እየተገበረች መሆኑን የመረጃ ምንጩ አክሏል።

በሌላ በኩል ከፍኛ የውኃ ጸጋ ያላት ኢትዮጵያ ባላት ሀብት ልክ ተጠቃሚ አይደለችም፤ ዘርፉ አለመዘመኑም ተጠቃሽ ምክንያት ነው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ያላትን ከፍተኛ የእርሻ መሬት ከእምቅ የውኃ ሀብቷ ጋር በማቀናጀት ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሠጥታለች፤ ይህም የዜጎችን የምግብ ዋስትን ለማረጋገጥ ያስችላል ነው የተባለው::

የትኩረቱ ማሳያ ሀገሪቱ ካላት የተመቸ የልማት ቀጣና ውስጥ ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችለውን በጥናት መለየት፣ የተለያየ አቅም ያላቸውን የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን መገንባት፣ የወደ ፊት ልማትን ሊሸከም እና ሊያዘምን የሚችል ዘመናዊ አሠራርን ማስተዋወቅ ተጠቃሽ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል:: የአፈር ማዳበሪያን የአቅርቦት እና የዋጋ ውድነት በመፍታት በዘርፉ ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ ለመውጣትም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ትገኛለች::

በተመሳሳይ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በ2015 ዓ.ም በዓለም ባንክ ድጋፍ ሀገሪቱ ለመስኖ ልማት ልታውለው የምትችለውን የመሬት መጠን በጥናት ለይቷል:: በጥናቱ መሠረት 10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ እንደሚችል ተረጋግጧል:: ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለግብርና መር ኢንዱስትሪ ዘላቂ ስንቅ እንደሚሆን ነው ሚኒስቴሩ ያመላከተው::

በአሁኑ ወቅትም ሀገሪቱ የመስኖ ልማት ሥራን በትኩረት እያከናወነች ትገኛለች:: ውጤትም አስገኝቷል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየዳረጋት የነበረውን የስንዴ ምርት ለማስቀረት በተሠራው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ውጤታማ መሆኗ ደግሞ ማሳያ ነው::

መንግሥት ለመስኖ ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ስንዴ ከውጪ ማስገባት እንዳቆመች የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አብዱራህማን አብደላ አስታውቀዋል፤ በመስኖ መሠረተ ልማት ሥራ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ በጥናት እና ዲዛይን እንዲሁም በበጀት አስተዳደር ያሉ ሥራዎችን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል::

ወቅቱ የ2018 የበጋ መስኖ ልማት ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር የሚገባበት ነው፤ ከአራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማትም ታቅዷል:: በዚህም ከ175 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር  29  ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here