አንታርክቲካ

0
71

ወደ ደቡባዊው የምድር ጫፍ በምናባዊ ሽርሽር ልውሰዳችሁ። እጅግ ቀዝቃዛማ ወደ ሆነው የዓለማችን ክፍል ስለምወስዳችሁ ለብርድ ተገቢ አለባበስ ልበሱ የበረዶ ጫማም ተጫሙ! እያልኩ ወደ አንታርክቲካ እናቅና።

አንታርክቲክ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኝ የምድራችን በጣም ቀዝቃዛውና ሩቁ ቦታ ነው። ይህ ክልል በግምት የደቡባዊን ንፍቀ ክበብ 20 በመቶ የሚሆነውን ቦታ ይሸፍናል። አንታርክቲካ በቆዳ ስፋት ረገድ በዓለም አምስተኛው ግዙፍ አህጉር ነው፤ 14.2 ሚሊዮን ስኩዌር ኪ.ሜ ይሸፍናል፤ ማለትም ከኦሺኒያ እና ከአውሮፓ ይበልጣል።

የአንታርክቲክ የበረዶ ንጣፍ በክልሉ ላይ ሰፊውን ስፍራ ይሸፍናል። ይህ በምድር ላይ ያለው ትልቁ ወጥ የሆነ የበረዶ ቁራጭ ነው። የበረዶው ወለል በበጋው መጨረሻ ላይ ከሶስት ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር ወደ 19 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር በክረምት ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ ያድጋል። የበረዶ መደርደሪያዎች ከአህጉሩ ጋር የተገናኙ ተንሳፋፊ የበረዶ ንጣፎች ናቸው።

አንታርክቲካ አህጉሩን ወደ ምስራቅ እና ምዕራብ ክልሎች የሚከፍሉትን የትራንስ አንታርክቲክ ተራራዎችን ጨምሮ በርካታ የተራራ ጫፎች አሉት።

ምንም አይነት በረዶ ባይኖር አንታርክቲካ እንደ አንድ ግዙፍ ገብ መሬትን እና የደሴቶች ስብስብን የያዘ ክልል (Lesser Antarctica) እና ከአውስትራሊያ የሚበልጥ አንድ ወጥ ትልቅ መሬት ያለው ክልል (Greater Antarctica) ሆኖ ይታይ ነበር። ማውንት ኤርባስ (Mount Erebus) በምድር ላይ በስተደቡብ ጫፍ የሚገኝ ንቁ እሳተ ገሞራ ነው። አንታርክቲካን የሚከቡት ውቅያኖሶች እጅግ ጥልቅ ሲሆኑ ጥልቀታቸውም ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺህ ሜትር ይደርሳሉ።

የአየር ንብረት

አንታርክቲካ እጅግ በጣም ቀዝቃዛ እና ደረቅ የአየር ንብረት አለው። በበረዶ ንጣፉ ውስጥ በሚገኙ ተራራማ አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ በክረምት ከ -60 ዲግሪ ሴልሺየስ በታች ሊወርድ ይችላል። በአንታርክቲካ እስካሁን የተመዘገበው ዝቅተኛው የሙቀት መጠን -89.4 ዲግሪ ሴልሺየስ ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 15 ዲግሪ ሴልሺየስ ነው።

አንታርክቲካ ሁለት ወቅቶች ብቻ አሉት-በጋ እና ክረምት። በበጋው ወቅት አህጉሩ ለስድስት ወራት የማያቋርጥ የፀሐይ ብርሃን ያገኛል። በክረምት ደግሞ ለስድስት ወራት አህጉሩ በጨለማ ይዋጣል። አይነጋም ማለት ነው።

አንታርክቲካ ሀገራት ወይም ቋሚ የሰው መኖሪያ የሌለበት ብቸኛ አህጉር ብቻ አይደለም። ተወላጅ የሚባል ሕዝብም የለውም። ለብዙ የአውሮፓ እና የሰሜን አሜሪካ ኃያላን ሀገሮች፣ አንታርክቲካ ለሰው ልጅ የምድር አሰሳ የመጨረሻውን ታላቅ ድንበር ይወክል ነበር። በብሔራዊ ኩራት የተሞላ እና በሳይንስ እና በሳይንስ እድገት የተደገፈ ነበር። ሁሉም ወደ ደቡብ ዋልታ በሚደረገው ውድድር ተወዳድረዋል።

በ1911 ኖርዌያዊው አምንድሰን እና እንግሊዛዊው ስኮት ወደ ደቡብ ዋልታ የሚደርሰው የመጀመሪያው ሰው የመሆን ዓላማ ይዘው ጉዞዎችን ጀመሩ። ሆኖም በመጨረሻ የአሙንድሰን ቡድን ታህሳስ 15 ላይ ወደ ደቡብ ዋልታ የደረሰ የመጀመሪያው ሆነ። ቡድኑ ጤናማ ነበር፤ እና ከአንታርክቲካ ጉዞውን በተሳካ ሁኔታ አድርጓል። የስኮት ቡድን እ.አ.አ ጥር 17፣ 1912 ደቡብ ዋልታ ደረሰ፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ በበረዶው ነፀብራቅ ዐይንን መታወር፣ በድካም እና በጉዳት ተሠቃይተዋል። ሁሉም ወደ ቤታቸው ሲጓዙ መሞታቸው በታሪክ ተዘግቧል።

ሕይወት በምርምር ጣቢያዎች

አንታርክቲካ በተለያዩ የምርምር ጣቢያዎች የተሞላ ስፍራ ነው። የማክሙርዶ ጣቢያ በኒውዚላንድ የሚተዳደረው በሮስ ደሴት ደቡባዊ ጫፍ ላይ የሚገኝ የአሜሪካ የምርምር ማዕከል ነው። ማክሙርዶ በአንታርክቲካ ውስጥ ትልቁ ጣቢያ ሲሆን 1ሺህ 250 ነዋሪዎችን ለመደገፍ የሚችል ነው። አብዛኛዎቹ እነዚህ ነዋሪዎች ሳይንቲስቶች አይደሉም፤ ነገር ግን የጣቢያ ስራዎችን፣ ግንባታን ፣ ጥገናን እና የዕለት ተዕለት ኑሮን ለመደገፍ ይሰራሉ። ማክሙርዶ ከ80 በላይ ሕንፃዎች ያሉት ሲሆን እንደ ትንሽ ከተማ ያገለግላል። በዓለም ደረጃ የላብራቶሪ እና የምርምር ተቋማት ያሉት ሲሆን የእሳት ማገዶ፣ የመኝታ ክፍሎች፣ መደብሮች እና የአህጉሩ ብቸኛ ኤቲኤምም ተሟልተውለታል።

የአርጀንቲና ትልቁ የአንታርክቲክ ተቋም የሆነው ቤዝ ኤስፐራንዛ በአንታርክቲክ ባሕረ ገብ መሬት ጫፍ ላይ በሆፕ የባህር ዳርቻ ላይ ይገኛል። ጣቢያው በአንታርክቲካ ውስጥ የተወለደው የመጀመሪያው ሰው የሆነው ኤሚሊዮ ማርኮስ ፓልማ የትውልድ ቦታ ነው። ቤዝ ኤስፐራንዛ በአህጉሩ የተገነባውን የመጀመሪያውን የካቶሊክ ጸሎት ቤት (1976) እና የመጀመሪያ ትምህርት ቤት (1978) ይይዛል። እ.ኤ.አ. በ1979 ቤዝ ኤስፐራንዛ የምርምር ጣቢያውን ከአርጀንቲና አህጉራዊ ግዛት ጋር በማገናኘት የአህጉሩ የመጀመሪያ የአጭር ሞገድ የሬዲዮ ስርጭት ሆኗል።

የዴቪስ ጣቢያ በአውስትራሊያ ውስጥ በጣም ሥራ የበዛበት ሳይንሳዊ የምርምር ጣቢያ ነው። ቬስትፎልድ ሂልስ በመባል በሚታወቀው በረዶ በሌለበት አካባቢ ይገኛል። ልክ እንደሌሎች የአንታርክቲካ የምርምር ጣቢያዎች፣ በዴቪስ ጣቢያ ምግብ በጣም አስፈላጊ ነው። ሆኖም የምግብ አቅርቦቶች በጣም የተገደቡ ናቸው። በዴቪስ ጣቢያ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የምግብ አቅርቦት በዓመት በአንድ ሰው ተመን ለሁሉም ይከፋፈላል። ነዋሪዎች በአብዛኛው በቀዘቀዘ እና በታሸገ ምግብ ይኖራሉ።

በእነዚህ ጣቢያዎች የተለያዩ ሀገራት ተመራማሪዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ይኖራሉ። ሳይንቲስቶች በመንግሥት በሚደገፉት በእነዚህ የምርምር ጣቢያዎች ውስጥ የሚሰሩ እና ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ናቸው። ምርምር የሚያደርጉ የሳይንስ ሊቃውንት ቁጥር ዓመቱን ሙሉ ይለያያል፤ በክረምት እስከ 1ሺህ በበጋ እስከ 5ሺህ አካባቢ ይሆናል።

ከተለያዩ ሳይንሳዊ ዘርፎች የተውጣጡ ተመራማሪዎች አንታርክቲካን እንደ ልዩ አካባቢነቱ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ሰፋ ላሉ ዓለም አቀፍ ሂደቶች ማመላከቻ በማድረግ ያጠናሉ። የጂኦግራፊ ባለሙያዎች በጣም ቀዝቃዛውን እና በጣም የተገለለውን የዓለማችንን አህጉር ገጽታ ካርታ ያነሳሉ። የሜትሮሎጂ ባለሙያዎች በአንታርክቲካ ላይ የሚያንዣብበውን “የኦዞን ሽንቁር” ጨምሮ የአየር ንብረት ቅጦችን (patterns) ያጠናሉ። የአየር ንብረት ተመራማሪዎች የምድርን የአየር ንብረት ታሪክ የሚከታተሉት በአንታርክቲካ ላይ ነው። የባህር ባዮሎጂስቶች የዓሣ ነባሪዎችን፣ የባህር አንበሶችን(seals) እና የስኩዊድን ባህሪ ያጠናሉ። የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ከአንታርክቲካ ውስጠኛ ክፍል ምልከታ ያደርጋሉ፣ ምክንያቱም ከምድር የቦታውን ግልጽ እይታ ስለሚሰጥ።

በአንታርክቲካ አህጉር ውስጥ አንድም ዛፍ ወይም የቁጥቋጦ ዘር አያገኙም። ይሁን እንጂ ሊቸንስ፣ ሞሰስ እና የየብስ አልጌ በአንታርክቲካ ውስጥ ከሚበቅሉት ጥቂት የእፅዋት ዝርያዎች መካከል ናቸው። ተክሎቹ በሰሜናዊ እና በባህር ዳርቻማ የአንታርክቲካ ክልሎች ይበቅላል፣ ውስጠኛው የአህጉሩ ክፍል ግን ምንም አይነት እፅዋት የለውም።

በሌላ በኩል በአንታርክቲካ የተለያዩ እንስሳት ዝርያዎች አሉ። ከ9 ሺህ በላይ የታወቁ የእንስሳት ዝርያዎች ይገኛሉ፣ ይህም 46 የአእዋፍ እና አስር የውሃ ውስጥ የአሳ ዝርያዎችን፣  ስድስት አሳ በሊታ የባህር እንስሳትን እና የአንታርክቲክ ፔንጉዊን ዝርያዎችን ያካትታል። ዓሳ እና ብዙ አይነት የባህር አጥቢ እንስሳትም በቀዝቃዛው የአንታርክቲክ ውሃ ክፍል ውስጥ ይኖራሉ።

የአንታርክቲካ አስፈላጊነት

የአንታርክቲካ ክልል በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሂደቶች ውስጥ ትልቅ ሚና አለው። አንታርክቲካ የምድርን የሙቀት ሚዛን በመጠበቅ ረገድ ከአብዛኞቹ አህጉራት የበለጠ ሚና አለው። በረዶ ከመሬት ወይም ከውሃ ወለል የበለጠ አንጸባራቂ ነው። በመሆኑም ግዙፍ የአንታርክቲካ የበረዶ ንጣፍ ከፍተኛ መጠን ያለው የፀሐይ ጨረር አንፀባርቆ ይመልሳል።

በአንታርክቲካ ዙሪያ ያሉ ውቅያኖሶች  የምድር ውሃ ሚዛናዊ እና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ እንዲዘዋወር ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።

አንታርክቲካ የራሱ የሆነ ስምምነት አለው

ሰዎች በ1820 አንታርክቲካን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩ የአገሬው ተወላጆች ያልነበሩበት ብቸኛው አህጉር ነበር። በመሆኑም በርካታ ሀገሮች በፍጥነት ለአህጉሩ የይገባኛል ጥያቄ አቅርበዋል፤ ይህም ከፍተኛ ውጥረት አስከትሏል። አንዳንድ ሀገሮች አንታርክቲካ የራሳችን ነው ብለው ሲከራከሩ ሌሎቹ ግን ከልባቸው አልተስማሙም።

ውጥረቱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ሁሉም ሰላማዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ተስማምተዋል። በታህሳስ 1952 ዓ.ም አስራ ሁለት ሀገሮች የአንታርክቲክ ስምምነትን ፈርመዋል። ይህም አህጉሩን ሰላምና ሳይንስን አንድ ላይ ለማስተዳደር የሚያስችል ታይቶ የማይታወቅ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው።

በውሉ ውስጥ ክልሉ በፖለቲካዊ መልኩ ገለልተኛ ሆኖ እንዲቆይ፣ ምንም ዓይነት ሀገር የአንታርክቲካን ክፍል የግዛቱ አካል አድርጎ መያዝ እንደማይችል፣ ክልሉ ለወታደራዊ ዓላማ ወይም ለራዲዮአክቲቭ ቆሻሻ ማስወገጃነት ማገልገል እንደሌለበት እና በክልሉ የሚደረግ ማንኛውም ምርምር ለሰላማዊ ዓላማዎች ብቻ መከናወን እንዳለበት የሚያስገነዝቡ ሀሳቦች ተደንግገውበታል። በአሁኑ ወቅትም 47 ሀገራት ውሉን ፈርመዋል።

ዛሬ የአንታርክቲክ ስምምነት ስርዓት ለንግድ ዓሣ ማጥመድ፣ ለማሸግ እና የማዕድን ፍለጋን ሙሉ በሙሉ ለማገድ ጥብቅ መመሪያዎችን በማካተት ተስፋፍቷል።

መጪው ዘመን

የአንታርክቲካ አህጉር መጪው እጣ ፋንታ ስጋት አለበት። የአየር ንብረት ለውጥ እና ቱሪዝም የአንታርክቲካ ዋነኛ ስጋቶች ናቸው። በ2010 ዓ.ም. 40,000 ያህል ጎብኚዎች ወደ ክልሉ መጥተዋል። ሳይንቲስቶች እና ፖሊሲ አውጪዎች ይህንን ስስ አካባቢ ለመጠበቅ እና የተፈጥሮ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም በትኩረት እየሰሩ ነው።

አጭር እውነታ

  • አንታርክቲካ በምድር ላይ ከፍተኛው፣ ደረቅ፣ ቀዝቃዛ እና ነፋሻማ አህጉር ነው
  • አንታርክቲካ 14.2 ሚሊዮን ስኩዌር ኪ.ሜ (5.5 ሚሊዮን ስኩዌር ማይል) ይሸፍናል
  • የአንታርክቲክ የበረዶ ንጣፍ በምድር ላይ ትልቁ የበረዶ መደብር ነው
  • የመሬት ስፋቱ 14 ሚሊዮን ኪ.ሜ (5.4 ሚሊዮን ስኩዌር ማይል) ይሸፍናል
  • ክብደቱ 30 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር (7.2 ሚሊዮን ኪዩቢክ ማይል) ነው
  • አማካይ ጥልቀቱ 2,160 ሜትር (7,000 ጫማ) ሲሆን ከፍተኛው ጥልቀት 4,776 ሜትር (15,669 ጫማ) ነው።
  • በረዶ 98% የሚሆነውን የአንታርክቲካ ክፍል ይሸፍናል፤ ይህም 90% የሚሆነውን የምድር በረዶ እና 70% የሚሆነውን የንፁህ ውሃችንን ይሸፍናል።

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here