እ.አ.አ በ1960 የሮም ኦሎምፒክ አበበ ቢቂላ ታላቅ ገድል ከፈፀመ በኋላ በሀገራችን እና በአህጉራችን በአትሌቲክሱ ዘርፍ ትልቅ መነቃቃት ተፈጥሯል። ከዛን ጊዜ ጀምሮ በሁሉም መድረኮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በረዥም እና በመካከለኛ ርቀት የሚቀድማቸው አልተገኝም። በተለይ ርዥም ርቀት በሁለቱም ፆታዎች የኢትዮጵያውያን ባህል ከሆነ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ተቆጥሯል። ታዲያ ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ካደረጉ እና እያደረጉ ካሉ ክልሎች አማራ ክልል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል።
አማራ ክልል ለአትሌቲክስ ስፖርት ፀጋውን አብዝቶ የሰጠው ክልል ነው። ምቹ የመሬት አቀማመጥ እና ተስማሚ የአየር ፀባይ አለው። ለዘርፉ የሚሆን ደጋ፣ ወይና ደጋ እና ቆላማ የአየር ፀባይ አለው። ይህን ፀጋ በመጠቀም አሁን ላይ አራት የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ተከፍተው ተተኪ ስፖርተኞችን እያፈሩ ሲሆን በርካታ ያልተጠናቀቁ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላትም በክልሉ ይገኛሉ።
አዲስ ከተቋቋሙ ከተማ አስተዳደሮች በቀር በሁሉም የክልሉ ዞኖች የማሰልጠኛ ማዕከላት ይገኛሉ። በክልሉ ስልጠና እየሰጡ ከሚገኙ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ውስጥ ተንታ፣ ደብረ ብርሃን፣ ጉና፣ በየዳ፣ ዳባት፣ ደባርቅ፣ ጃን አሞራ፣ ጎዛምን እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።
የተንታ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት አንዱ ነው። በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ቤቶች ፈራርሰው ንብረቶች ተዘርፈዋል፤ መረጃዎች እንዲጠፉ ሆነዋል። ማዕከሉን መልሶ ለማቋቋም ከወረዳ እስከ ክልል ድጋፍ ተጠይቆ ምላሽ እንዳልተገኘ እና ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በተገኘ ውስን ድጋፍ ስልጠናዎችን ማስኬድ እንደተቻለ ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ማዕከሉ አሁን ላይ ጥሩ ሊባል የሚችል ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በማዕከል ደረጃ በሚደረጉ እና በሀገር አቀፍ ውድድሮች ላይ አትሌቶችን እያሳተፈ ይገኛል። ማዕከሉ ከስሩ 59 አትሌቶችን እያሰለጠነ እንደሚገኝም ማወቅ ተችሏል።
የተንታ አትሌቲክስ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል የአጭር ርቀት አትሌት የሆነችው ወጣት መሠረት መኮነን ብቁ አትሌት ለመሆን የሚያስችላትን ስልጠና እና ልምምድ እያደረገች መሆኑን ትገልፃለች። የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት የሚያስችሉ ናቸው የምትለው አትሌት መሠረት በተንታ ማሰልጠኛ ማዕከል ሰልጥነው ሀገርን ወክለው መወዳደር የቻሉ ወጣቶች እንዳሉ ነግራናለች።
“በአሰልጣኞቻችን እና በወሎ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ እና አስተባባሪነት አንዳንድ ወድድሮችን እያደረግን እንገኛለን’’ በማለት ሃሳቧን ያጋራችው አትሌትዋ በክልሉ ላይ ያለው የሰላም መደፍረስ በክልሉ ውስጥ ይደረጉ የነበሩ የአትሌቲክስ ውድድሮች እንዲስተጓጎሉ አድርጓል በማለት ትናገራለች።
በሌላ በኩል የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ አቶ አማረ ሙጬ በክልሉ ላይ ባለው ቀውስ ምክንያት ዝግጅቶችን በተገቢው ጊዜና ቦታ እያደረግን አይደለም ብለዋል። ክልሉ ላይ ያለው የፀጥታ ሁኔታ በጀት ላይ ጫና ፈጥሮብናል ያሉት አቶ አማረ ሙጬ፣ በዚህም ምክንያት ተገቢ የሆነ ስልጠና መስጠት አልተቻለም ብለዋል።
በተጨማሪም በሰሜኑ ጦርነት በተፈጠረው ችግር የማሰልጠኛ ማዕከሉ ጉዳት ደርሶበታል። የጅምናዚየም መሳሪያዎች እና ሌሎችም የስፖርት ቁሶች ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን በህዳር ዘጠኝ ቀን 2017 ዓ.ም የበኵር ጋዜጣ እትም አሰልጣኝ አማረ ሙጬ መናገሩ አይዘነጋም። የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት በበጀት እና በፀጥታ ችግር ምክንያት ውድድሮች ለማካሄድ እየተቸገሩ መሆኑን አሰልጣኝ አማረ ተናግሯል።
የአማራ ክልል አትሌቲክስ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ገነቱ በክልሉ ስላሉ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ለበኩር ስፖርት ሃሳብ ሲሰጡ “ክለቦች አሉን፤ ማዕከላትም አሉን። መጀመሪያ ማዕከላትን ማጠናከር ታዳጊዎች ላይ መስራት ስለሆነ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ስልጠናዎችን እየሰጡ ይገኛሉ። ሆኖም በክልሉ ባለው ግጭት ጉዳት ያልደረሰበት የትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል የለም። ጉዳት ቢደርስም ግን ማዕከላቱ አትሌቶችን ከማሰልጠን ወደ ኋላ አላሉም” በማለት አብራርተዋል።
በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እና በበጀት እጥረት ምክንያት ውድድሮች እየታጠፉ እንደሆነም ጠቁመዋል። የክልሉ የስፖርት ምክር ቤት ለስፖርት በጀት ባለመበጀቱ ምክንያት ውድድሮችን ማድረግ ባይቻልም እንኳ ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው የሚል ማብራሪያም ሰጥተዋል።
በግጭቱም ሆነ በበጀት እጥረት ምክንያት የሚታጠፉ ውድድሮች ዘርፉን ለስብራት ይዳርጋሉ ብለዋል የጽ/ቤት ኃላፊው። የአትሌቲክስ የስልጠና ማዕከላት የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲያሳኩ የክልሉ መንግስት በጀት በጅተው በትኩረት እንደሚሰራ እምነት አለን በማለት ተናግረዋል።
የግንባታ ሥራቸው አልቆ ዝግጅት አጠናቀው የነበሩ ማሰልጠኛ ማዕከላት ወደ ሥራ ገብተዋል ወይ? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ የጽ/ቤቱ ኃላፊው ምላሽ ሲሰጡ “የዳባት አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ስራ ገብቷል፤ እውቅናም ተሰጥቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ የሰከላ ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠና መስጠት ጀምሯል። በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ተሳትፎ አዊልማ በሚል ስያሜ የተከፈተው የቲሊሊ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሁሉም ወረዳዎች ባለመስማማታቸው ለጊዜው ተዘግቷል” ብለዋል። ቀጣይ ላይ ለመክፈት መተማመን ላይ ደርሰናል፤ ከዚህ ውጭ ያሉ ሁሉም የማሰልጠኛ ማዕከላት ስልጠናዎችን እየሰጡ ይገኛሉ።’’ ሲሉ ተናግረዋል።
ዓመቱን ሙሉ ሲሰለጥኑ የነበሩ አትሌቶች ህልም እውን እንዲሆን እና የውድድር እድል እንዲያገኙ በማሰብ ወጣትና ስፖርት ቢሮ ከግለሰቦች ሳይቀር ገንዘብ በመበደር የአማራ ክልል አትሌቶች በሀገር አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ እያደረጉ መሆናቸውን ኃላፊው አክለዋል።
(አምኃ ሞገስ)
በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም