ጥላሁን ገሰሰ አንድ ቀን በሚል ርዕስ ዘፍኗል። ዳዊት መለሰም እንዲሁ አንድ ቀን በሚል ርዕስ አዚሟል። የዳዊት መለሰ አንድ ቀን ተስፋ ማድረግን፣ በእምነት መጠበቅን ይነግረናል።
የጥላሁን ገሰሰን አንድ ቀን ስንመለከተው አጉል ተስፋ ማድረግን፣ የዕድሜ መባከንን እና በይሆናል ተስፋ የዕድሜ ጀንበር መጥለቅን የሚያሳይ ነው።
ብዙዎቻችን በሕይወት እንደዚህ ሙዚቃ አንድ ቀን የሚል የሰነፍ ተስፋ ውስጥ ነን። ለተግባራችን እና ለእቅዳችን የአሁንን ጊዜ ለመስጠት ጥረት ማድረግ አንፈልግም። ይልቁንስ አንድ ቀን ይሆናል የሚል ራስን የምንሸነግልበት የስንፍና ሐረግ መምዘዝን እንመርጣለን።
ቻይናዊያን ይህንን የስንፍና ሐሳባችንን የሚሽር አባባል አላቸው። “ዛፎችን ለመትከል ትክክለኛው ጊዜ የዛሬ ሀያ ዓመት ነበር። ሁለተኛው ትክክለኛ ጊዜ አሁን ነው” ይላሉ። ቻይናዊያን እንደ እኛ አንድ ቀን የሚል መዝሙር የላቸውም። አሁን የሚል ግልጽ የጊዜ ምዕራፍን ነው የጠቀሱት። አሁን፤ አሁን!
የዘፓዎር ኦፍ ናው መጽሐፍ ደራሲ ኤኻርት ቶሌ ጊዜን በትናንት፣ በዛሬ እና በነገ ከፋፍሎ ያስቀምጥና በትናንትና ሐሳብ መያዝ ጸጸት ነው፤ በነገም ሐሳብ መጠመድ ቅዠት ነው ይላል። ለዚህም ነው የአሁን ኀይል ነው የሚያስፈልገን፣ ይህች የያዝናት ቅጽበት ናት በሕይወታችን ርግጠኛ የምንሆንባት ሲል ያስቀመጠው። ኤኻርት ነገ ምንም የሚጨበጥ አይደለም፤ ተገማች አይደለም፤ አሁን ያለንበትን ቅጽበት ለለውጥ እንጠቀምበት ነው የሚለው።
በኑሯችን ትክክለኛ ብለን የምናስበውን ጊዜ የመጠበቅ ዝንባሌ አለን። “እሄዳለሁ ባይ ስንቀ-ፈጅ ነው” እንደሚሉት አበው አደርጋለሁ ብለን ለምናስበው ነገር ነገ ላይ አሻግረን በመትለም ዕድሜያችንን እንፈጃለን። አንድ ቀን የሚል ሰው በጨለማ የሚጓዝ ነው። መድረሻውንም ሆነ አቅጣጫውን አያውቅም። አቅጣጫ ቢስ ጉዞ፤ መድረሻ አልባ መንገድን ይመስላል። በአንድ ቀን ውስጥ ርግጠኛ መሆን የሚቻለው ወደ ፊት የሚለው የጊዜ ምዕራፍ ላይ ብቻ እንደሚያተኩር ነው። የ20 ዓመት ወጣት አንድ ቀን ጥሩ ሕይወት ይኖረኛል ሲል፤ ከዚህ ዕድሜው ጀምሮ እስከሚሞትበት ያለውን ያጠቃልላል።
30 ዓመቱ ላይ ነው? በ40 ዓመቱ? በ60 ዓመቱ ነው? በ90 ዓመት ዕድሜው ነው? የሚለው ግልጽ መልስ የለውም። ኤኻርት እንደሚለው አንድ ቀን የአደርጋለሁ ቅዠት ነው። አንድ ቀን ኀላፊነትን መሸሽ? ዛሬ ነገ ማለት እና ሰበብ መፍጠር ነው። ጊዜው በራሱ እስኪስተካከል? ጦርነቱ እስኪቆም? ኑሮው እስኪረክስ? ፍቅር እስኪስፋፋ? ሕጉ መብታችንን እስኪያስከብር? ሰዎች እስኪደግፉን? መንግሥት ጥረታችንን ዓይቶ እስኪያግዘን መጠበቅ ነው አንድ ቀን ማለት?!
