ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን “ዶርዜ ሰፈር” በሚለው ግጥሙ ዶርዜዎች ለሞት ያላቸውን አመለካከት አንጸባርቋል:: ሞት ለብዙዎች ከባድ ነገር ነው:: አንዳንዶች ደግሞ እንደ ባህላቸው ቀለል አድርገው ተቀብለውታል:: በአርማጭሆ ጀግና ሲሞት በቀረርቶ፣ በሽለላ፣ በፉከራ ታሪኩ እየተነገረ ጥይት እየተተኮሰ ይለቀስለታል:: በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ፊትን መንጨት እና ራስን መጉዳት ባህል ይሆናል::ሞት ሁልጊዜ አዲስ ክስተት ነው:: ከሞቱም፤ አሟሟቱ ይከብዳል:: ልዩ ልዩ ክዋኔ አለው::
የሰው ልጆች በአኗኗር ቢለያዩም በሞት ግን እኩል ይሆናሉ:: “ሞት ፍትሐዊ ዳኛ ነው” የሚባለው ለዚህ ነው:: የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡራን የሚለየው ሟች መሆኑን በማወቁ ነው::
በማህበራዊ ሥነ ልቦና ውስጥ የፍርሀት አስተዳደር (ቴረር ማኔጅመንት ቲዎሪ) የሚባለው ጽንሰ ሀሳብ የሞት ፍርሃታችንን ለመረዳት ሰፊ ማዕቀፍ ይሰጣል:: የሰው ልጆች በአንድ በኩል በደመነፍስ የመኖር እና የመቀጠል ፍላጎት ሲኖራቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሞት የማይቀር መሆኑን የማወቅ አእምሯዊ ችሎታ አላቸው:: በእነዚህ ሁለት ተቃራኒ እውነታዎች መካከል ያለው ግጭት ከባድ የሆነ ስነ ልቦናዊ ሽብር ወይም ጭንቀት ይፈጥራል:: ይህንን ሽብር ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር የሰው ልጆች ሁለት ዋና ዋና መከላከያዎችን ይጠቀማሉ:: “ቬሪ ዌል ማይንድ” የተሰኘው ድረ ገጽ ሁለቱን መከላከያዎችን አስፍሯል::
የመጀመሪያው ባህላዊ የዓለም አመለካከት ነው:: ሰዎች ትርጉም፣ ሥርዓት እና ዘላቂነት ባለው ዓለም ውስጥ እንደሚኖሩ እንዲሰማቸው የሚያደርጉ የጋራ እምነቶችን፣ እሴቶችን እና መመዘኛዎችን ይቀበላሉ:: ሃይማኖቶች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት (ገነት፣ ሲኦል፣ ዳግም ልደት) የሚሰጡት ተስፋ የዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው:: ይህም ሞትን እንደ መጨረሻ ሳይሆን እንደ ሽግግር እንድንመለከተው ይረዳናል:: የሞትን ሰይፍ ቀለል አድርገን እንድመለከተው ያደርገናል::
ሁለተኛው ለራስ ከፍ ያለ ግምት ነው:: አንድ ግለሰብ በባህሉ ውስጥ የተቀመጡትን እሴቶችና መመዘኛዎች በሚገባ እየተወጣ እንደሆነ ሲሰማው ለራሱ ያለው ግምት ከፍ ይላል:: ይህ ስሜት፣ ግለሰቡ ትርጉም ባለው ዓለም ውስጥ ጠቃሚ ሚና ያለው አካል እንደሆነ እንዲሰማው በማድረግ የሞት ፍርሃትን ያቀልለዋል:: ከኀጢያት ጎራ ርቄያለሁ ብሎ ሲያስብ ለሞት በፈቃዱ እጁን ለመስጠት አያቅማማም::
አያቴ ሁልጊዜ ስትጸልይ የምሰማት ቃል ነበር:: “እናቴ እመቤት እባክሽ ስቃየን ሳታበዢ ከቤቴ-ቤትሽ አስገቢኝ” ትል ነበር:: ግን ለሁለት ወራት አስቸጋሪ ሕመም ታማ አረፈች:: ብዙ ሰዎች ከሞት ይልቅ በመጨረሻዎቹ ጊዜያት ሊያጋጥም የሚችለውን ህመም፣ ስቃይ እና የክብር መዋረድን ይፈራሉ:: በአያቴ ያየሁት ይህን ነበር::
የሞት ፍርሃት የጋራ ስሜት ቢሆንም፤ ባህሎች ይህንን ፍርሃት የሚጋፈጡበት እና ለሞት ትርጉም የሚሰጡበት መንገድ እጅግ የተለያየ ነው:: አንዳንዶቹ ሞትን የህይወት ዑደት አካል አድርገው ሲያከብሩት ሌሎች ደግሞ በከባድ እና በተራዘመ ኀዘን ይገልጹታል::
“ኢተርኔቫ” ድረ ገጽ እንደሚለው ሞትን እንደ አስደሳች ክስተት ከሚያከብሩ ባህሎች መካከል የሜክሲኮ “የሙታን ቀን” በዓል ዋነኛው ነው:: ይህ በዓል በየዓመቱ ከጥቅምት 31 እስከ ህዳር ሁለት ይከበራል:: መሰረቱ ከስፔን ወረራ በፊት ከነበሩት የአዝቴክ ስልጣኔዎች የተወሰደ ነው ይባላል:: በአዝቴክ እምነት ሞት እንደ መጨረሻ ሳይሆን እንደ ተፈጥሯዊ የህይወት ዑደት ይታይ ነበር:: ነፍስ ከሞት በኋላ ጉዞዋን እንደምትቀጥል ያምኑ ነበር:: ይህ አስተሳሰብ ከካቶሊክ እምነት ጋር ተቀላቅሎ የዛሬውን በዓል ፈጥሯል:: በበዓሉ ቀናት የሟች ቤተሰቦች እና ወዳጆች መናፍስት ወደ ምድር ተመልሰው ከህያዋን ጋር ጊዜ እንደሚያሳልፉ ይታመናል:: ከለቅሶና ከሀዘን ይልቅ “የሙታን ቀን” በሙዚቃ፣ በዳንስ፣ በምግብና በመጠጥ የተሞላ ነው::
በሌላኛው ጫፍ ሞትን በከፍተኛ መከራ፣ በኀዘን እና በጨለምተኝነት ከሚመለከቱ ባህሎች መካከል በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የእንግሊዝ የቪክቶሪያ ዘመን ይጠቀሳል:: በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ የሞት መጠን እና የንግሥት ቪክቶሪያ ባለቤቷ ልዑል አልበርት ሲሞት ለረጅም ዓመታት የቆየ ጥልቅ ሀዘን፤ ሞትን የተመለከቱ እጅግ ጥብቅ እና የተወሳሰቡ ሕጎችን በህብረተሰቡ ውስጥ አስርጿል::
ይሕም ልምምድ ቁልፍ እምነቶች እና ልምዶች ተክሎ አልፏል:: ኀዘን የግል ስሜት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ሊያየው የሚገባ ነበር:: ቤተሰቦች ኀዘናቸውን በደረጃ እና በህግ በተደነገገ መልኩ መግለጽ ነበረባቸው:: በተለይ ሴቶች ባሎቻቸው ሲሞቱ ለረጅም ጊዜ ኀዘን እንዲቀመጡ ይገደዱ ነበር:: አንዲት ባልቴት ቢያንስ ለሁለት ዓመት ሙሉ ጥቁር ልብስ መልበስና ማህበራዊ ህይወትን ሙሉ በሙሉ ማቆም ይጠበቅባት ነበር:: ለወንዶች የኀዘን ጊዜው በጣም አጭር ነበር:: የቀብር ሥነ ሥርዓቶች እጅግ የተጋነኑና የሀብት ማሳያ ነበሩ:: የቪክቶሪያ ዘመን ሰዎች ሞትን እንደ ጨካኝ እና አስፈሪ ጎብኚ ይመለከቱት ነበር::
ከእነዚህ ሁለት ጽንፎች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ባህሎች ለሞት የራሳቸውን ትርጉም ሰጥተዋል:: “ካንትሪ ናቪጌተር” ድረገጽ እንደሚለው በሂንዱ እምነት ሞት ነፍስ ከአንድ አካል ወደ ሌላ የምትሸጋገርበት ሂደት ነው:: ይህ የልደት፣ የሞትና የዳግም ልደት ዑደት “ሳምሳራ” ይባላል:: አንድ ሰው በቀጣይ ህይወቱ የሚኖረው ህይወት የሚወሰነው አሁን በሚሰራው ስራ ነው::
የዚህ እምነት የመጨረሻ ግብ ከዚህ ዑደት ሙሉ በሙሉ ነጻ መውጣት ነው:: ስለዚህ ሞት እንደ መጨረሻ ሳይሆን እንደ የጉዞው አንድ አካል ይታያል:: ዳግም መወለድ ነው:: አስከሬን ማቃጠል ነፍስን ከስጋ በፍጥነት ለማላቀቅ ፈጣኑ መንገድ እንደሆነ ስለሚታመን ባህላዊ ልምምድ ነው:: አመዱ ብዙውን ጊዜ እንደ ጋንጅስ ወንዝ ባሉ ቅዱስ የውኃ አካላት ውስጥ ይበተናል::
በብዙ የአፍሪካ ባህላዊ እምነቶች፣ አንድ ሰው ሲሞት አይጠፋም፤ ይልቁንም ወደ ቅድመ አያቶች ዓለም ይሸጋገራል ተብሎ ይታመናል:: እነዚህ ቅድመ አያቶች በህይወት ያሉትን የቤተሰብ አባላት ይጠብቃሉ፣ ይመራሉ፣ ይባርካሉ ወይም ይቀጣሉ ይባላል:: እነርሱ በህያዋን እና በመንፈሳዊው ዓለም መካከል እንደ አገናኝ ድልድይ ይቆጠራሉ እንጂ ሞቱ አይባልም:: ይህም በህያዋንና በሙታን መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት የሚያሳይ ሆኖ እንዲታይ ያደርገዋል::
