እ.አ.አ በ2022 የካቲት ወር አጋማሽ የሩሲያ ታንኮች ወደ ዩክሬን ዘልቀው ሲገቡ ዋና ከተማዋን ኬቭን ጨምሮ በርካታ ከተሞችን በአጭር ቀናት ውስጥ በመዳፋቸው እንደሚያስገቡ በመተማመን ነበር:: ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ቨላድሚር ፑቲን ያሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ጦርነቱ በርካታ ነገሮች እየታዩበት ይኸው አንድ ሺህ ቀናትን ተሻግሯል::
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን እንዴት ሆኖ የኔቶ አባል ሀገር ትሆናለች? የሚለው እና ወደ አባት ሀገር ሩሲያ የሚጠቃለሉ ግዛቶችን ኬቭ ትመልስ ሚለው ጥያቄቸው “ልዩ ዘመቻ” ብለው ለጠሩት ጦርነት መጀመር ሰበብ እንደነበር የሚታወስ ነው::
የሞስኮው አለቃ በቀላሉ ይህ ህልማቸው እንዳይሳካ ግን ምዕራባዊያኑ ሀገራት እንቅፋት እንደሆኑባቸው ግልጽ ነው:: በዚህ ምክንያት በየጊዜው የመረጃ ማሰራጫ ጣቢያዎችን እየተጠቀሙ በአሜሪካ የሚመሩ ሀገራት ከዚህ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል:: ፓሪስ፣ በርሊን እና ብራሰልስን የመሳሰሉ ግዙፍ የአውሮፓ ከተሞች በሚሳኤሎቻችን ዕይታ ስር ናቸው፣ ብታርፉ ይሻላል ሲሉም ነው በማይፈታ ፊታቸው ታግዘው በተደጋጋሚ ያስጠነቀቁት::
የምዕራባዊያኑ ሀገራት መሪዎች ግን እንዲያውም ይውጣልዎት በማለት ሲያሻቸው ኬቭ በባቡር ድረስ በመጓዝ ሲፈልጉም ደግሞ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ሀገራቸው ድረስ በመጥራት የጀግና አቀባባል እያደረጉ ሲያበሳጯቸው ከርመዋል:: የአሜሪካን ምክርቤት እንደ ራሳቸው የተመላለሱበት ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንሰኪም የልብ ልብ እየተሰማቸው ዩክሬን የእናንተን ጦርነት እተዋጋች ስለሆነ ሳታመነቱ ልደግፉን ይገባል ሲሉ በተደጋጋሚ ተማጽኖም፤ ጥያቄም አሰምተዋል::
አሜሪካ እና አጋሮቿም ፍትሐዊ ጦርነት ብለው የሰየሙትን ዘመቻ በመጀመሪያ ቁመው በማጨብጨብ ቀጥሎ መቀነታቸውን በመፍታት ከማን ወገን በግልጽ እንደተሰለፉ አስመሰከሩ:: ዩክሬንም በቀላሉ ራሷን ለመከላከል የሚያስችላትን የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ከምዕራቡ ዓለም ማግኘት ጀመረች::
በቀላሉ በሩሲያ ኃይሎች ድል አድራጊነት ይጠናቀቃል ተብሎ የታሰበው ጦርነት መልከ ብዙ ሆኖ እንደቀጠለ ነው:: የክሬምሊን ባለስልጣናት ታዲያ አዲሱን አሰላለፍ ተመልክተው ምሥራቁን ዓለም ያማከለ የአፍሪካ ሀገራትንም ያልረሳ አዲስ ዋልታ ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ጀመሩ:: በዚህ ሁለት ጫፍ በረገጡ አመለካካቶች ምክንያት አስታራቂ የሌለው ጦርነት ሆኖ አድማሱንም አስፍቶ ቀጥሎ አንድ ሺህ ቀናትን (ሦስት ዓመት ገደማ) ተሸግሯል::
ቻይና አልፎ አልፎ ከምታደርገው የተናጠል ሙከራ በዘለለ ኬቭ እና ሞስኮ እንዲስማሙ ከአንጀቱ የሚፈልግ፤ የሚደክም አካል ጠፋ:: በዚህ የፖለቲካ ጨዎታ መሀል ግን የተለያዩ የዩክሬን ከተሞች እንደችቦ እየነደዱ ነው፤ ዜጎቾም በቀናቸው መንገድ ሁሉ ይሰደዳሉ:: በተቃራኒው የሩሲያ ከተሞችም ቦንብ በታጠቁ ከምዕራባዊያን በተለገሱ ሰው አልባ አውሮፕላኖች መደብደብ ቀጠሉ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ስልጣን ሊለቁ ጥቂት ቀናት የቀራቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዩክሬን አሜሪካ ሠራሽ ሚሳኤሎችን ወደ ሩሲያ ማስወንጨፍ እንደምትችል ፈቃድ መስጠታቸውን ተከትሎ በችግሩ ላይ ቤንዚን ጨምረውበታል:: ከዚህ ውሳኔ በኋላ ታዲያ ዩክሬን ወደ ሩሲያ ዘልቆ የገባ ጥቃት ፈጽማ ጦርነቱ ወደ ሌላ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አድርጎታል::
ይህን ተከትሎ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለጦራቸው በሰጡት ቀጭን ትዕዛዝ ዓለማችን ዓይታው የማታውቀውን አዲስ የሚሳኤል አይነት በዩክሬን ላይ ማዝነብ ጀመሩ:: አሜሪካን ጨምሮ ድርጊቱ ያስጨነቃቸው ሀገራት በዩክሬን የሚገኙ ኤምባሲዎቻቸው ለተወሰነ ጊዜ መዝጋታቸው ነው የተሰማው::
የኒውክለር ጦር መሣሪያ አጠቃቀምን ሥርዓት ያሻሻሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ስለ አዲሱ ሚሳኤላቸው በኩራት ያለውን አቅም ዘረዘሩ:: ይህ አዲሱ ኦሪሽንክ ብለው አቆላምጠው የሚጠሩት የሚሳኤል አይነት ከድምጽ ፍጥነት በዐሥር እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በሰከንድ ከሦስት ኪሎ ሜትር በላይ መምዘግዘግ ይችላል:: ይህ የሚሳኤል አይነት በዓለም ላይ አለ የተባለ የትኛውም ጸረ – ሚሳኤል መሣሪያ ሊያከሽፈው እንደማይችል ፕሬዝዳንት ፑቲን አስታውቀዋል::
ወትሮውንም “ምዕራባዊያን ሆይ ዐይታችሁት የማታውቁትን መዓት እናወርድባችኋለን” ሲሉ በተደጋጋሚ ያስጠነቀቁት ፑቲን ሰሞነኛውን ጥቃት ሙከራ ነው ሲሉ ገልጸውታል፤ ጥቃቱንም ስኬታማ በማለት የአዲሱን ሚሳኤል እንከን የለሽነት አሞካሽተውታል:: “ከዚህ በኋላ በርካታ ተመሳሳይ ዓለም ያላያቸው ውስብስብ የጦር መሣሪያዎችን በዩክሬን ምድር ላይ መሞከራችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ዝተዋል::
ይህ ኦሬሽኒክ በማለት ፑቲን የጠሩት ሚሳኤልም በቀላሉ የኒውክሌር ቦንብ ተገጥሞለት ወደ ተፈለገው ቦታ መሄድ የሚችል መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውሰዋል:: ይህን ሚሳኤል እስከ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ያለን ዒላማ በቀላሉ መምታት ይችላል:: ይህ ማለት የትኛውም በአውሮፓ የሚገኝ ሀገር በፕሬዝዳንት ፑቲን እጅ ሥር ይወድቃል ነው የተባለው::
ባለሙያዎች ይህ ኦሬሽኒክ የተሰኘው ሚሳኤል አንዱ ብቻ እስከ ዐሥር ሚሊዮን ዶላር ወጭ የሚጠይቅ መሆኑን በማንሳት ፑቲን መልዕክት ለማስተላለፍ ብቻ እንዳስወነጨፉት ያብራራሉ::
ጦርነቱ አድማሱ እየሰፋ መሆኑን የተረዱት እንደ ፖላንድ እና ጀርመን ያሉ ሀገራት ራሳችንን እናዘጋጅ እያሉ በመሪዎቻቸው አማካኝነት እያሳሰቡ ነው:: ስዊድንም ብትሆን ለዓመታት የነበረው ሰላማዊ ሕይወት ሊያበቃ ትንሽ ቀናት እንደቀሩት ለዜጎቿ አዋጅ በማስነገር ሁሉም ወታዳራዊ ስልጠና እንዲወስድ ትዕዛዝ አስተላልፋለች::
ሩሲያ በበኩሏ በራሷ ለዓመታት በማምረት ያዘጋጀቻቸውን ሚሳኤሎች ፊት ወደ አውሮፓ ከተሞች ከማዞር በተጨማሪ ሰሜን ኮሪያን እና ኢራንን በጎኗ በማሰለፍ ለአውዳሚው ጦርነት እየተሰናዳች ነው:: እስካሁን ገለልተኛ ነኝ የምትለው ቻይና ይህን ውጥረት በመመልከት ሁሉም አካላት እንዲረጋጉ መጠየቋ ተሰምቷል::
የቀድሞ የደህንነት ክፍል ኃላፊውን ሪቻርድ ግሪንል የሩሲያ ዩክሬን ግጭት ልዩ መልዕክተኛ አድርገው የሾሙት የአሜሪካ አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን ኒውክለር ያዘለ ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ሊወልድ የተቃረበውን ፍጥጫ እንደሚያስቆሙ ለጊዜው ተስፋ የተደረገባቸው ግለሰብ ናቸው:: ጦርነቱንም በ24 ሰዓታት ውስጥ እንደሚፈቱት መናገራቸው ይታወሳል፤ ይሁን እንጂ ተፋላሚ ኋይሎች ባላቸው የማይታረቅ ፍላጎት ምክንያት ለአንድ ሺህ ቀናት የዘለቀውን ጦርነት አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት በ24 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ እንደማይፈቱት ግለጽ ነው::
አሜሪካ የረዥም ርቀት ሚሳኤሎችን ተጠቅማ ዩክሬን ሩሲያን እንድታጠቃ መፍቀዷን ተከትሎ ጦርነቱ አድማሱን አስፍቷል፤ ሩሲያም የመልሶ ማጥቃቷን በማጠናከር ፈጣን የተባለውን ግስጋሴ እያደረገች፣ የዩክሬንን ግዛቶች እየተቆጣጠረች ነው ተብሏል፤ የሩሲያ ጦር በአንድ ሳምንት ብቻ ከ230 ኪሎ ሜትር በላይ የዩክሬንን መሬት መቆጣጠሩ ተነግሯል::
የተመድ መረጃ የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት የመቶ ሺዎችን ሕይወት ያጠፋ፣ ለአካል ጉዳት የዳረገ እና ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለ መሆኑን ያሳያል:: መረጃው አክሎም ጦርነቱ የከፋ የረዥም ጊዜ ጉዳት እንደሚያስከትል ጠቁሟል::
የመረጃ ምንጮቻችን፡- ቲ አር ቲ ወርልድ፣ ኢንዲፔንደንት፣ አልጀዚራ፣ ፍራንስ 24 እና ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ናቸው::
(በፍቃዱ ሄሮዳ)
በኲር የህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም