አብሮነትን በሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ ትኩረት እንዲደረግ ተጠየቀ

0
80

የኪነጥበብ ሙያተኞች እና ባለሙያዎች በሕዝብ መካከል አብሮነትን በሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቆመ። የሙሉዓለም ባሕል ማዕከል በክልሉ ከሚገኙ የኪነጥበብ ሙያተኞች፣ የባሕል ማዕከላት እና የኪነጥበብ ማሕበራት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የባሕል ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ገብረማርያም ይርጋ እንደተናገሩት የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ትልቅ ነው። በመሆኑም ሀገራችንን ያለችበትን ሁኔታ በመረዳት የበኩላቸውን በመወጣት የችግሩን መውጫ መንገድ ማሳየት ይኖርባቸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም “የኪነ ጥበብ ሙያተኞች እና ባለሙያዎች በሕዝብ መካከል አብሮነትን በሚያጎለብቱ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው። የጠፉ ዕሴቶችን እንደገና እንዲጠናከሩ በማድረግ ሙያቸውን መጠቀም ይገባል” ብለዋል።

የኪነ ጥበብ ሙያተኞች ለዘርፉ አስፈላላጊ በሆነ በጀትና አሠራሮች አለመደገፋቸው፣ የኪነጥበብ ሙያተኞች የገጠማቸዉን ችግር ተወያይተዉ የሚፈቱበት መድረክ አለመዘርጋቱ እና መሰል ክፍተቶች ስለመኖራቸው በውይይቱ ተነስቷል። በዘርፉ ላይ ለተጋረጡ ችግሮችም ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለ ነው ተሳታፊዎች የተናገሩት።

በመሆኑም አስፈጻሚ አካላት የኪነጥበብ ምክር ቤት እንዲቋቋም ከማድረግ ጀምሮ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እደሚገባ ተሳታፊዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በውይይቱ የተገኙት የአብክመ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ  አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ኪነ ጥበብ ለማሕበረሰብ ለውጥና ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። የኪነ ጥበብ ሙያተኞችም ከራሳቸዉ ነፃነት በመነጨ ከፍ ባለ ራዕይ ሀገርን እና ትውልድን የመቀየርና ታሪክን የማሸጋገር አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።

በኪነጥበብ ዘርፉ የሚታየዉን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንደ ቢሮ ብቻ ሳይሆን እንደ ክልል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ በክልሉ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች፤ የዞን እና ወረዳ ባህል ማእከላት፤ ተወካዮች ተገኙ ሲሆን ንቁ ተሳትፎም አድርገዋል፤

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የሚዝያ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here