የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ቡደን በተከታታይ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በማንሳት በሀገራችን የሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው ቡድን ሆኗል።
ከተመሠረተ 14 ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን የሊጉን ዋንጫ ለስምንተኛ ጊዜ ማሳካት ችሏል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ፕሪምየር ሊጉን የትኛውንም ቡድን ጣልቃ ሳያስገባ በተከታታይ አምስት አመታት የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘንድሮው የውድድር ዓመት አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ነው ዋንጫውን ያነሳው። ባለፉት 51 ጨዋታዎች ባለመሸነፍ ዋንጫ ያነሳ በኢትዮጵያ እግር ኴስ ታሪክ በወንዶችም በሴቶችም የመጀመሪያ ክለብ ነው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰቶች ቡድን በቀጣይ የሴካፋ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ ሀገራችንን በመወከል ተሳታፊ ይሆናሉ። ቡድኑ ዘንድሮ በሁሉም የሜዳ ክፍል ምርጥ አቋም በማሳየት ነው የውድድር ዓመቱን የጨረሱት።
በተለይ ደግሞ የኋላ ክፍሉ እና የፊት መስመሩ አስደናቂ የውድድር ጊዜ አሳልፏል። የፊት መስመሩ ከየትኛውም የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ክለብ በላይ ብዙ ግቦችን አስቆጥሯል፤ ከ60 በላይ ግቦችን ማስቆጠሩን ቁጥሮች ይናገራሉ። የኋላ ክፍሉም በቀላሉ የማይረበሽ እና ጠንካራ ሲሆን አነስተኛ ግቦች ናቸው የተቆጠሩበት፤ በአጠቃላይም 12 ግቦች ተቆጥረውበታል።
ባለፉት ዓመታት በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበረው ሀዋሳ ዘንድሮም እስከ መጨረሻው ከንግድ ባንክ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ዐመቱን ጨረሷል። ሀዋሳ ከተማ ሁለተኛ ሆኖ ዓመቱን ሲያጠናቅቅ ሲዳማ ቡና ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል።
በዚህ ውድድር ዘንድሮ የሀምበሪቾን ያህል ደካማ የውድድር ጊዜ ያሳለፈ ክለብ የለም፤ ክለቡ በውድድር ዓመቱ አንድም ጨዋታ ሳያሸንፍ ዓመቱን አጠናቋል። ከየትኛውም ክለብ የበለጠ ብዙ ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን ከሌሎች ያነሰ ግብ ደግሞ በተጋጣሚ መረብ ላይ አሳርፏል። ሴናፍ ዋቁማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስፖርት ማህበር ለእግር ኳሱ እያደረጉ ያሉት ያልተቋረጠ ድጋፍ እና ክትትል ክለቡን ለውጤት አብቅቶታል። ከአሚኮ በኵር የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ክለቡ የሀገር ውስጥ አንበሳ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃም ትልቅ ስም ያለው ክለብ ለማድረግ ትልቅ ድጋፍ ተደርጎልናል፤ እየተደረገልን ነውም ብሏል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ምንም እንኳ ሰፊ እና ጥልቅ የተጫዋቾች ስብስብ ቢይዝም የውድድር ዓመቱ ሲጀምር ግን በርካታ ተጫዋቾችን በጉዳት አጥቶ ነበር የጀመረው። ነገር ግን ጠንካራ የአሸናፊነት ስነ ልቦና መያዙ እና ወጥ አቋም በማሳየቱ ዘንድሮም ሻምፒዮን እንዲሆን አስችሎታል ነው ያሉት አሰልጣኙ።
በዘንድሮው ውድድር ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጠንካራ ተፎካካሪ እንደነበሩ የተናገሩት አሰልጣኝ ብርሃኑ ፕሪሚየር ሊጉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና እየተሻሻለ እንደሆነ ተናግሯል። ” በታዳጊ ውድድሮች ቢታጀብ ደግሞ ይበልጥ የተሻለ እና ጠንካራ ውድድር ይሆናል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የቅርብ ጊዜ ውድድር ነው። ገና 14 ዓመታት ዕድሜን ብቻ ነው ያስቆጠረው። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ማራኪ እና ጥሩ ፉክክር የሚታይበት ሊግ ሆኗል። ምንም እንኳ ክለቦች የንግድ ባንክን ኃያልነት መግታት ቢሳናቸውም እስከ መጨረሻው ሳምንት መርሀግብር ድረስ የሚያደርጉት ተጋድሎ ሊጉ እንዲወደድ እና ድባቡ ደመቅ እንዲል አስችሎታል። የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ታዳጊዎች ዕድል የሚያገኙበት እና የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችም የሚወጡበት ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን ሊጉ በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው። ይህንንም አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች በተዳጋጋሚ ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በሴካፋ ዞን የምስራቅ አፍሪካ የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ ለ5ኛ ተከታታይ ጊዜ የሚሳተፍ ይሆናል። ታዲያ ቡድኑ በቅርቡ ለካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድር ቅድመ ዝግጅት ይጀምራል። ለዚህ ውድድር የሚረዱ በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ተጫዋቾችን ለማስፈረምም እቅድ እንዳላቸው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ገልጿል፡፡
በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በተደጋጋሚ ዋንጫ በማንሳት እና በአፍሪካ መድረክ በመሳተፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብ ቀዳሚው ክለብ ነው፡፡ አምና በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሻምፒዮን በመሆን በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉ አይዘነጋም። ታዲያ ዘንድሮም በአፍሪካ መድረክም ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንሠራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ክለብ በየእድሜ እርከኑ ለብሄራዊ ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾችን የሚያስመርጥ ክለብ ነው:: ባለፉት 14 ዓመታትም ለሀገራችን እግር ኳስ ትልቅ አስተዋጽኦ ካደረጉ እና እያደረጉ ከሚገኙ ክለቦች መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣል፡፡
(ስለሺ ተሸመ)
በኲር የግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም