በታይዋን ኪሉዩንግ ሙዚየም የበጐ ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ሰራተኛ “ዊ አር ሚ” በሚል ስያሜ በተዘጋጀ የስነ ጥበብ ውጤቶች አውደ ርዕይ አቧራ በለበሰ መስታዉት ላይ ለዕይታ የቀረበን ስራ በለስላሳ ወረቀት በማፅዳቱ ሙሉ በሙሉ የጥበብ ውጤቱን ማበላሸቱን ኤንዲቲቪ ድረ ገጽ በህዳር ወር መባቻ ለንባብ አብቅቶቷል::
መገኛ ወይም ያሉበትን አካባቢ ዙሪያ መለስ ማፅዳት ተገቢ እና ከማንኛውም ሰው የሚጠበቅ ቢሆንም በአንዳንድ ቦታዎች ሁነቱን ተፈፃሚ ማድረግ ጥፋት እና ያልታሰበ የከፋ ውጤት እንደሚያስከትል በማሳያነት አስነብቧል ድረ ገጹ::
በኪሉዩንግ ሙዚዬም ከተሰበሰቡት የታዋቂ አርቲስቶች የጥበብ ውጤቶች መካከል “ኢንቨርትድ ሲንታክስ -16” በሚል ርዕስ ለዕይታ የበቃው የጥበብ ስራ አንዱ ነበር::
የጥበብ ስራው ቺን ሱንግ – ቺን በተባለ ጠቢብ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ማህበረሰብ ባህላዊ ንቃተ ህሊናውን በተምሳሌትነት ለማሳየት ታስቦ የተዘጋጀ ነው::
የጥበብ ስራው መስታወቱ ላይ ባለ አቧራ ወደ ውስጥ የፎቅ ቤት መውጫ መውረጃ ደረጃ ቆሽሾ፣ ጥርት፣ ፅድት ሳይል ተዝረክርኮ የሚያሳይ ነበር::
በአውደ ርዕዩ ዙሪያ ገባውን የሚያፀዳው በጐ ፈቀደኛ የተጠቀሰውን የጥበብ ስራ ሲመለከተው በዓዕምሮው የመጣው በአቧራ መበላሸቱ ሆን ተብሎ ሳይሆን ከመቆሸሽ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ አድርሶታል:: እናም በቃ ወደ ኪሱ እጁን ሰዶ ባገኘው “ሶፍት” መስታወቱን ያፀዳዋል::
ድረ ገጹ የጥበብ ውጤቱ ሳይፀዳ እና በበጐ ፈቃደኛው ድንገተኛ ያልታሰበ የፀዳት ስራ የተበላሸውን ግራ እና ቀኝ አስቀምጦታል:: የጥበብ ሀያሲያንም ገሚሶቹ የጥበብ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ መበላሸቱ ትልቅ ጥፋት ነው ሲሉ ገሚሶቹ በአጋጣሚ፣ ሳይታሰብ ለማፅዳት ታስቦ ብልሽት ወይም ጥፋት ደረሰበት የተባለውም ራሱን ችሎ በጥበብ ውጤትነቱ የአውደ ርዕዩ አካል ሆኖ መቀመጥ ይኖርበታል ሲሉ መሞገታቸው በማደማደሚያነት ለንባብ በቅቷል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የህዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


