“አንዳንዱ የመስጠት ሌላው ደግሞ የመንጠቅ ልክፍት አለበት”

0
182

ገጣሚ ዬሐንስ ሞላ ከአሚኮ ጋር ያደረገውን ቆይታ በክፍል አንድ አስቃኝተናቸኋል፤ በክፍል አንድ ስለ ግጥም ያለውን አመለካከት፣ ለየት ያሉ ፍልስፍናዎቹ፣ ስለ ምስጋና ወዳድነቱ እና ሌሎች ነጥቦች አጫውቶናል፡፡ በዚህ የመጨረሻ ክፍል ደግሞ ግጥም የጀመረበትን አጋጣሚ፣ ስለወላጅ እናቱ እና ሌሎች ተጨማሪ የግጥም ፍልስፍናዎቹ ነግሮናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

የሦስቱ መጽሐፎችህ ምርቃት ላይ እናትህ የክብር እንግዳ  ነበሩ፤ ማን ናቸው እኝህ ብርቱ ሰው? አስተዋውቀን?

እናቴ ወይዘሮ ልጃለም ጤና ትባላለች፤ እኔ የመጨረሻ ልጅ ነኝ ከእኔ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ልጆቿ ጋር ቅርብ ትስስር አላት፡፡ ታሪክ መንገር ታውቅበታለች፡፡ ሬዲዮ በጣም ታዳምጣለች፡፡ ታሪክ በደንብ ታውቃለች፤ ታሪክ ሲነበብላትም ትወዳለች፡፡  በኑሮዋችን ብዙ ውጣ ወረድ ነበረ፤ ብዙ ለፍታ አሳድጋናለች፡፡ ለእሷ ትልቅ ቦታ አለኝ፡፡

በሦስቱም መጸሐፎቼ ምርቃት ላይ እንግዳ እሷ ነበረች፡፡ የእናት መልክ የሚል ግጥምም ለመታሰቢያነቷ ተቀኝቼላታለሁ፡፡

ከግጥሙ የተወሰነ አንብብልን?

ከችጋር ጋር ታግሎ የረታ ቁንጅና፣

ከማጣት ተጋፍቶ በጉልበት የጠና፣

በእምነት የደደረ በተስፋ  የቀና፣

በብርታት የቆመ ያልዛለ ቁመና፤

በብልሀት ተስሎ በዕውቀት የታተመ፣

በስስት ተነድፎ በፍቅር የቀለመ፤

በዓላማ ተከቦ ሰንደቁን ናፋቂ፣

ሰርክ አንጸባራቂ፣

እንባ አደራራቂ፣

ክፉውን አራቂ፣

ታምሩን ፈልቃቂ፤

በቸርነት ታጥሮ ይኖራል ሲያበራ፣

መሽሞንሞን ያላየው የደራ የኮራ፤

የእናት መልክ…

ግጥም ወደ መግጠም እንዴት ገባህ፤ ፍቅርስ ያሳደረብ አጋጣሚ ምንድን ነው?

ልጅ እያለሁ መጻፍ እና መጫር እወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ሙያ ነው ችሎታ ነው የሚል ነገር ውስጤ አልነበረም፡፡ አራተኛ ክፍል እያለሁ የዓለም የኤድስ ቀን መታሰቢያ ሲደረግ የግጥም ውድድር ነበረ፡፡ የክፍል ስም ጠሪየ እና የአማርኛ ቋንቋ መምህሬ  እንድወዳደር ሀሳብ አቀረበችልኝ፡፡ ቀደም ሲል ትኩረቷን ስቤያለሁ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ከዚያ በፊት ለአስተማሪየ አይን የሚሞላ ግጥም ጽፌያለሁ ማለት ነው፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ላይ የስነ ግጥም ጽንሰ ሀሳብን ስንማር የጠቀመኝ ነገር አለ፡፡ እሱ እንግዲህ ለጅማሮየ ረድቶኛል፡፡ በውድድሩ አሸነፍኩ፡፡

