አባት ‘አልባ’ነት

0
23

አባት በቤተሰብ ውስጥ ያለው ሚና ከኢኮኖሚ አቅራቢነት በእጅጉ ይዘላል። አባት የጥንካሬ፣ የዲሲፕሊን፣ የማንነት እና የደህንነት ተምሳሌት ነው። ይሁን እንጂ በሞት፣ በፍቺ ወይም በቸልተኝነት ምክንያት በርካታ ልጆች ያለ አባት ለማደግ ይገደዳሉ። ይህ አባት አልባነት በልጆች ስነልቦና ላይ የሚተወው ጠባሳ ቀላል አለመሆኑን በርካታ ጥናቶች ያመለክታሉ።

የአባት አለመኖርን ጉዳይ በስፋት ከመረመሩት መጻሕፍት አንዱ በሱዛን ሽዋርትዝ የተጻፈው “ዘ አብሰንት ፋዘር ኢፌክት” ነው። ይህ መጽሐፍ ችግሩን ከሌሎች በተለየ ስነልቦናዊ ጥልቀት ይመለከተዋል። ሽዋርትዝ በመጽሐፏ ላይ ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን ታነሳለች። አባት በአካል ወይም በስሜት ከልጆቹ ጋር ላይኖር ይችላል የሚለውን።

አባት አልባነት ማለት በአካል አለመኖር ብቻ አይደለም። አባትየው በቤት ውስጥ በአካል እያለ ነገር ግን ለልጆቹ ፍቅር የማይሰጥ፣ የማይጫወትና ስሜታዊ ትስስር የሌለው ከሆነ፣ ልጆቹ ላይ የሚፈጠረው ስነ-ልቦናዊ ጉዳት አባቱ ከሌለ ልጅ ጋር ተመሳሳይ ወይም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ታስረዳለች። ይህንን ነው በስሜት አለመኖር የምትለው።

ሌላኛው ደግሞ አባት በሞት፣ በስደት፣ በፍቺ ወይም በእስራት ከልጁ ጋር የማይኖርበት አጋጣሚ ነው። ይህ አካላዊ አለመገኘት ተብሎ ይገለጻል። ልጆች አባታቸውን አያውቁም፤ አያዩም፤ ግንኙነት የላቸውም። “አባቴስ?” የሚል ጥያቄ እድሜያቸውን ሙሉ ይከተላቸዋል።

“ፋዘርለስ አሜሪካ” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ዴቪድ ብላንክንሆርን እንደገለጹት፣ አባት አልባነት ለህጻናት ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ችግሮች ቀዳሚ መንስኤ ነው። ያለ አባት የሚያድጉ ልጆች ለድብርት፣ ለጭንቀት እና ለዝቅተኛ በራስ መተማመን የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው።

በልጆች አስተደዳግ ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ያለ አባት የሚያድጉ ልጆች (በተለይም ወንዶች) ስሜታቸውን የመቆጣጠር ችግር ይገጥማቸዋል። አባት የሚሰጠው ገደብ እና ዲሲፕሊን ስለሚጠፋ በጉርምስና ዕድሜያቸው ለአመፅ እና ለሱስ የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ ነው። የአሜሪካ የትምህርት መምሪያ መረጃ  ያለ አባት ካደጉ ልጆች መካከል 71% የሚሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የማቋረጥ ዕድል አላቸው ብሏል። ሳይኮሎጂ ቱዴይ የአባት አለመኖር በሴት ልጅ ላይ የሚያደርሳቸውን ተፅዕኖዎች አስፍሯል።

የመተው (ብቸኝነት) ፍርሃት

የአባት አለመኖር ጥልቅ የሆነ የመተው ወይም የብቸኝነት ፍርሃትን ሊያሳድር ይችላል። ሴት ልጆች ከአባቶቻቸው ጋር ጠንካራ ግንኙነት ሲያጡ ያንን ስሜታዊ ክፍተት በሌላ ቦታ ለመሙላት ይሞክራሉ። ይህን ክፍተት መሙላት ለእነሱ በጣም አስፈላጊ ስለሚሆን ብዙውን ጊዜ ክፍተቱን መርዛማ ከሆኑ ግንኙነቶች ጋር እየሞሉ እንደሆነ ላያስተውሉ ይችላሉ።

ልቅነት እና ተጋላጭነት

ጥናቶች እንደሚያሳዩት አባት የሌላቸው ሴት ልጆች ቀድመው ወደ ወሲባዊ እንቅስቃሴ የመግባት ዝንባሌ አላቸው። በለጋ እድሜያቸው ወሲባዊ እንቅስቃሴ የሚጀምሩ ልጆች ለአባላዘር በሽታዎች (ኤችአይቪ/ኤድስን ጨምሮ) ላልተፈለገ እርግዝና እና ለአእምሮ ጤና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው።

ዝቅተኛ በራስ መተማመን

ለጤናማ ስሜታዊ እና ማህበራዊ እድገት ጠንካራ በራስ መተማመን ወሳኝ ነው። ያለ አባት መኖር ሴት ልጆች ለራሳቸው ያላቸውን ክብር ሊያሳጣ ይችላል። ይህ ደግሞ ወደ ተሳሳቱ ምርጫዎች፣ ትምህርት ላይ ወደ ኋላ ማለት፣ እንዲሁም ዝቅ አድርገው ከሚይዟዋቸው ሰዎች ጋር ወደሚኖሩ ጎጂ ግንኙነቶች ይመራል።

ጭንቀት እና ቅናት

የመተው ስሜት፣ ዝቅተኛ በራስ መተማመን እና የግንኙነት እጥረት ውህደት እንደ ጭንቀት እና ቅናት ያሉ ስሜታዊ ፈተናዎችን በግንኙነቶች ውስጥ ይፈጥራል። የአባት ስሜታዊ ድጋፍ አለመኖር ደህንነት እንዳይሰማቸው ያደርጋል። በዚህም እንደገና እንዳይተዉ ይፈራሉ።

ቀጥሎ ደግሞ አባት አልባነት በወንዶች ላይ ያለውን ተጽዕኖ እንመልከት።

 ለራስ ያለን ክብር ሊጎዳ እና የማንነት ቀውስ ሊፈጥር ይችላል

ልጆች “ከእኔ ይልቅ ለሌሎች ነገሮች ሁሉ ቅድሚያ ከሰጠ እኔ ዋጋ የለኝም ማለት ነው?”  እንዲሉ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ የራስን ማንነት ለማወቅ ወደሚደረግ የህይወት ዘመን ትግል ይመራል። ይህም ለአእምሮ ጤና ችግሮች ሊዳርግ ይችላል።

በግንኙነቶች ውስጥ የመተው ፍርሃትን ሊፈጥር ይችላል

የመተው ህመም ያጋጠመው ወንድ ልጅ መወደድ እንደማይገባው ሊሰማው ይችላል። ስለዚህ አባቱ ያደረገበትን ነገር በሁሉም ግንኙነቶቹ ላይ ያንጸባርቀዋል። ሁሉም ሰው በሆነ ወቅት ላይ ጥሎት እንደሚሄድ ይሰማዋል። በዚህም ምክንያት በራስ የመተማመን ስሜቱ ዝቅተኛ ይሆናል።

ጫና ሊፈጥር ይችላል

በአባቶቻቸው የመተው ስሜት ያጋጠማቸው ወንዶች ልጆች ብቁ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ማንም ሰው ወንድ እንደሆኑ አልነገራቸውም ወይም እንዴት ወንድ መሆን እንደሚችሉ አላሳያቸውም። ለመስራት እና ውጤት ለማምጣት ጫና ይሰማቸዋል። በቋሚነት በቂ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል።

ማረጋገጫ ወይም ተቀባይነትን አጥብቆ መፈለግን ያስከትላል

አንድ ወንድ ልጅ ከአባቱ ማረጋገጫ ወይም አዎንታዊ ትኩረት ካላገኘ ከሌላ ቦታ እና በተቻለ መጠን ከማንኛውም አካል ተቀባይነትን ይፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ወንዶች ልጆች ይህንን የሚያደርጉት በሌላ ሰው ኪሳራ ሌሎች እንዲስቁ በማድረግ ወይም እንደ መጠጣት፣ መኪና መወዳደር፣ ዕፅ መጠቀም ወይም ንብረት ማውደም በመሳሰሉ ከባድ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ በመሳተፍ ሊሆን ይችላል።  ከአባታቸው ማረጋገጫ በማጣት የተፈጠረውን ስሜታዊ ክፍተት ለመሙላት የማያቋርጥ የትኩረት እና የመቀበል ፍላጎት ሊሰማቸው ይችላል።

መፍትሄው ምንድን ነው?

የስነልቦና እና የማህበራዊ ሳይንስ ጥናቶች አባት አልባነትን ማከም የሚቻልባቸውን አማራጮች አቅርበዋል።  ብዙ ሰዎች አባት አልባ መሆናቸውን እንደ “የተለመደ” ነገር በመቁጠር ህመሙን ይክዱታል። ነገር ግን እንደ አሜሪካ ሳይኮሎጂ ማህበር  ያሉ ተቋማት እንደሚገልጹት መፍትሔው የሚጀምረው ክፍተቱ መኖሩን እና ይህም ስሜታዊ ጉዳት (እንደ በራስ መተማመን ማጣት፣ ብቸኝነት፣ ወይም ቁጣ) እንዳስከተለ አምኖ በመቀበል ነው።

ህመሙን፣ ንዴቱን ወይም ሀዘኑን አለመደበቅ። “አባቴ ባለመኖሩ ይህ ነገር ጎድሎብኛል” ብሎ ለራስ መንገር የመፈወስ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

አባት አልባነትን ለማከም አንዱና ዋነኛው መንገድ በህይወት ውስጥ አባት አከል (Father figures) ሰዎችን ማካተት ነው። “ናሽናል ፋዘርሁድ ኢንሼቲብ” የተሰኘው ተቋም ባደረገው ጥናት መሰረት አባት የሌላቸው ልጆች ከሌላ ኃላፊነት ከሚሰማው ወንድ ጋር ግንኙነት ሲፈጥሩ የስነልቦና መረጋጋት ያገኛሉ።

በዘመናዊ ስነልቦና “ሪፓረንቲንግ” የሚባል ጽንሰ ሀሳብ አለ። ይህ ማለት በልጅነትህ ከአባትህ ያላገኘኸውን ፍቅር፣ ማበረታቻ እና ዲሲፕሊን አሁን አዋቂ ሆነህ ለራስህ መስጠት ማለት ነው። ራስህን ከመውቀስ ይልቅ ማበረታታት፣ ለራስህ ድንበር ማበጀት እና ለራስህ ጥብቅና መቆም ማለት ነው።

ችግሩ ስር የሰደደ ከሆነ (ለምሳሌ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት፣ ሱስ ወይም የወንጀል ተባባሪነት ካለ) የሥነልቦና ባለሙያ ማማከር ትክክለኛው መንገድ ነው። ባለሙያዎች “ኮግኒቲቭ ቢሔቬራል ቴራፒን (CBT)” በመጠቀም የተዛቡ አስተሳሰቦችን ለማስተካከል ይረዳሉ።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የታህሣስ 13  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here