“አንድ ሀገር የሚሠለጥነው የራሱን ሀገር በቀል ዕውቀት በማደስ መሻሻል ሲያሳይ  ነው”

0
163

     የተወለዱት በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን እነብሴ ሳር ምድር ወረዳ መርጡ ለማርያም ከተማ ነው:: የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመርጡ ለማርያም ከተማ ተከታትለዋል:: የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ ተመርቀዋል:: የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተመሳሳይ የሙያ መስክ ሠርተዋል:: የሶስተኛ ዲግሪያቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሥነ ጽሑፍ ተመርቀዋል፤ የዚህ እትም እንግዳችን ዶክተር ዳዊት ዲበኩሉ:: አሁን ላይ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሂማኒቲስ ፋኩልቲ ውስጥ በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ:: ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ምርምር ሥራዎችን ለህትመት አብቅተዋል:: በአሁኑ ሰዓት የግእዝ ትምህርትን በሶስተኛ ዲግሪ ለማስጀመር ሥርዓተ-ትምህርቱን በዋናነት በመምራት ከቀረፁት ውስጥ አንዱ ናቸው:: ስላለፉበት የሕይዎት ጎዳና፣ ስለ ግእዝ ቋንቋ ትምህርት እና ተዛማጅ ጉዳዮች አነጋግረናቸዋል::

መልካም ንባብ!

የግእዝ ትምህርትን በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ማስተማር የተጀመረው መቼ ነው?

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት በማድረግ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን በመቀበል በመደበኛ መርሐ ግብር እያስተማረ ይገኛል:: በመጭው የ2018  የትምህርት ዘመን ደግሞ በሶስተኛ ዲግሪ የግእዝ ጥናትን ለመጀመር ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጿል::

የግእዝን ትምህርት መርሃ ግብር በሶስተኛ ዲግሪ መክፈት ያስፈለገበት ምክንያት ምንድነው?

አሁን ላይ ግእዝን ማስተማር ያስፈለገበት ዋናው ምክንት እንደ ሀገር ተሐድሶ ስለሚያስፈልግ ነው:: የአስኳላ ትምህርት የተመሠረተበት ንድፈ ሐሳብ የአውሮፓውያንን አመለካከት እና ማኅበራዊ ስርዓት ተቀዳሚ አውሮፓዊ ያልኾኑ ባህሎችን እና አሠራሮችን ኋላ ቀር በማድረግ ላይ ነው:: አንድ ሀገር የሚሠለጥነውና የሚበለጽገው ሌላውን ተከትሎ ማንነቱን ሲያጣ ሳይኾን የራሱን ሀገር በቀል ዕውቀት በማደስ መሻሻል ሲያሳይ  ነው:: ለምሳሌ በአክሱም ሥርወ መንግሥት የግእዝ ቋንቋ የንግግርም የሥነ ጽሑፍም ቋንቋ ነበር:: እስከ ፲ኛዉ ክፍለ ዘመን የመግባቢያ እና የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ እንደነበር የሚታወቅ ሲኾን ከ፲ኛዉ ክፍለ ዘመን በኋላ የመግባቢያ ቋንቋ መኾኑ ቀርቶ እስከ ፲፱ኛዉ ክፍለ ዘመን የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ በመኾን አገልግሏል::

ግእዝ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሁንም የዕውቀት ማእከል በመኾን ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች እየተተነተኑበት ይገኛል:: ስለሆነም በቋንቋዉ የተፃፉ ዕውቀቶችን  በመመርመር ዛሬ ላይ ልንጠቀምባቸው ግድ ይላል::

ሥርዓተ ትምህርቱን የመቅረጽ ሃሳቡ እንዴት ተነሳ?

ከመጀመሪያው ጀምሮ የግእዝን ትምህርት ክፍል በባሕር  ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት እና አሁንም በሶስተኛ ዲግሪ ለማስጀመር በሚደረገው ሂደት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱት ከእኔ ይልቅ ሌሎች የትምህርት ክፍሉ አባላት ናቸው:: አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው ይህንን ጥንታዊ ቋንቋ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው:: በዓለም ላይ የግእዝ ቋንቋን በትምህርትነት ብዙ የአውሮፓ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ይሰጡታል:: ይህን የሚያደርጉት ቋንቋውን ለማሳደግ አስበው ሳይሆን በውስጡ ያለውን እምቅ ዕውቀት አውጥተው ለመጠቀም ነው:: እኛ ግን የቋንቋዉ ባለቤቶች ሆነን ከቋንቋዉ መጠቀም ባለብን ልክ መጠቀም አልቻልንም:: ይህን ክስተት “የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው” እንደማለት ነው የምቆጥረው:: እንደ መነሻ የሆነው ዋነኛው ምክንያትም ሌሎች ሀገራት የኛ የሆነዉን ዕውቀት ወስደው ለችግሮቻቸው መፍቻ ሲያደርጉት እኛ ግን መጠቀም ባለመቻላችን የተፈጠረ ቁጭት ነው::

ሥርዓተ ትምህርቱን ለመቅረጽ በመጀመሪያ የተሠራው ሥራ ምንድን ነው?

በመጀመሪያ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተዘዋዉረን የዳሰሳ ጥናት አድርገናል:: በመቀጠልም በዘርፉ ልምድ ካላቸዉ ባለሙያዎች እንዲሁም ተቋሞች ጋር በተከታታይ ተወያይተናል:: በተጨማሪም ቃለ መጠይቆችን አዘጋጅተን መረጃዎችን ሰብስበናል:: በመጨረሻም የፕሮግራሙን (መርሃ ግብሩን) አስፈላጊነት ስንረዳ ወደ ሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ገብተናል::

ሥርዓተ ትምህርቱ በሌሎች ሀገራት ይሰጣል፤ የተወሰደ ተሞክሮስ አለ?

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጥንታዊ መጽሐፍት በተለያየ ጊዜ ከሀገር ተሰርቀው ወጥተዋል:: የግእዝ ትምህርትም ባውሮፓ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል::  ለምሳሌ የጀርመንን ብንወስድ “Ethiopian and Eritrean studies” ብለው ነው እየሰጡት ያለዉ፤ የግእዝ ትምህርትን:: ሌሎች ሀገራት ደግሞ “Classical Studies” ብለው ይሰጡታል:: ይህን ሲያደርጉ ቋንቋዉ ላይ ትኩረት አያደርጉም:: እኛ ግን ሥርዓተ ትምህርቱን ስንቀርፅ ትኩረቱ እንዲሆን ያደረግነው ሥነ ቋንቋን ማጥናት ላይ ነው:: በዋናነት ተማሪዎች ሥነ ቋንቋዉን እንዲመረምሩ፣ በቋንቋዉ የተጻፉ መዛግብትን እንዲያጠኑ፣ ስለ መድኃኒት ቅመማ በሀሳብ ደረጃ የተቀመጡ ጉዳዮችን  ከቴክኖሎጂ እና ሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመሥራት ወደ ተግባር በመለወጥ ሂደቱ ጥልቅ ምርምር እንዲያደርጉ በማሰብ ነው የቀረጽነው::

ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶች  ነበሩ? ክፍተቶች ካሉ ይህ መርሃ ግብር ክፍተቶችን በመሙላት ረገድ የሚጫዎተው ሚና ምንድነው?

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ለመሆን በሂደት ላይ ነው:: እንደ ዩኒቨርሲቲም ባብዛኞቹ ሥርዓተ ትምህርቶች ላይ ክለሳ እያደረገ ነው:: እኛም በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ ሥርዓተ ትምህርት ላይ የነበሩ ችግሮችን  እንዲሞላ ታሳቢ አድርገን ነው የሠራነው:: በተጨማሪም ዕውቀት እና ክህሎት ከማስጨበጡ በዘለለ ገበያ ተኮር እንዲሆን ተደርጎ የተቀረፀ ሥርዓተ ትምህርት ነው:: ተማሪዎች ዉጤታማ ሆነው እንዲወጡ ዉጭ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ላይም ሄደው እንዲከታተሉ ለማድረግ በሂደት ላይ ነን::

ብዙ ጊዜ ግእዝን  ከኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያን  ጋር የማያያዝ ነገር አለ:: ይህን እንዴት ያዩታል?

እውነት ነው፤ ግእዝ ሲጠራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ አብሮ ስሟ ይጠራል:: ይህን ጉዳይ ልንነጥለው አንችልም:: ምክንያቱም ሀብቱን እና ዕውቀቱን ሰንዳ የያዘች የእምነት ተቋም ናት:: ስለዚህ የመርሃ ግብሩ መነሻም መድረሻም የሚሆነው እሷው ላይ ነው:: ይህም ኾኖ ሥርዓተ ትምህርቱን ከእኛ የሚለየው ጉዳይ አለ:: እኛ የምናስተምረው ቲዎሎጂውን ወይም የሃይማኖቱን ዶግማ አይደለም:: መርሃ ግብሩ የሚሰጠው  ሥነ ቋንቋዉ፣ ሳይንሱ እና በዉስጡ የተሰነዱ ዕውቀቶች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ነው::

በሰው ኃይል ደረጃ ብዙ ዓመት የማስተማር ልምድ ያላቸው በውስጥ እና በውጭ ሀገር የተማሩ  ረዳት ፕሮፌሰሮች አሉን:: በተጨማሪም ከሌሎች የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮፌሰሮችን እንጋብዛለን፤ እንዲሁም የውጭ ሀገር ተጋባዥ መምህራንንም እናመጣለን::  በቤተ መጻሕፍት ውስጥም ክላሲካል (ጥንታዊ) ጽሑፎች እና የጥናትና ምርምር (አካዳሚክ)መጽሔቶች እና ተዛማጅ የታሪክ ሰነዶች አሉ::

ተማሪዎች በሶስተኛ ዲግሪ የትምህርት ቆይታቸው ምን ይዘት ያላቸው ትምህርቶችን ሊያገኙ ይችላሉ?

በዋናነት የግእዝ ቋንቁ ሰዋስው፣ ሥነ ጽሑፍ እና  የቤተ ክርስቲያን ሥዕላት ላይ ሰፊ ምርምር የሚያደርጉ እና ጥናቶችን የሚሠሩ  ይሆናል::

ተማሪዎች በሙያው ተመርቀው ሲወጡ የት ሊቀጠሩ ይችላሉ? የሚጠብቃቸው ኃላፊነትስ ምንድነው?

የቅጥር ኹኔታን በተመለከተ ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋማት ተቀጥረው ሊሠሩ ይችላሉ:: ማለትም በኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች ባስተማሪነት፣ በባህል ማዕከላት ወይም ቤተ መዘክሮች (ሙዚየሞች)  ውስጥ በተመራማሪነት፣ በቤተ መዘክሮች እና ቤተ መዛግብት ውስጥ፣ ታሪካዊ የብራና ጽሑፎችን፣ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን እና የባህል ቅርሶችን በማስተዳደር፣ ጥንታዊ  ጽሑፎችን ወደ ዘመናዊ ቋንቋዎች በመተርጎም፣ በኅትመት እና በብዙኃን መገናኛ፣ በማማከር እና በፖሊሲ ልማት ላይ ተቀጥረው ሊሠሩ ይችላሉ:: እስካሁን የሚመረቁ ተማሪዎቻችንም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቀጣሪዎች ሆነዋል::

የመርሃ ግብሩ መከፈት ለዩኒቨርሲቲው እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?

የመርሃ ግብሩ መከፈት በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት:: በመጀመሪያ የዩኒቨርሲቲዉ ገፅታ ከፍ ይላል:: በመቀጠል በሀገር ውስጥ እና በውጭ ግእዝን የመማር ከፍተኛ ፍላጎት ስላለ በምስክር ወረቀት በ”ኦንላይን” ማስተማር ቢጀምር የገቢ ማመንጫ መንገድ ይሆናል:: በተመሳሳይ ተቋሙ ያለበት አካባቢ በርካታ ገዳማት፣ ቅርስ እና የግእዝ ዕውቀት ያለበት አካባቢ ነው:: ስለዚህ ተቋሙ ታሪክን በመመርመር፣ በመሰነድ የአካባቢዉን ማህበረሰብ ሊያግዝ ይችላል:: ግእዝ ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ የተሸከመ ቋንቋ ነው:: የማህበረሰቡ ታሪክ ተሰንዶ የምታገኘውም እዚሁ ቋንቋ ላይ ነው:: ታሪኩን እንዲያውቅ እንዲሁም ለሌሎች እንዲያስተዋውቅ ታደርገዋለህ::

በግእዝ  ቋንቋ  እና ሥነ ጽሑፍ ላይ ጥናት እያደረጉ ላሉ ተማሪዎች እንዲሁም ባለድርሻ የሚሉት ካለ?

ሥርዓተ ትምህርቱን ለመቅረፅ በነበረው ሂደት በትምህርት ክፍሉ ውስጥ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ምሁራን መኖራቸውን ተገንዝቤአለሁ:: ነገር ግን ከመማር ማስተማሩ በዘለለ ያለውን ዕውቀት ከሌሎች ሙያዎች ጋር  በማዋሃድ ወደ ተግባር መግባት ያሻል::  እኛ ሀገር አንድ ሰው ሀገር በቀል ዕውቀትን መሰረት አድርጎ መድሃኒት ሲቀምም እንደ ጠንቋይ ነው የሚታየዉ:: ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የግእዝ መጻሕፍትን በጀርመን ሀገር በራሳቸው ቋንቋ ተርጉመዉ ለመድሃኒት ቅመማ ይጠቀሙባቸዋል:: ቋንቋዉ የሄደው ግን ከእኛ ነው:: አሁን ላይ መድሃኒት በውድ ዋጋ የሚሸጡልን ግን እነሱ ናቸው:: ስለሆነም ይህ ሀገር በቀል ዕውቀት በሳይንስ ከተደገፈ እና ከሌሎች ሙያዎች ጋር በጥምረት ከተሠራ ዉጤታማ ሥራዎችን መሥራት ይቻላል:: በዘርፉ ላይ ያሉ አካላትም ይህን ቢያደርጉ የሚል ሀሳብ ነው ያለኝ::

ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ?

የግእዝ ቋንቋን ትምህርት ለማጠናከር መንግሥት ልክ እንደ ሌሎች ቋንቋዎች በፖሊሲ አስደግፎ በሥርዓተ ትምህርቱ  ማካተት አለበት ብየ አስባለሁ:: የግእዝ ቋንቋን ማጠናከር አማርኛ ቋንቋን እንደ ማጠናከር ነው::  ለአማርኛ ቋንቋ መወለድ ግእዝ ቋንቋ ነው መሰረቱ:: አማርኛ ባመዛኙ የሚጠቀመው የግእዝ ፊደላትን ነው:: ትግርኛም በተመሳሳይ የግእዝን ፊደላት ነው የሚጠቀም:: የግእዝ ቋንቋ ብዙ አይነገርም እንጂ በሰፊው ተሰንዶ ተቀምጧል:: በርካታ የኢትዮጵያ ልቦለድ ጸሐፊያን የግእዝ መሰረታዊ ዕውቀት አላቸው:: ለምሳሌ ደራሲ ሃዲስ ዓለማየሁን ማንሳት እንችላለን:: ይህም የግእዝ ቋንቋ እምቅ  የሥነ ጽሑፍ ዳራ እንደሚሰጥ ያሳያል::

(ደሳለኝ አላዩ)

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here