ከዚያ በኋላ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ የግጥም ውድድሮች ሲኖሩ እሳተፍ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ሰገል ፕሮሞሽን የሚባል ድርጅት ባዘጋጀው ውድድር ላይ ተሳተፍኩ፡፡ አንደኛ ወጣሁ፡፡ ከዛም በኋላ የተለያዩ ውድድሮች አሸንፌያለሁ፡፡ የማሸንፈው ሌላ ተወዳዳሪ ስለሌለ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ወንድሞቼ ግጥም ይሞክሩ ነበር፤ እናም ሁሉም ሰው ግጥም መጻፍ የሚችል ነበር የሚመስለኝ፡፡ የሆነ ቦታ ተወዳድሬ ሳሸንፍም እኔ ብቻ ተወዳዳሪ ወይም አመልካች ስለሆንኩ የተመረጥኩ ይመስለኝ ነበር፡፡

በኋላ ዩኒቨርሲቲ ስገባ መቅርዝ የኪነ ጥበባት አፍቃሪያን ህብረት የሚባል ደስ የሚል ማኅበር ውስጥ ገባሁ፡፡ እኔን የሚመስሉኝን ሰዎች አገኘሁ፡፡ እዛም ስገባ ሰው ተከፋፍሎ የተለያየ ክለብ ነበር፡፡ በመጀመሪያ አባላቱ ፈልገው ማኅበሩን የተቀላቀሉ አይመስለኝም ነበር፡፡ የመጡበትን ዓላማ አሳክተው ወደየ መጡበት ይመለሳሉ የሚል እምነት እንጂ ለኪነ ጥበብ ፍቅር አላቸው ብየ አላሳብኩም ነበር፤ የሆነው ግን ከአሰብኩት ተቃራኒው ነው፡፡

በጣም የቅርብ ጓደኛዬ በግጥሞቼ ያደንቀኝ ነበር፤ በእሱ የተነሳ ደግሞ ቤተሰቦቹ አድናቂዎቼ ሆኑ፡፡ በተለይ ጓደኛዬ አድንቆቱ የበዛ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ አድናቆት መቋቋም አቃተኝ እና አንድ ቀን ራስህ ለምን አትጽፍም አልኩት(ሳቅ)፡፡ የሚመስለኝ የነበረው ልጻፍ ቢል ይጽፋል ነው፡፡ ራሴን ዝቅ ለማድረግ ወይም አጉል ትህትና ሳይሆን የእውነት ሁሉም ሰው የሚችለው ግን የፈልገው ብቻ የሚያደርገው ነበር የሚመስለኝ፡፡ ምክንያቱም ይሄ ነገር ወደፊት ያስኬደኛል፤ ውጤታማ ልሆን እችላለሁ ብየ ከግጥም ዓለም ለመውጣት ያመነታሁባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ወንድሞቼም ግጥምን ሲተው አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው እንደዛ ይመስለኝ ነበር፤ የፈለገ ይቀጥላል ያልፈለገ ይተዋል፡፡

ያንተ የግጥም አጻጻፍ ወደ የትኞቹ ገጣሚዎች ያደላል፤ ወይስ የራስህ አጸጻፍ ዓይነት (ስታይል) አለህ?

የራሴ ስታይል አለኝ ማለት አልችልም፡፡ ምክንያቱም ስንሰማ ስናነብ ያደግናቸው ነገሮች ናቸው ተጽዕኖ የሚፈጥሩብን፡፡ እየቀረጹን የሚሄዱትም እነሱ ናቸው፡፡ ግጥም ልጻፍ ብየ ስነሳ ከሆነ ዜማ እና መልክ መውጣት አልችልም፡፡ ወጣሁ እንኳ ብየ ባስብ ተመልሼ እዛው ነው የምገኘው፡፡ እንደነ እከሌ ልምሰል ብየ አግን አላውቅም፡፡ በልጅነትም ሆነ አሁን ልምሰል ብየ አላውቅም፤ አልሞከርኩም ወደፊትም አልሞክርም፡፡ በእርግጠኝነት ግን የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ሁሉም አይነት አጻጻፎች ሊቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ የራሴን ግን መንገድ መፍጠር አልችልም፡፡

የገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ የሎሬት ጸጋየ ገብረመድህን፣ ደበበ ሰይፉ፣ በዕውቀቱ ስዩም፣ ሰለሞን ሳህሌ፣ ትግስት አለም ነህ፣ አበባ የሺጥላ እና ሌሎችን ግጥሞች ሳነብ ነው ያደኩት፡፡ ከእነሱ አጻጻፍ አልወጣም፡፡

ብርሃን ጋር ያለህ ቁርኝት ከፍተኛ ነው፤ ለምሳሌ የብርሃን ልክፍት እና የብርሃን ሰበዞች በርዕስነት ወስደሃቸዋል፤ ለብርሃን ምን የተለየ ትርጉም አለህ?

ብርሃን ያው ብርሃን ነው፡፡ የብርሃን ሰበዞች ግጥም ሳይሆን የመጽሀፌ ርዕስ ነው፤ የፊት ገጽ ስዕሉን የሠራው ጓደኛየ ነው፤ ሀሳቡ የእኔ ነው፡፡ የፊት ገጹን ሰው እያየ እንደ ግጥም የራሱን ትርጉም እና እይታ እንዲወስድ ፈልጌ ያደረኩት ነው፡፡ ሰበዞቹ በክር ሲሰፉ የሚሸፈነውን ብርሃን ለማሳየት ነው የፈለኩት፡፡ የብርሃን ሰበዞቹ ውስጥ ገቡ፤ ተሸፈኑ፤ በላይ ቢሆኑ ሰፌዱ ምንኛ ያምር ነበር ነው እኔ የሰጠሁት አንድምታ፡፡

የብርሃን ልክፍት መስጠት እና መቀበልን የሚዳስስ ነው፡፡ አንዳንዱ የመስጠት ልክፍት ሌላው ደግሞ መቀበል መንጠቅ ልክፍት አለበት፡፡ አንዳንዱ ይቃጠላል ሌላው ደግሞ እሳት ይጭራል፡፡ እነሱን ነው በብርሃን የገለጽኳቸው፡፡ ወደፊት ሁለቱ ርዕሶች በግጥም ሆነው ይመጡ ይሆናል፡፡ ለጊዜው ሽፋን ስዕላቸው ከግጥሞቹ በላይ መልዕክት ያስተላልፋሉ ብየ ስላመንኩ አላካተትኳቸውም፡፡

በከንፈርሽ በራፍ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ?

የተለየ ነገር ላያመጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን የተለየ ቅርጽ ይዤ ለመምጣት ሞክሬያለሁ፡፡ የግጥሞቼን ሀሳብ እና ትርጉም  ሳይሆን ቅርጻቸውን ነው ለማስረዳት የሞከርኩት፡፡ ቅርጻቸውን ለማስረዳት የሞከርኩት ከዚህ በፊት ተጽፎባቸው ስለማያያውቅ ነው፡፡ ተጽፎባቸው አላየሁም፤ እንግዲያ ያላየሁት ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ሌላ ያጣቀስኩት ጽሑፍ የለም፡፡ እንደሚገባኝ አዲስ ቅርጽ እየሞከርኩ ስለሆነ እግረ መንገዱን ሌሎች ሰዎች ከወደዱት እና ካመኑበት እንዲከተሉት፣ ዝም ብሎ በአጋጣሚ እንዳልሆነ አንዲታወቅ ነው ማስገንዘቢያውን ያሰፈርኩት፡፡

የግጥሜን ቅርጽ ሳስረዳ ክብነት አለው የምለው ስንኞቹ ተደርድረው ሲያልቁ መዝጊያው ከርዕሱ ስለሚገጥም ነው፡፡ በሀሳብ ቤት ይመታል፤ በቃል ቤት ይመታል፡፡ ያ ማለት ከላይ የተነሳው ሀሳብ ከታችኛው ጋር ይጋጠማል፤ ክብ ቅርጽም እንደዚሁ ነው፡፡ ይህ አዲስ ነገር ነው ብየ አስባለሁ፡፡

በመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ግጥም አለ፡፡ ግጥሙ የዘፈን ነው፡፡ ዘፈኑ ደግሞ የግጥሙ ማጀቢያ ነው፡፡ ሙዚቃው በከንፈርሽ በራፍ የሚል ነው፡፡ ራስ ብሩክ ጸሐይ ነው የተጫወተው፡፡ ኪ ዋር ኮድ በተሰኘ ቴክኖሎጂ የተሠራ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የወጣው መጽሐፌ ሙዚቃ ነበረው ቴክኖሎጂው ግን እንዳሁኑ አልተራቀቀም እና ማዳመጥ አልተቻለም ነበር፡፡ አሁን ስካን አድርጎ ማዳመጥ ይቻላል፡፡

ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን

እኔም አመሰግናለሁ

(ቢኒያም መስፍ)

በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here