“አትሩጥ አንጋጥ” እንዴት?

0
205
ዘኢኮኖሚክ ታይምስ ገንዘብን ሲተረጉም የሰው ልጆች በተወሰነ ዘመን ምርትና አገልግሎትን ለመለዋወጥ የሚጠቀሙበት መገበያያ ነው ብሎ ያስቀምጣል። ይህ ትርጉም ሁሉም የሚግባበት ቀጥተኛና ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በእያንዳንዳችን ዘንድ የገንዘብ ትርጉም የተለያዬ ነው።የገንዘብ ትርጓሜው ከዚህም ይልቃል። የምንመለከትበት ዕይታ ለየቅል ነው። ይህ ትርጓሜያችን ደግሞ በሕይወታችን ላይ ልዩነት ይፈጥራል።
ፎርብስ መጽሔት የታዋቂ ቢሊየነሮችን ሀብት መጠን ይፋ ሲያደርግ በርናርድ አርኖልት እና ቤተሰቦቹን በቅድሚያ ያስቀምጣል። ይህ ቤተሰብ 221 ነጥብ አንድ ቢሊየን ዶላር የተጣራ ሀብት አለው። አሁን ዓለምን በሚያነጋግሩት የፈጠራ እና የንግድ ሀሳቦቹ የሚታወቀው ቢሊየነር ኢሎን መስክ 205 ነጥብ ሁለት ቢሊየን ዶላር ሀብት በመፍጠር በሁለተኛነት ተቀምጧል። ጄፍ ቦዝስ፣ ማርክ ዙከርበርግ፣ ላሪ ኤሊሰን እያለ እስከ 10ኛ ደረጃ ድረስ ይቀጥላል።
ከበርናርድ አርኖልት በስተቀር ሁሉም ቢሊየነሮች አሜሪካዊያን ባለጸጋዎች ናቸው። በርናርድ ፈረንሳዊና የ74 አመት አዛውንት ናቸው። ገንዘብን ሲተረጉሙትም “ገንዘብ ጥላ ነው ስል ለባልደረቦቼ እነግራችዋለሁ፤ ሥራችሁን በአግባቡ እስከሠራችሁ ጊዜ ድረስ ስለ ትርፋማነት አትጨነቁ። ትርፋማነት በራሱ ጊዜ ይመጣል” እላለሁ በማለት ገንዘብ ሥራን በጥራትና በትክክል የመስራት ውጤት መሆኑን ያስገነዝባሉ።
በሌላ በኩል ኢሎን መስክ” የኔ ጉዳይ ስለገንዘብ አይደለም፤ ለሚቀጥለው ትውልድ ችግሮችን ስለመፍታት እንጂ” ሲል ዓለምን የገጠሟትን ችግሮች ከመሸሽ፤ በችግሮች ከመቆዘም ያለፈ ችግርን እንደ ዕድል የመጠቀምን ቁርጠኝነት እንደሚወስድ እናያለን። ቀጥሎም “ ሁልጊዜም በፈጠርናቸው ኩባንያዎች ላይ ገንዘብን ፈሰስ አደርጋለሁ። የሌሎችን ሰዎች ሀብት ስለመጠቀም አስቤ አላውቅም። ትክክለኛ ሐሳብም አይመስለኝም። በራሴ ያላለማሁትን ፣ሌሎች ሰዎች የእኔን ድርጅት እንዲያለሙም አልጠብቅም” ይላል። በራስ ኀላፊነትን ስለመውሰድ ለራስ ዓላማ ራስ መትጋትን ያስገነዝባል።
ከዝነኞቹ የህይወት ክህሎት አሰልጣኞች አንዱ ዚግ ዚግላር የህይወት አመራርና አካሄድን በተመለከተ ሲናገር “ሀብታም ሰዎች ትንሽ ቴሌቪዥንና ትልቅ ቤተመጽሐፍት አላቸው፤ ደሀ ሰዎች ግን ትልቅ ቴሌቪዥንና ትንሽ ቤተመጽሐፍት አላቸው “ ይላል። ሀብታም ሰዎች የሚጠቅማቸውን ፤ ለዓላማቸው መሳካት የሚያግዛቸውን በንባብ ጥልቅ ምርምርና ጥበብ የሚያገኙበትን ቤተመጽሐፍ ገንብተው ዕውቀት ይገበያሉ። ለጠቅላላ መረጃ የሚሆኑ ሁነቶችን ለመመልከት እንዲት ኮሳሳ ቴሌቪዥን ካላቸው በቂ ነው። ዓላማቸውን፣ ሥራቸውን ፣ውሏቸውንና አመለካከታቸውን መቀየር፤ ወደ ሚመኙት ስኬት ለመድረስ እውቀትና ንባብን ያስቀድማል።
በሌላ በኩል ደሀዎች የሚታዩ ነገር ላይ ማተኮራቸው ርግጥ ነው። የዕለት ከዕለት ዜናዎችን ለመስማት፣ በክፍያ የሚታዩ የቴሌቪዥን ድራማዎችን፣ ፊልሞችን ለመመልከት ግድግዳውን የሚሞላ ቴሌቪዥን ይገዛሉ። ቤተመጽሐፍ እንኳን ቢገነቡ የተብራራ እና መዳረሻ ያለው ሕልም ስለሌላቸው የመጣ የሄደውን ቴሌቪዥን ቻናል በመቀያየር ተጠምደው መቼ ያነቡትና። በዓለም እንደምናስተውለው የሀብታም እሳቤ ያላቸው ሰዎች ለፋሽን እና ለውበት ብዙ ቦታ የላቸውም።ሥራቸውንና ዓላማቸውን ያስቀድማሉ።
ስቲቭ ሲቦልድ ሀብታም ሰዎች እንዴት ያስባሉ በሚል መጽሐፍ አሰናድቷል። በመጽሐፉ አንድ መቶ የሚጠጉ የሀብታም እሳቤዎችን በማንሳት በአንጻሩ የድሃዎችንም አመለካከት አሳይቷል። ደሃዎችን፣ መካከለኛ ሀብታምና ባለጸጋዎችን የሚለያያቸው ሐሳባቸው እንጂ ሌላ አይደለም በማለት አስፍሯል። ሦስቱም ደረጃዎች ላይ ያሉ ሰዎችን ወስደን ብንመለከት ልዩነቱ ሐሳባቸውና እሱን ተከትሎ በተፈጠረባቸው ስሜት ተገፍተው የደረሱበት ድርጊትና ውጤት ነው ይላል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሮበርት ኪዮሳኪ ድሃ እና ሀብታም አባት ስለ ገንዘብ አሠራርና መገኛ ያላቸውን የእሳቤ ልዩነት፤ ይህ ልዩነት ዛሬ ምድር ላይ ለተፈጠረው ደሃ እና ሀብታም ህዝብ ምክንያት መሆኑን ያነሳል በመጽሐፉ።
የእኔ ልጅ ሀብታም ባል ነው የምታገባው ብሎ ልጁን እንደ ማስያዣና ራሱ ኖሮበት ያላየውን በልጁ ዕድሜ ለመኖር የሚመኝን ድሃ አባትን አስቡት። በሌላ በኩል ደግሞ ልጄ ተምራ የግል ንግዷን ጀምራ፤ ኩባንያ ገንብታ ሀብታም ትሆናለች የሚልን ሰው አመለካከት ልብ በሉ።
ሀብታም አባት በተጓዘበት መንገድ ልጁን ይመራል። ደሃ አባት ደግሞ እሱ በወደቀበት መንገድ ልጁ ተሻግራ ያቋረጠውን መንገድ እንድትጓዝ ነው የሚያደርገው። ሮበርት ኪዮሳኪ እንደሚለው ሀብታም አባት፤ ደሀና ሀብታም መሆን በሥራ እና በትምህርት የሚገኝ ነው ይላል። ደሀውሳ? ቤተሰቦቼ ደሃ ናቸው፤ ከድሃ ተወልጄ ብሎ ያማርራል።
