“አባ ይርጋ”

0
35

ልዑል ራስ ስዩም በአድዋ ከተማ የመስቀል በዓልን በማስመልከት ከሁሉም ሀገራት ለተወጣጡ ቆንጽሎች ግብዣ እያደረጉ ነበር:: በዚህ መሃል የጣሊያን ቆንጽል ጽሕፈት ቤት አባላት ግብዣው ሳያልቅ ይቅርታ ጠይቀው እየተጣደፉ ወጡ:: እነዚህ ጣሊያኖች ሀገራቸው በቅርቡ ወረራ እንደምትፈጽም ስለሚያውቁ ወደ ቆንጽል ጽሕፈት ቤታቸው በማቅናት ሚስጥራዊ መረጃዎችን ሲያቃጥሉ እና ሲያስወግዱ ቆዩ::

ከዚያም የሚችሉትን ያህል ጠመንጃ ይዘው መሸከም ያቃታቸውን ወንዝ ውስጥ ጨምረው ከኢትዮጵያ ለመውጣት ወደ ድንበር አቀኑ:: ጣሊያኖቹ ሃገራችንን እየሰለሉ ለሚያኪያሂዱት    ወታደራዊ ዝግጅት ሁለንተናዊ መረጃ አቀባዮች ነበሩ:: ከድንበር ለመውጣት እና ኤርትራ ከሚጠብቃቸው የጣሊያን ሠራዊት ጋር ለመቀላቀል ያረጉት ሙከራ በኢትዮጵያ ድንብር ጠባቂዎች ከሸፈባቸው፤ ድንብር ላይ ተያዙ:: እነዚህ ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ለመውጣት የዲፕሎማሲ ወረቀታቸውን እንኳ ለመጠቀም አልሞከሩም፤ ይልቁንም ለድንበር ጠባቂው አለቃ ጉቦ ሰጥተው ከኢትዮጵያ ለመውጣት ሞከሩ:: ነገር ግን ሀቀኛው የድንበር አለቃ ኢትዮጵያዊ፤ ቀን በክብር ግብዣ ሲጋበዙበት ወደ ነበረው ቤተ መንግሥት የፊጥኝ አስሮ ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ፊት አቀረባቸው::

የቆንጽል ጽ/ቤት ሠራተኞቹ አድዋ ውስጥ በሚገኘው ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ ተደረጉ:: በዚህ መሃል የጣሊያን አውሮፕላኖች የአድዋ ከተማን በቦንብ ደበደቡ:: ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ አስቀድሞ መረጃው ስለነበራቸው በጥሩንባ የአድዋ ከተማ ሕዝብ ከተማዋን በፍጥነት ለቆ እንዲወጣ አስነግረዋል:: በዚህም ሕዝቡ ላይ ይደርስ የነበረው ከፍተኛ ጉዳት ቀንሷል:: አድዋ ከተማ በቦንብ ስትደበደብ ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ እነዚያ ሰላይ የቆንጽል ጽ/ቤት ሠራተኞች ትዝ አሏቸው፤ ሰላዮቹ ተረስተው አድዋ ከተማ ውስጥ እንደታሰሩ ነው:: ልዑሉ ደነገጡ፤ ነገር ግን ምንም ማድረግ አይችሉም ነበር::

የቦንብ ድብደባው ካበቃ በኋላ ላይተርፉ ይችላሉ የተባሉት የጣሊያን ሰላዮች እነሱ የታሠሩበት ቦታ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት  በሕይወት ተገኙ:: የጣሊያን አብራሪዎች ሰላዮቹ የታሠሩበት ቦታ መረጃ ስለነበራቸው ሳይሆን፤ በአጋጣሚ ነበር እስር ቤቱ ያልተደበደበው:: ልዑል ራስ ስዩም ጣሊያኖቹን ካስመጡ በኋላ ምንም ሳያደርጓቸው አቆይተው፤ የንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ቴሌግራም ሲመጣላቸው አሳጅበው ወደ ወገኖቻቸው ጣሊያኖች ላኳቸው:: ይህ ታሪክ አዶልፍ ፓርለሳክ በጻፈው እና ተጫነ ጆብሬ በተረጎመው የሀበሻ ጀብዱ መጽሐፍ የትግራዩን ሀገረ ገዢ እና የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ የልጅ የልጅ ልዑል ራስ ስዩም መንገሻን በተመለከተ የቀረበ የታሪክ ማስረጃ ነው:: ከዚህ ታሪክ የልዑል ራስ ስዩም መንገሻን ርህራሄ፣ ሰው አማኚነት፣ ለቅጣት አለመቸኮል፣ ትዕዛዝ አክባሪነት እንመለከታለን:: በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ከስራቸው ተሰግስገው ራሳቸውን የሚሰልሏቸውን እና መረጃ የሚያወጡባቸውን ሰዎች እና ሀገራት ማወቅ እና መለየት አቅቷቸው ለጥቃት እና ለችግር የሚጋለጡበትን ሁነትን እንረዳለን::

የዚህ ጽሑፍ ባለታሪካችን ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ (አባ ይርጋ) በጎጃም ጠቅላይ ግዛት ዝምብሪ በምትባል የአገው ምድር ከተማ ውስጥ ሰኔ 17 ቀን 1878 ዓ.ም ነው የተወለዱት:: አባታቸው የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ልጅ እና አልጋ ወራሻቸው የሆኑት ራስ መንገሻ ዮሐንስ ሲሆኑ እናታቸው የአገው ምድር ባላባት የሆኑት ወይዘሮ ተዋበች ወልደ ገብርኤል ይባላሉ:: አባታቸው ልዑል መንገሻ ዮሐንስ ዐፄ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ የዳግማዊ ምኒልክ ተቀናቃኝ ነበሩ::

በተወለዱ በአራት ዓመታቸው ወደ አባታቸው ሀገር ትግራይ ሔደው የአማርኛ ትምህርት እና የአስተዳደር፣ ሥነ ሥርዓት፣ ሕግ እንዲሁም የመንፈሳዊ ትምህርት አጠናቅቀው ተማሩ:: በ10 ዓመታቸው የደጃዝማችነት ማዕረግ ተሰጧቸው ተንቤንን እና አበርገሌን እንዲያስተዳድሩ ተሾሙ:: በኋላም እንደርታ፣ ተምቤን፣ ሁለት አውላሎ፣ ሰላዋን እና ዋጅራትን ተሾሙ::

ራስ ስዩም የራስነት ማዕረጋቸውን በ1907 ዓ.ም ነበር ያገኙት:: ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አልጋ ወራሽ ሳሉ ማለትም በ1917 ዓ.ም የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ገዢ ሆነዋል:: ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፤ የተለያዩ ኒሻኖችን እና ሽልማቶችንም ከአውሮፓ መንግሥታት ተቀብለዋል:: የልዑልነት ማዕረጋቸውንም በ1922 ዓ.ም አግኝተዋል፤ የማርሻልነት ማዕረግ ደግሞ የንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የዘውድ በዓል በተከበረበት ቀን በ1923 ዓ.ም አግኝተዋል::

የልዑል ራስ ስዩም መንገሻ የመጀመሪያ ሚስታቸው የወሎው ንጉሥ ሚካኤል ልጅ እና የልጅ ኢያሱ እህት ወይዘሮ ተዋበች ናቸው:: ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ከወይዘሮ ተዋበች የልዑል አሰፋወሰን ኃይለ ሥላሴ ባለቤት የሆኑትን ልዕልት ወለተ እስራኤል ስዩምን ወልደዋል::

ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ በማይጨው ዘመቻ በሰሜን ጦር ግንባር የትግራይ ጦር አዛዥ ሆነው ተሰልፈዋል:: ጠላት ሀገራችንን ለመውረር በመጣ ጊዜ ከመረብ ጀምሮ ተምቤን እስከ ታላቁ ማይጨው ጦርነት ብዙ አሽከሮቻቸው ጦር ሜዳ መሥዋዕት እስኪሆኑ ድረስ በጀግንነት እና በእምነት ተዋግተዋል:: በዚሁ ጊዜ ባለቤታቸው ልዕልት አፀደ አስፋው ስንቅ በማደራጀት እና ለቆሰለም፤ ለታመም ከፍ ባለ ቆራጥነት እገዛ እያረጉ ከጎናቸው ተሰልፈዋል::

ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ከወታደሮቻቸው ጋር ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ማዘዣ ጣቢያቸውን ህዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም ወደ ደሴ ካዛወሩ በኋላ በትግራይ የሰፈረውን የወራሪው የፋሽስት ኢጣሊያ አዲሱ የጦር አዛዥ ማርሻል ባዶሊዮ ያለውን ኃይል ለመገመት አስበው፤ ታህሳስ አምስት ቀን የኢትዮጵያ የሰሜን ግንባር የጦር ኃይሎች ተቀናጅተው ማጥቃት እንዲጀምሩ ትእዛዝ አስተላለፉ:: የዚህ የማጥቃት ዋና ዓላማ የትግራይን የተለያዩ ስፍራዎች የተቆጣጠረውን የፋሽስት ጦር በተለያየ አቅጣጫ ማለትም በመሐል፣ በግራ እና በቀኝ አቅጣጫ በማጥቃትና ኃይሉን ለሁለት ከፍሎ በማዳካም በተለይ በግራ አቅጣጫ ያለው የኢትዮጵያ ጦር ኤርትራን ለመቆጣጣር ዕቅድ ነበረው::

በዚህም መሠረት በልዑል ራስ ስዩም መንገሻ የሚመራው 30 ሺህ ጦር ቀደም ሲል በጠላት እጅ ተይዛ የነበረችውን አቢ አዲን ለማስለቀቅ ታህሳስ 12 ቀን በከፈተው ጥቃት ጠላትን አሸንፎ መልሶ ተቆጣጥሯል በማለት ተክለ ጻድቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ተርከዋል:: ይሁን እንጅ የጠላት አይሮፕላን ያለማቋረጥ የሚያዘንበው የሙስታርድ ጋዝ እና ቦምብ እጅግ ብዙ የኢትዮጵያ ሠራዊት ስለጨረሰ እና ጦርነቱን በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ የሚዋጋበትን ሥፍራ ለቆ ወደኋላ በመመለስ ከልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ ጦር ጋር ሠራዊታቸውን ይዘው ወደኋላ በመመለስ ከንጉሠ ነገሥቱ ጦር ጋር ለመቀላቀል ተገደዱ:: ከማይጨው ሽንፈት በኋላ በሮም እና አዲስ አበባ በጣሊያን ግዞት ቆይተዋል:: በኋላም የጃንሆይን “በጠላትህ ላይ ክንድህን አንሳ” የሚል አዋጅ ተከትሎ 70 ሺህ የሚገመት ሠራዊት እየመሩ በሰቆጣ፣ ኮረም እና ማይጨው እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ከአንግሊዝ ወታደሮች ጋር በመተባበር ጠላትን ወግተዋል:: ጃንሆይ ከድል በኋላ ሀገራቸው መግባታቸውን ተከትሎ ልዑል ራስ ስዩም የትግራይ ግዛት ጠቅላይ ገዢ ሆነው ተሹመዋል::

ልዑል ራስ ስዩም በተቀበሉት አደራ መሠረት ሕዝባቸውን በቀናነት እና በታማኝነት ያገለግሉ ነበር:: የቤታቸውን በር ለሕዝብ ክፍት በማድረግ ግብሩ ዓመት እስከ ዓመት፣ ሳያቋርጥ ይወጣ ነበር:: ለታረዘው፣ ልብስ ለሌለው፣ ገንዘብ ለቸገረው እንደየፍላጎቱ ይረዱ እንደነበር ደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ’’ በሚል በ1962 ዓ.ም ባወጡት መጽሐፍ አትተዋል::

