አትሌቲክሱ ለምን ትኩረት ተነፈገዉ?

0
139

ኢትዮጵያ ለአትሌቲክስ ስፖርት የማይነጥፍ የተፈጥሮ ፀጋ ያላት ሀገር ናት። በየርቀቱ እንደ አብሪ ኮከብ የሚወረወሩ አትሌቶች የሚፈለፈሉባት ሀገር ጭምር ናት። በአበበ ቢቂላ የተጀመረው ገድል በትውልድ ቅብብሎሽ  በወንዶች ማሞ ወልዴን፣ ምሩጽ ይፍጠርን፣ ኃይሌ ገብረ ስላሴን፣ ቀነኒሳ በቀለን በሴቶች ደራርቱ ቱሉን፣ መሰረት ደፋርን እና ጥሩነሽ ዲባባን የመሳሰሉ ድንቅ አትሌቶች ወጥተዋል፡፡ አሁን ላይ ግን የእነዚህን ብርቅዬ አትሌቶች ገድል የሚያስቀጥል ትውልድ እየጠፋ ይገናል፡፡ በጊዜ ሂደት ዘርፉ እየደበዘዘ ስለመሆኑ ምልክቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ለአብነት ባለፉት ሁለት የኦሎምፒክ መድረኮች ሀገራችን ዝቀተኛ ወጤት ማስመዝገቧ አይዘነጋም፡፡ በዓለም ሻምፒዮናም ቢሆን ያን ያህል የሚያኩራራ ውጤት አልተመዘገበም፡፡

ዛሬም በቆየው ባህላዊ የስልጠና ሂደት እና አስተሳሰብ መመራታችን ዓለም ከደረሰበት የስልጠና መንገድ ለመጓዝ በብዙ ወደ ኋላ ቀርተናል። ከዚህ በፊት ነጮች በአትሌቲክሱ ዘርፍ ኢትዮጵያውያንን፣ ኬኒያውያንን፣ ዩጋንዳውያንን እና የመሳሰሉትን ሀገራት አትሌቶችን፤ በገንዘብ በማስኮብለል ነበር ውጤታማ ሲሆኑ የሚስተዋሉት። አሁን ላይ ግን የስልጠና ደረጃቸውን እጅግ በማዘመን አትሌቶቻቸው ከምስራቅ አፍሪካውያን አትሌቶች ቀድመው እንዲታዩ ሲያደርጉ እኛ ግን ባለንበት ተቸክለን ቀርተናል። እንዲያውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተተኪዎቹ ላይ እየተሠራ አለመሆኑ በርካታ የዘረፉ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአትሌቲክሱ ዘርፍ በተተኪዎች ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን በደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ የሆኑት አማረ ሙጬም ለአሚኮ በኩር ስፖርት ዝግጅት ክፍል ተናግረዋል። በዘርፉ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች እና አመራሮች ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸው ተተኪዎች በብቃት እንዳይወጡ አድርጓልም ብለዋል።

ከዚህ በፊት ለማሰልጠኛ ማዕከላት እና ለፕሮጀክቶች ከስፖርት ቁሳቁስ እና ትጥቅ ጀምሮ በትክክል የተለያዩ ድጋፍ እና ክትትል ይደረግ እንደነበር አሰልጣኙ አስታውሰዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የዘርፉ ባለሙያዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም ተብሏል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስን ጨምሮ የክልል ፌዴሬሽኖች የውድድር ሥርዓት ከመዘርጋት ውጪ ፕሮጀክቶችን እና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላትን በተገቢው መንገድ ሲደግፉ አይሰተዋልም።

ታዲያ ይህ ችግር  በአትሌቲክስ ስፖርት እንደ ሀገር ተተኪዎችን ለማፍራት እያደረገ ላለው እንቅስቃሴ መቀዛቀዙ ትልቁ መንስኤ መሆኑን ነው አሰልጣኝ አማረ ያስረዱት። ይሁን እንጂ በልጆች አትሌቲክስ ስፖርት እና በተለያዩ የሜዳ ተግባራት እና የመም ዝግጅቶች ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ በትግራይ ክልል፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ በትንሹም ቢሆንም አበረታች ሥራ እየሠራ ነው። ከእነዚህ ውጪ ግን እንደ በፊቱ ተተኪዎችን ለማፍራት እየትሠራ ያለው ሥራ እጅግ ተቀዛቅዟል ነው የተባለው።

ከባለፉት ዓመታት በተለየ ዘንድሮ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ለማሰልጠኛ ማዕከላት እና ፕሮጀክቶች የስፖርት ቁሳቁስ እና ትጥቅ ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት አሰልጣኙ ይህም ምርጫው በመድረሱ ትኩረት ለማግኝት ሊሆን እንደሚችል አልሸሸጉም። ያም ሆነ ይህ ግን ድጋፍ እና ክትትሉ ግን ቀጣይነት መኖር እንዳለበት አሳስበዋል። ውድድሮች ሲኖሩ በተደጋጋሚ የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ እንደ ችግር ሲነሳ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ዐይተናል። ታዲያ ባህል እየሆነ የመጣው ይህ ችግር በተተኪዎች ላይ አለመሥራቱንም ያረጋግጣል።

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ሲቋቋም ከዋና ዋና ተግባራቱ መካከል የታዳጊ ወጣቶች እና የሴቶች ተሳትፎ የሚያድግበትን ስልት መቀየስ፤ ምርጥ እና ተተኪ አትሌቶች እንዲወጡ ዘመናዊ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ማመቻቸት እና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘወተሪያ ሥፍራ እንዲሠሩ መደገፍ እውቅና መስጠት ይገኝበታል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የውድድር ስርዓት ከመዘርጋት እና መርሀ ግብሮችን ከማውጣት ያለፈ ተግባር እያክናወነ አይደለም በሚል ትችት ይቀርብበታል።

ታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርገው ያልሥሩ ፕሮጀክቶች እና የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ውድድር ላይ ሲቀርቡ ከክለቡ እና ከአካዳሚው የወጡ ልምድ ያላቸውን አትሌቶች ውጤት ለማስመዝገብ ሲያሳትፏቸው ማየት የተለመደ ነው። ይህ ማለት እንደ ሀገር በታዳጊዎች ላይ በበቂ ሁኔታ የሚሠራው ሥራ አነስተኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል አሰልጣኝ አማረ ሙጬ። ይህ ደግሞ የታዳጊዎችን ስነ ልቦና እና እድገት በእጅጉ ያቀጭጫል ነው የተባለው። አሁን ላይ ተተኪዎች በበቂ ሁኔታ እየወጡ ባለመሆኑ በታላላቅ አትሌቶች እና በታዳጊዎች መካከል የሚደረገው ሽግግርም ጤናማ አይደለም።

እናም ሀገራችን በዘርፉ ችግር እንዳይገጥማት ስጋትን ፈጥሯል። “በሀገራችን ውድድር የመዘርጋት ችግር አይስተዋልም፤ ከክልል እስከ ሀገር አቀፍ የውድድር እጥረትም የለም ነው የተባለው። ይሁን እንጂ በየእድሜ ክልሉ በበቂ ሁኔታ ስልጠናዎች እየተሰጡ አይደለም” ሲል ሰልጣኙ ተደምጧል። ስልጠናዎች የተቀዛቀዙበት ምክንያትም ባለሙያዎችን የሚደግፉ አካላት ባለመኖራቸው እንደሆነ ነው የተነገረው።

ስፖርቱን የሚመሩ አካላትም በበጀት እጥረት ሰበብ ምክንያት ስልጠናዎች እንዲሰጡ ባለመፍቀዳቸው ከ13፣ ከ15፣ እና ከ18 ዓመት በታች ታዳጊዎች ስልጠና ሂደቱን ጠብቆ እና በአግባቡ እንዳይከናወን አድርጓል። አሁን ላይ በሀገራችን ሰባት የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ተንታን እና ሀገረ ሰላምን የመሳሰሉ በጥሩ መንገድ ሥራቸውን የሚያከናውኑ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት እንዳሉ ሁሉ ለቁጥር ማሙያ የሆኑና ኃላፊነታቸውን የማይወጡ ማዕከላትም አሉ ተብሏል።

ስልጠና ለመስጠት ምቹ ከባቢ ባለመፈጠሩ እና አስፈላጊ ነገሮች ባለመሟላታቸው ምክንያት ነው የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ውጤታማ መሆን ያልቻሉት። በታዳጊዎች ላይ በተገቢው መንገድ ካልተሠራ አትሌቲክሱ ላይ የሚደርሰው ስብራት ከፍተኛ መሆኑን በ2023ቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና ባለፉት ሁለት የኦሎምፒክ መድረኮች ተመልክተናል። ለአብነት በዐስር ሺህ ሜትር ወንዶች በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ የወርቅ ሜዳሊያ ለማግኝት ከተቸገርን ቆይተናል። አሁን ላይ ተተኪዎች በበቂ ሁኔታ እየወጡ ባለመሆኑ በየመድረኩ የምናያቸው አትሌቶችም ተመሳሳይ መሆናቸው የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡

ታዲያ ይህ ችግር የሚቀረፈው እና ሀገራችን እንደቀደሙት ጊዜያት በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ ብሎ መጠራት የሚችለው ከታች ከታዳጊዎች ላይ መሠራት ሲችል መሆኑን አሰልጣኙ አጽንኦት ሰጥተውታል።  በበቂ ሁኔታ የስፖርት ማዘወተሪያ ሥፍራ አለመኖሩም የአትሌቲክሱን ዘርፍ ጎድቶታል። ከዚህ በፊት ምንም እንኳ በየቦታው ለመለማመጃ የሚሆን መም (Track) ባይኖርም ስፊ ሜዳ እና የማዘወተሪያ ሥፍራ እንደነበር አይዘነጋም። አሁን ላይ እነዚያ ቦታዎች ለተለያዩ የልማት ሥራዎች በመዋላቸው የማዘወተሪያ ሥፍራ እጥረት ተፈጥሯል። በሀገራችን አሁን ላይ ክፍት ሆኖ አገልግሎት የሚሰጥ በሱሉልታ የሚገኘው የቀነኒሳ በቀለ የልምምድ መዕከል ብቻ  መም (Track) ያለው መሆኑን አሰልጣኝ አማረ አስታውሰዋል። በስፖርት አካዳሚው የሚገኝው መም  (Track) ባልታወቀ ምክንያት አሁን ላይ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ጭምር ተነግረዋል።

ታዲያ ለስልጠና ምቹ ሁኔታ ባልተፈጠረበት ሁኔታ ተተኪዎች ላይ ለመሥራት ማሰብ አስቸጋሪ መሆኑን አሰልጣኝ አማረ ሙጬ ይናገራሉ። ወደፊትም ችግሩ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ግን የአፍሪካውያን ኩራት የሆነው አትሌቲክሳችን በትውልድ ክፍተት የመቋረጥ አደጋ የሚቃረብበት ቀን ሩቅ አይሆንም። ዘርፉ በአንድ ጀንበር ተሠርቶ ውጤት የሚመጣበት ሳይሆን በሂደት የሚገነባ ነው። እናም የረጅም ጊዜ ድካም እና ልፋት በሚጠይቅበት በዚህ ስፖርት ከወዲሁ በርካታ ሥራዎች መሥራትን እንደሚጠይቅም የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኙ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

በየእድሜ እርከኑ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሥልጠናዎች እንዲሰጥ እገዛ ሊደረግ ይገባል! የአሰልጣኙ አስተያየት ነው። በየክልሉ ያሉት ፌዴሬሽኖች ከዚህ በፊት ጥሩ ሥራ ሲሰሩ እንደነበር ያስታወሱት አሰልጣኝ አማረ አሁን ላይ ግን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ አለመሆኑንን ውጤቱን አይቶ መናገር ይቻላል ብለዋል። እናም ከታች ወርዶ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች እና ማሰልጠኛ ማዕከላት እገዛ ማድረግ እንዲሚያስፈልግም ተናግረዋል። “ይህ ካልሆነ የስፖርት ቁሳቁስ እና ትጥቅ ለክልል ፌዴሬሽኖች አስረከበ ማለት ለፕሮጀክት እና አትሌቲክስ ማዕከላት ድጋፍ ተደረገላቸው ማለት አይደለም” ብለዋል አሰልጣኝ አማረ ሙጬ። አሰልጣኞችም በዘርፉ ትውልድን ለማስቀጠል ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው ነው የተባለው። አሁን ላይ ለአትሌቲክሱ ለምን ትኩረት ተነፈገው የሚለውን በባለሙያ ማስጠናት እንደሚያስፈልግ ጭምር በመጠቆመ፡፡

ለዘርፉ ምቹ የሆኑ እና ያልተሠራባቸውን አካባቢዎች በመለየትም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሁሉም ድርሻ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here