እያንዳንዱ ባህል ለሞት የሚሰጠው ምላሽ የራሱን እሴቶች፣ ፍርሃቶች እና ተስፋዎች ያንጸባርቃል:: እነዚህ የተለያዩ ልምምዶች የሰው ልጅ ይህንን ታላቅ ምስጢር ለመረዳትና ከእርሱ ጋር በሰላም ለመኖር የሚያደርገውን የማያቋርጥ ጥረት የሚያሳዩ ህያው ምስክሮች ናቸው::
ሦስቱ ዋና ዋና የአብርሃም ሃይማኖቶች ይሁዲነት፣ ክርስትና እና እስልምና ለሞት የተለያየ ምልከታ አላቸው:: በይሁዲነት ውስጥ ትኩረቱ በዋነኝነት በምድር ላይ ጻድቅ ህይወት መኖር ላይ ነው:: የኀዘን ጊዜው የሚጀምረው በሰባት ቀናት ከፍተኛ ኀዘን ነው:: በመቀጠልም እስከ አንድ ዓመት ሊቆዩ የሚችሉ አነስተኛ የኀዘን ጊዜያት ይከተላሉ::
ለክርስቲያኖች ሞት የነፍስ ከአካል መለየት ሆኖ ይታያል:: ለአማኞች የትንሣኤ እና የዘላለም ህይወት ተስፋ አላቸው:: ማዕከላዊው እምነት “የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ ሞትን ድል ነስቷል፤ ለሰው ልጆችም መዳንን ሰጥቷል” የሚል ነው::
ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር ዘላለማዊ ህብረት ወዳለበት ወደ ሰማይ፣ ወይም ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ መለያየት ወደሆነው ወደ ገሃነም የሚላኩበት የመጨረሻ ፍርድ እንዳለ ያምናሉ::
ሙስሊሞች ሞት ከዚህ ህይወት ወደ ድህረ ህይወት የሚደረግ ሽግግር እንደሆነ ያምናሉ:: ነፍስ እስከ ፍርዱ ቀን ድረስ በመጠባበቅ ላይ እንደምትቆይ ይታመናል:: በዚህ ጊዜ “አላህ የሰው ልጆችን በሙሉ ከሞት ያስነሳል እና በሥራቸው ይፈርዳል:: ጻድቅ ህይወት የኖሩት በገነት (ጀናህ) ይሸለማሉ፤ ያልኖሩት ደግሞ በገሃነም (ጀሃነም) ይቀጣሉ” ብለው ያምናሉ:: በእስልምና ውስጥ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ቀላል እና ከሞት በኋላ በፍጥነት የሚከናመወኑ ናቸው:: አስከሬኑ ታጥቦ፣ ተከፍኖ እና ወደ ቅድስቲቱ ከተማ መካ ፊት ለፊት ይቀበራል::
በአይቀሬው ሞት ፊት የሰው ልጅ በተስፋ መቁረጥ አልተሸነፈም:: ይልቁንም፣ ለሞት ትርጉም የሚሰጡ፣ ኀዘንተኞችን የሚያጽናኑ፣ የተስፋ እና የቀጣይነት ስሜት የሚሰጡ አስደናቂ የባህል እና የሃይማኖት ማዕቀፎችን ፈጥሯል:: ይሕ ደግሞ በምድር ላይ ለመኖር አቅም እና ተስፋ ሰጥቶታል::
ማረፈያ
ከሞት በፊት የመጨረሻ ቃላት
1.ካርል ማርክስ “የመጨረሻ ቃላት የሚናገሩት በቂ ያልተናገሩ ሞኞች ናቸው”
- የሮማው ንጉሠ ነገሥት አውግስጦስ “ሚናዬን በሚገባ ተጫውቻለሁ? እንግዲያውስ ስሄድ አጨብጭቡልኝ”
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል “ሁሉም ነገር ሰልችቶኛል”
- ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ “ስራዬ ሊኖረው የሚገባውን ጥራት ስላላገኘ እግዚአብሔርን እና የሰውን ልጅ አስቀይሜያለሁ”
- አሜሪካዊቷ ገጣሚት ኤሚሊ ዲኪንሰን “መግባት አለብኝ፣ ጉሙ እየመጣ ነው”
6- ኤልቪስ ፕሬስሊ “ለማንበብ ወደ መጸዳጃ ቤት እሄዳለሁ” ኤልቪስ ይህንን ለሴት ጓደኛው ጂንጀር አልደን የተናገረው በመጸዳጃ ቤት ውስጥ በአደንዛዥ ዕፅ ምክንያት በደረሰበት የልብ ድካም ከመሞቱ በፊት ነው።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሕዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