በ1953 ዓ.ም በተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት የመፈንቅለ መንግሥት ጠንሳሾቹ የመንግሥት ልዑላንን፣ መሳፍንትን፣ መኳንንትን እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ጠርተው አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሆነው በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ውስጥ አስረዋቸው ነበር:: ከታሰሩትም ውስጥ ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ አንደኛው ስለነበሩ የታሰሩት በሙሉ ያለምንም ምህረት በጥይት ሲረሸኑ እርሳቸውም አብረው ተረሽነዋል። በመጨረሻም አስከሬናቸው ወደ አክሱም ተወስዶ በአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል::

 

ሳምንቱ በታሪክ

ሕዳር ሲታጠን

የታሪኩ መነሻ፤ በ1911 ዓ.ም ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚሊዮኖችን ህይወት የቀጠፈው “እስፓኒሽ ፍሉ (ኤንፍሎይዛ)” እየተባለ የሚጠራው ወረርሽኝ ክስተት ነው።

በሽታው ይፋ የሆነው እ.አ.አ በሕዳር ወር 1918 ዓ.ም በስፔን እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ደግሞ የመጀመሪያው የበሽታው ምልክት በዓለም ላይ ከታየ ከአስር ወር በኋላ በሕዳር ወር 1911 ዓ.ም እንደሆነ ነው የሚነገረው::

በኢትዮጵያ ከሕዳር 7 እስከ ሕዳር 20/1911 ዓ.ም ለአስራ አራት ቀናት ገደማ ቆየ፤ በሽታው በሕዳር ወር የተከሰተ በመሆኑም ሕዝቡ “የሕዳር በሽታ” እያለ ይጠራው ጀመር::

ብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን ወልደቂርቆስ “የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት ወረርሽኙ እስከ 40 ሺህ ኢትዮጵያዊያንን ለሞት ዳርጓል። በተለይ አዲስ አበባን ክፋኛ እንደጎዳም ጽፈዋል።

አዲስ አድማስ ጋዜጣ በአንድወቅት ባስነበበው ጹሑፍ ደግሞ እስፓኒሽ ፍሉ ወረርሽኝ እ.አ.አ ከጥር ወር 1918 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 1920 ዓ.ም በመላው ዓለም 100 ሚሊዬን የሚጠጋ ሕዝብ ፈጅቷል ብሏል። በእርግጥ በወረርሽኙ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ያሻቀበ እንደሆነ የሚጠቅሱ መረጃዎች አሉ።

 

የሴቶችን ጥቃት የማስወገድ ቀን

ዓለም ዓቀፍ የሴቶችን ጥቃት የማስወገድ ቀን ህዳር 16/ 1992 ዓ.ም ወይም እ.አ.አ. ህዳር 25 1999 ሆኖ እንዲከበር የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ያስተላለፈው ህዳር 16 ነው::

እ.አ.አ. በ1960 የዶሚኒካን ሪፐብሊክ ተወላጅ የሆኑት እህታማቾች ማሪያ፣ ቴሬዛ እና ሚኔርቫ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ለመዘከር የሴቶች ጥቃት ማስወገጃ ቀን እንዲሰየም ሃሳብ ያመነጨችው ባለጉዳይዋ ዶሚኒካን ነች::

ምንም እንኳ የላቲን አሜሪካዎቹ እና የካሪቢያን ደሴት ሀገራት ዕለቱን እ.አ.አ. ከ1981 ጀምሮ እያከበሩት ቢገኙም ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ሀገራት ግን በይፋ ተቀብለው ለማክበር እ.አ.አ. እስከ 1999 ድረስ ዘግይተዋል::

ቀኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ እንዲከበር ጉዳዩ ያሳሰባቸው በርካታ ድርጅቶች እና በተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ፈንድ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል::

ምንጭ ፡ -ሂስትሪ ዚስ ዴይ

 

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here