አቋራጩ መሿለኪያ

0
59

 

በቻይና ሰሜን እና ደቡብ ዢንጂያንግ ግዛትን ለማገናኘት በተራሮች ውስጥ ተቦርቡሮ የተዘረጋው 22 ኪሎ ሜትር የተለካው የፍጥነት መሿለኪያ መንገድ በዓለም በርዝመቱ ቀዳሚ መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል፡፡

ቀደም ብሎ በነበሩት ዓመታት 2500 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የቲያንሺን ተራራ ማእከላዊ ዢንጂያንግ ግዛትን በሰሜን እና ደቡብ ይከፍለዋል፡፡ እናም ከአንዱ ወደ ሌላው ለመጓጓዝ ከሰባት ሰዓታት ያላነሰ በተሽከርካሪ የተጠማዘዘ ጉዞ መከወንን ግድ ይል ነበር፡፡

እስከ አራት ሺህ ሜትር ከፍታ ያላቸው ተራሮችን አቆራርጦ በክረምት ጐዳናዎች ሲዘጉ መስተጓጐልም አይቀሬ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ያሁሉ ታሪክ “ነበር” ሆኗል ድረ ገጹ እንዳሰፈረው፡፡

 

የግንባታ ድርጅቱ መሀንዲስ ሚያኦ ባኦዶንግ ቻይና ዴይሊ ለተሰኘው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ኘሮጀክቱ ረዢም የዋሻ ውስጥ ቅኝት እና ንድፍ፣ አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው የግንባታ ስልቶች እና ለሚያጋጥሙ ችግሮች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፈጣን መፍትሄን ግድ ብሏል፡፡

የግንባታው ስራ በአምስት ዓመታት መጠናቀቁን የጠቆሙት መሀንዲሱ በአጠቃላይ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ መደረጉንም ነው ያሰመሩበት፡፡

 

ባለፉት ዓመታት በተለይም ዝናብ በሚበዛባቸው ወራት ዙሪያ ጥምጥም ማሽከርከርን ግድ ይል በነበረው የተያንሺን ተራራዎች ጠመዝማዛ መንገድ፣ በመሬት መንሸራተት የመንገዶች መዘጋት  እና ተሽከርካሪዎች ለቀናት ቆመው ያሳልፉ እንደነበርም ነው ለንባብ የበቃው፡፡ ይህንኑ ችግር ለመፍታት ሀገሪቱ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በዘርፉ ምን ያህል እንደመጠቀች የሚያሳየውን የመሰረተ ልማት ግንባታ በብቃት ማጠናቀቋ አብነት መሆኑ ነው በማጠቃለያነት የሰፈረው- በድረ ገጹ፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 18  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here