ሮበርት ሀብታም መሆንን ተማር፣ የገንዘብ አሠራር፤ አያያዝን ከስኬታማ ሰዎች ተማር። ቀጥለህ ትክክለኛ እምነትን ገንባና ሀብትን ከመጠበቅ ይልቅ በመፍጠር አግኘው ይላል።ወደ ስቲቭ ሲቦልድ ሐሳቦች ልመልሳችሁ። ሀብታም አባቶች ልጆቻቸውን ሀብትና ብልጽግና እንዴት እንደሚገኝ ያስተምሯቸዋል።
ደሀዎች ደግሞ እንደነ እገሌ፣ እነ እገሌን እያቸው፣ እንደነ እንትና ልጅ ነው መሆን፣ እነሱን አታያቸውም እያሉ መንጋውን ስለመከተል ያስተምሯቸዋል። የመጀመሪያው መገለጫቸው ገንዘብ በማስቀመጥ እና በማግኘት ይለያያሉ። ሀብታም ገንዘብ ስለ ማግኘት ያስባል፤ ደሀዎች ገንዘብ ስለማስቀመጥ ያስባሉ። አይሰሩበትም፤ ሀብታሞች ወስደው ይሠሩበታል። ተጨማሪ ገቢ ያገኙበታል። ቀጥሎ የምንመለከተው ገንዘብ የብልጽግና ምንጭ ነው የሚለውን የሀብታሞች ሀሳብ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ደሀዎች ገንዘብ የኃጢአት ሁሉ ስር ነው ብለው ያስባሉ።
ባደጉት እና ባላደጉት ሀገራት እንዲሁም ሰዎች መካከል ያለ አንድ ሐሳብ፤ ሀብታሞች ገንዘብን በአዕምሯቸው ስዕል ሰርተው ያስቀምጡትና ያንን ገንዘብ ለመዳሰስ፣ ከምዕናብነት ወደ ተጨባጭ ቁስነት ለመለወጥ በሚያስችላቸው የህይወት ቅኝትና መስመር ይራመዳሉ። ከፍታና ዝቅታውን አልፈው ዓላማቸውን አሳክተው ያንን ገንዘብ ያገኙታል። በድርጊት መስመር በጽናት ይመላለሳሉ። ደሀዎች ስለ ገንዘብ ማግኘት፣ ስለሚበሉት፣ ስለሚጠጡት እንደተጨነቁ ያልፋሉ።
የሚያሳዝነው ልጆቻቸውም ከዚያ የድህነት አዙሪት ለመውጣት ብዙ የሚቸገሩ መሆናቸው ነው። ለሀብታም የሀብት መንገድና ምንጩ ቀላል ነው። ጠንክሮ በጥበብ መስራት። ለደሀው ግን ገንዘብ ከሰው የሚሠጥ፣ በዕድል የሚወሰን፣ በደረጃ ዕድገት፣ በመዋቅር፣ በፖሊሲ መሻሻል፣ በስጦታ እና በሌሎችም የሚገኝ ውስብስብ ቁስ ነው። ባለጸጋዎች ገንዘብን በአዎንታዊ መልኩ ይመለከቱታል፣ ይፈልጉታል። ሊከፈለው የሚገባን ጊዜ፣ ጉልበት፣እውቀትና ትኩረት ይሠጡታል። ሲጠሩት ይመጣል። ደሀውሳ? ደሀውማ ገንዘብ’ኮ ምናባቱ፣ አፈር ይብላ፣ የጠንቋይ ፈረስ፣ ምናምን እያለ ያቀለዋል። እሱን ለማግኘት የሚገባውን ዋጋ አይከፍለውም። አይጠራውም። ቢጠራውም አይመጣም። በአሉታዊ መልኩ አይቶታልና። የሀብታሞች መንገድ በአንድ የተወሰነ ዘርፍ ላይ ባለ ዕውቀት ተመስርቶ የሚመጣ ነው። አሁን ዓለም አሉኝ የምትላቸው ባለጸጋዎች ዶክተሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ፕሮፌሰሮች ወይም ሌላ አይደሉም። እንዲያውም ከብዙ የትምህርት ተቋማት ሰነፍ ተማሪዎች የነበሩ፤ ነገር ግን ባላቸው የአንድ ዘርፍ እውቀት የፈጠራ ስራዎችን የሠሩ ናቸው። መደበኛ ትምህርት በሕይወት ለመኖር ይረዳል፣ ክህሎት ግን ባለጸጋ ያደርጋል። የክህሎት ስልጠናዎችን በቶሎ ወስደው አንዲት የፈጠራ ሐሳብን አዳብረው፤ ችግሮችን ወደ ዕድል ቀይረው ሐሳብ የፈጠሩ ናቸው።
ዛሬም በኢትዮጵያ ስማቸው የሚጠሩ ሀብታሞችን ብትመለከቷቸው ብዙዎች የዩኒቨርሲቲ ደጃፍ ያልረገጡ እዕምሯቸውን ለተለየ ዓላማና ስኬት ያዘጋጁ ናቸው። በሌላ በኩል ደሀዎች ትምህርት ቤት ገብተው ጠንክረው አንብበው፣ በውጤታቸው የሆነ ተቋም ተቀጥረው። ዶክተር፣ ፕሮፌሰር ተብለው 15 ሺህ ብር ተቀጥረው የቤት ኪራይ ሲቸገሩ፣ ልጆቻቸውን ማስተማር ዳገት ሲሆንባቸው እናያለን። ደሀዎች ሁልጊዜም የሀብታምነት መንገድ መደበኛ ትምህርት ነው ብለው ያስባሉ። ድሮ ያስጠኗቸው የነበሩ ሰነፍ ተማሪዎች በተሽከርካሪዎቻቸው መንገድ ይሸኟቸዋል።
ተጨማሪ ገንዘብ እንዴት ልገንባ እያለ ሀብታም ሁልጊዜ ያስባል። አንዱ ድርጅት ሁለት እንዲሆን 100 ስራተኛ 200 እንዲሆን ያስባል። ገንዘቤ አለቀች ምን ልበላ ነው? ደሞዝ ጭማሪ መቼ ነው? የደረጃ ዕድገት መቼ ነው? እያለ ደሀው ይጨነቃል።
ሀብታም ገንዘብን በሐሳብ፣ በዕቅድ፣ በዓላማ ነው ማሳካት የሚቻለው፤ ሁሉም ነገር ከሐሳብ ይጀምራል ብሎ ያምናል። ደሀው ግን ምን አጨናነቀኝ፣ ፈታ ልበል፣ ዓለም ዘጠኝ ናት ይልና አንዳች ጉልበቱን ብቻ ይጠቀማል። ሀብታም በሐሳቡ፤ ደሀ በጉልበቱ ልዩነትን ይፈጥራሉ። ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት፤ በሀብት ላይ ሀብት መገንባት ለሀብታም የበለጠ ነጻነትና ደስታ ይሠጠዋል። የጊዜ እና የኢኮኖሚ ነጻነትን እንዲሚያስገኝለት ያምናል። የበለጠ ገንዘብ መስራት ያልቻለ ደሀ ግን ሀብታሙ ሁሉ ጭንቀት እያሰቃየው ነው፤ ምን አለፋኝ ያው ድህነቴ ብሎ በድህነት ውስጥ ያለን ስቃይ ይመርጣል። ገንዘብንም የጭንቀት ምንጭ አድርጎ ይመለከታል። ሀብታሙ የአዕምሮ ሠላም ለማግኘት ይጠቀምበታል። ለሀብታም ትልቁ ሐሳቡና ትኩረቱ መዋለ ንዋይ ፈሰስ ማድረግ ነው፣ ደሀ ወጪውን ያስባል።
በኑሯችን እንደምናየው ሀብታሞች ለመዝናናት ያን ያህል ትኩረት የላቸውም። ገንዘባቸውን ሌላ ገንዘብ ለመሥራት ይጠቀሙበታል፣ ወደ ሥራ ቦታቸው ይጣደፋሉ። በየመዝናኛ ሥፍራውና መጠጥና ሥጋ ቤቱ የምናስተውለው ደሀውንና ገንዘብ ቢኖረውም እንኳን የደሀ እሳቤ ያለውን ሰው ነው። ደሀ ለመዝናናት፣ ጊዜን በአሉባልታ ለማሳለፍ የተጋለጠ ነው።
ሀብታሞች የሚወዱትን ሥራ ይሠራሉ፤ በድርጊትና ሥራ ያምናሉ፤ ገንዘባቸው ጓደኛቸው ነው፤ መርከባቸውን ራሳቸው ይሰራሉ። ደሀዎች የማይወዱትን ሥራ ይሠራሉ፤ በዕድልና ሎተሪ ያምናሉ፤ ገንዘብን እንደ ጠላት ይቆጥሩታል፤ መርከባቸውን ሰው እንዲሠራላቸው ይጠብቃሉ። ደሀዎች በትንሽ ሐሳብ ይጠመዳሉ፤ ጡረታ ሲወጡ ጥሩ ገንዘብ እንዲኖራቸው ያልማሉ፤ ሀብታሞች ሊረዱን ይገባል ይላሉ፤ ስ ለድሮው ዘመን መልካምነት ብዙ ያወራሉ፤ ገንዘብ ደስታን ይፈጥራል ይላሉ። ሀብታሞችሳ? ዘመናትን የሚሻገሩ ግዙፍ ሐሳቦች ላይ ናቸው፤ ዓለምን የሚቀይር ተግባርን ስለመከወን ያልማሉ፤ በራሳቸው ይተማመናሉ፣ ከማንም ርዳታን አይፈልጉም፤ ነገ ስለሚጀምሩት ተግባርና ተቋም ያስባሉ፤ ገንዘብ ደስታን ለመፍጠር ብቸኛው አማራጭ እንዳልሆነ ይገነዘባሉ።
ሮበርት ኪዮሳኪ እና ስቲቭ ሲቦልድ እንደሚሉት የሰው ልጅ የኢኮኖሚ ሁኔታና አኗኗር ከሐሳቡ የሚቀዳ ነው። ሐሳቡን የቀየረ ኢኮኖሚውን ይቀይራል። የሀብታምና የደሀ እሳቤዎች ሆድና ጀርባ፣ ጥቁርና ነጭ ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ለጊዜው የሚጠቀሙበት በቂ ገንዘብ ቢኖራቸውም እንኳን ሐሳባቸው የደሀ በመሆኑ ማደግና መለወጥ ሲችሉ ባሉበት ኖረው ያልፋሉ። የደሀ እሳቤ ሲባል ገንዘብን የምናይበት፣ የምንሠራበት፣ የምንጠቀምበት፣የምናወጣበትና የምናውልበትን አመለካከት ያጠቃልላል። ገንዘቡ ቢኖረንም አመለካከታችን ካልተለወጠ ደሀ በሚለው ምድብ ውስጥ እንቆያለን። በአንድ ወቅት ሥራዎችን ለመሥራት ወዲያ ወዲህ በማሰብ እባዝን ነበር። ሥራዎቼ በተፈለገው ፍጥነት ውጤት አላመጡም ነበር።አንድ ወዳጄ አንድ ቀን እንዲህ ሲል መከረኝ “አትሩጥ አንጋጥ፣በነገራችን ላይ መለወጥ በመፍጋት አይደለም” ሲል። ወደየት እንደማንጋጥጥ ግራ ገባኝና ረጅም ዝምታ ውስጥ ቆየሁ።” በነገርህ ላይ እኔ ሀብታም እንደምሆን በደንብ ይታወቀኛል፣ አንድ ቀን ዕድል ወደ አንተ ፊቷን ታዞራለች” ምክሩን ቀጠለ። ወዳጄ በመንግሥት ሥራ ነው፣ ልጆች ወልዶ፣ ቤት ሠርቶ፣ ሀብታም ሆኖ ለመኖር የሚመኘው። በቃ ዕድል ነው ተስፋው። የደሀ እሳቤ ማለት ይኼም አይደል? ዙሪያችን የደሀ እሳቤዎች ስለሞሉት ሀብታምም አንወድም እኮ። ምንድን ነው ማንጋጠጥ?
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here