“አተርፍ ባይ…”

0
100

ሩሲያዊው ወጣት በተወሰነ ሰዓት ውስጥ ቁጭ ብድግ እያለ (squats) ሳያቋርጥ ሁለት ሺህ ጊዜ ለመስራት ተወራርዶ ቢያሽንፍም ለኩላሊት ህመም መዳረጉን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት ለንባብ አብቅቶታል::

በቅርቡ በሩሲያ ቭላዲቮስቶክ ሆስፒታል እድሜው በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኝ ወጣት ከመጠን በላይ አካላዊ እንቅስቃሴ በመስራቱ የህመም መልክቶች ከታዩበት በኋላ ሆስፒታል ገብቶ በተደረገለት ምርመራ የኩላሊት መታወክ (kidney failure) እንዳጋጠመው ተረጋግጧል::

ታማሚው ወጣት በሆስፒታሉ ለሃኪሞች እንዳስረዳው ከጓደኛው ጋር ተወራርዶ ካሸነፈ በኋላ  ነው የህመም ስሜቱ የጀመረው::

በአካላዊ ጥንካሬው እና ችሎታው በአሸናፊነት እንደሚረታ ተማምኖ ቢጀምረውም ካጠናቀቀ በኋላ የቋንጃ መተሳሰር፣ የመገጠጠሚያ እብጠት፣ የሽንት ቀለም መለወጥ የመሳሰሉትን በማስተዋሉ ወደ ህክምና ተቋም አምርቷል::

በሆስፒታሉ በተደረገለት ምርመራም (ራብዶዮሊሲስ) የተሰኘ የኩላሊቱ ህመም ወይም 50 በመቶ ኩላሊቱ የማጣራት ተግባሩ መቀነሱ ተነግሮታል::

እንደ እድል ሆኖ ሀኪሞቹ ባደረጉለት ርብርብ የኩላሊት እጥበት ሳይደረግለት ኩላሊቱን ሙሉ በሙሉ ስራውን ከማቆም ሊታደጉለት ችለዋል:: ያም ሆኖ የጤና እክሉ ወይም “ራብዶዮሊሲስ” ከተሰኘው ጉዳት ለመዳን ረዘም ያለ ጊዜ እደሚሻ አረጋግጠውለታል::

ወጣቱ ከደረሰበት የጤና ጉዳት ለመዳን ወይም ለማገገም ከሦስት ወር እስከ አንድ ዓመት ሊወስድበት እንደሚችል ነው የተነገረው- በመጨሻም ሆስፒታሉ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ጥንካሬ የሚገኘው ወይም የሚረጋገጠው በአካል  መፈፀም ወይም መከወን በመቻል ብቻ ሳይሆን አካልን በመንከባከብ  ጭምር መሆኑን በማስገንዘብ ነው  ያደማደመው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 29 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here