ለውጡ አመራርን ከመቀየር የተሻገረ እንዲሆን ተጠየቀ

0
194

የሕብረት ሥራ ማሕበራትን ውጤታማነት ለማሳደግ ወደ ለውጥ ሥራ (ሪፎርም) መገባቱ ተነግሯል።  የለውጥ ሥራውም አመራርን ከመቀየር የተሻገረ መሆን እንዳለበት ነው የተገለፀው።

በኢትዮጵያ ከ110 ሺህ በላይ የሕብረት ሥራ ማሕበራት እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በአማራ ክልል እንደሚገኙ ተመላክቷል። ይሁን እንጂ ሕብረት ስራ ማሕበራቱ የቁጥራቸውን ያህል በአደረጃጀት፣ በአመራር፣ በአሠራር፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በገበያ ተሳትፎ፣ በካፒታል አቅማቸው፣ በቁጠባ እና ብድር ሽፋን፣ በሕጋዊ ማዕቀፍ እና በመሰል ጉዳዮች ክፍተቶች እንዳሉባቸው ሰሞኑን በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደ ምክክር ተነስቷል። ይህም ብቁና ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ነው የተባለው።

ለዚህም የአማራ ክልል የሕብረት ሥራ ማሕበራት ባለስልጣን አዲስ ሪፎርም (ማሻሻያ) ትግበራን ይፋ አድርጓል። ለዚህም ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ “የሕብረት ሥራ ማሕበራት ከማደራጀት ባሻገር” በሚል መሪ ሐሳብ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ከሰሞኑ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል። በወቅቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ለውጡ ከማደራጀት ባሻገር በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አቅም እንዲኖራቸው በሚያስችል መልኩ ሊተገበር እንደሚገባ አሳስበዋል። ማሕበራቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር እና የአባላቱን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር የሀገርን ምጣኔ ሀብት እና ማሕበራዊ ልማት የማፋጠን ሚናቸው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል። ለውጡም ታዲያ አመራሩን ከመቀየር ባሻገር አሠራርን፣ አቅምን እና ክህሎትን ማሻሻል እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሕብረት ሥራ ማሕበራት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ የሕብረት ሥራ ማሕበራትን በማዘመን የሀገርን ምጣኔ ሀብት እንዲደግፍ ሪፎርም (ለውጥ) አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። ክልሉ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የለውጥ ትግበራውን መጀመሩ የሚደነቅ መሆኑንም ገልፀዋል።

የአደረጃጀት ችግር፣ የአሠራር እና የአመራር ብቃት ጉድለት፣ የገንዘብ አቅም እና አስተዳደር ክህሎት ማነስ፣ ራስን ከሁኔታ ጋር ማጣጣም አለመቻል፣ በተደራረበው ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የተለወጠውን ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ መቋቋም እና ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል አለመቻል፣ ግልጽ የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ ጉድለቶች ለለውጡ አስፈላጊ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለውጡ ብልሹ እና ኋላቀር አሠራሮችን ከማስወገድ ባለፈ የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያሳድግ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል ሕብረት ሥራ ማሕበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ጌትነት አማረ ናቸው።

በክልሉ የሚገኙ የሕብረት ሥራ ማሕበራት በቁጥር ከሀገር አቀፍ ቀዳሚውን ደረጃ የያዙ ቢሆንም በገንዘብ እና በአመራር ብቃት ውስንነቶች ያሉባቸው መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ሁለንተናዊ አቅማቸውን ለማሳደግ ሪፎርም (ለውጥ) ማስፈለጉን አስረድተዋል። የሕብረት ሥራ ማሕበራቱ በየተደራጁበት ዘርፍ ውጤታማ፣ የአባላትን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ እና በገበያው ላይ ተሳትፏቸው ከፍ ብሎ በምጣኔ ሀብቱ እና በማሕበራዊ ዕድገቱ የተሻለ አበርክቶ እንዲኖራቸው በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንዳብራሩት ሕብረት ሥራ ማሕበራት በምጣኔ ሀብታዊ እና ማሕበራዊ ልማት ሚናቸው የጎላ ቢሆንም አሁንም ድረስ ውስብስብ ችግሮች አሉባቸው። በመሆኑም ችግሮቹን ለመፍታት ተቋማትን በማዘመን ብቁ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here