አሜሪካዊው የሰብዕና ግንባታ እና የሕይወት ክህሎት መጻሕፍት ደራሲ ናፖሊዮን ሂል አንድ ቀን የሚለውን ሐሳብ የሚሞግትበት ሐሳብ አለው። ናፖሊዮን “ጊዜው በራሱ ትክክል እስኪሆን አትጠብቀው” ይላል። ባለንበት ሁኔታ እና ጊዜ መጀመርን፣ በእጃችን ባሉ አቅሞች ስራ መስራትን ቀጥሉበት ነው የሚለን። በዚህም ሒደት መልካም ነገሮች እንደሚፈጠሩ ያስገነዝበናል። እንጂ መልካም ነገሮች በራሳቸው የመፈጠር ዕድል የላቸውም። ሰው ነው ተዋናዩ፤ የድርጊት ባለቤት።
ማይልስ ሙንሮ “የሰው ልጆች ለመፍጠር እንጂ ትክክለኛውን ነገር ለመጠበቅ አልተፈጠሩም” ይላል። በሕይወት ትክክለኛ የሚባል ጊዜ የለም። የሰው ልጆች ናቸው መጥፎ ጊዜያትን መልካም የሚያደርጓቸው ብሏል። ማይልስ የሰው ልጆች በውስጣቸው መፍጠር የሚችል አቅም አርግዘዋል፤ ብዙኀኑ ግን በመጠበቅ ያልፋሉ ይላል። ወፎችን በምሳሌነት ያነሳል። ወፎች ገና ልጅ መውለድ ሲያስቡ ለልጃቸው ጎጆ ለመስራት ሳር እና እንጨት ይለቅማሉ። ያለ ድካም ለረጂም ቀናትም ጎጆውን ሰርተው በዚያው ውስጥ ይራባሉ። የሰው ልጆች ከወፎች የማይነጻጸር ግዙፍ አቅም ቢኖራቸውም ሳይረዱት፣ መልካም ጊዜን በመጠበቅ እንደሚያፉ ያነሳል።
ትክክለኛ የሚባል ጊዜ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። የሰው ልጆች ግን የማይመጣውን ትክክለኛ ጊዜ ይጠብቁታል። የሰው ልጆች አረዳድ እና ትርጉም አሰጣጥ ልዩነት ካልፈጠረ በቀር የትኛውም ዘመን ብቻውን ሰላም፣ ብቻውን ረሀብ፣ ብቻውን ስደት፣ ብቻውን ፍቅር ሆኖ አያውቅም። በየትኛውም ዘመን ኑሮ ርካሽ ሆኖ አያውቅም፤ የሰው ልጆች አኗኗር እና አረዳድ ልዩነት ሊፈጥር ይችላል። አንድ ኪሎ ጤፍ አንድ ብር ከሐምሳ ሳንቲም እያለም ኑሮ ውድ ነበር። ዘይት በሊትር አስር ብርም እየተሸጠ ኑሮ ውድ ነበር። ዘንድሮ በመቶ ሐምሳ ብር አንድ ኪሎ ጤፍ ሲሸጥም ሕዝብ ይማረራል። ምናልባትም ከ20 ዓመታት በኋላም ዛሬ ተወደደ ብለን የተማረርንበትን ቀን እናመሰግን ይሆናል።
እኛ እየጠበቅን ያለነው ኑሮ እንዲረክስ፤ ጦርነት እንዲጠፋ፣ ሰዎች እንዲደግፉን እና ሌሎች መልካም ነገሮች እንዲሆኑ ነው። አንድ ቀን የማይመጣውን እንግዳ መጠበቅ ነው። ናፖሊዮን ትክክለኛውን ጊዜ አትጠብቁት፤ አይመጣም፤ ከጠበቃችሁት ቆማችሁ ትቀራላችሁ የሚለው ለዚህ ነው።
እወድቃለሁ የሚል ፍርሀት፣ በነገ ርግጠኛ መሆን አለመቻል፣ በራስ መተማመን ማጣት፣ ችግሮችን መሸሽ (ኀላፊነት አለመውሰድ) የሰው ልጆች ሕይወታቸውን አንድ ቀን በሚል ምኞት እንዲቆሙ ከሚያደርጋቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ሞክሮ መውደቅ ብዙዎች የሚፈሩት ጉዳይ ነው። በስኬታችን የሚደሰቱ ባይኖሩም በውድቀታችን የሚሳለቁ፣ የሚዘባበቱ እና የሚፈርዱ መኖራቸው ገሀድ ነው። ዛፍ ሲያድግ ልብ የሚለው የለም፤ ሲወድቅ እንጂ እንደሚባለው፤ ብዙዎች ለመጀመር የሚፈሩት ይህንን በትር መቋቋም የሚችል ትክሻ ባለማዳበራቸው ነው።
ነገ፣ ከርሞ፣ የዛሬ ወር፣ የዛሬ ዓመት፣ ከአምስት ዓመት በኋላ፣ የሚሉት ምናልባትም ግልጽ የጊዜ ገደብ የተቀመጠላቸው ይመስላሉ። የሆነ ቀን፣ አንድ ቀን፣ ፈጣሪ ሲፈቅድ የሚሉ ደግሞ ገደብ የለሽ ጊዜያት አሉ። አንድ ቀን በሚል ምኞት ውስጥ ከሆንን ዛሬን የማጣጣም እና የመኖር ዕድላችን ደካማ ነው። ስራችን፣ ደስታችን፣ ሕይወታችን፣ ፍቅራችን፣ ትዳራችን ለነገ በቀጠሮነት ማስያዣ ቀብድ ይሆናል። ነገ እደሰታለሁ እና ተጨማሪ ገንዘብ ሲኖረኝ ዘና ብዬ እኖራለሁ የሚሉ አስተሳሰቦች በዛሬ ደስታ እና ጥሩ ሕይወት እንዳይኖረን የሚያደርጉ ናቸው።
የሆነ ቀን የሚሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ በጉዞ ላይ አይደሉም። የሚጠብቁት ቆመው ነው። መልካም መንገዶች ደግሞ በጉዞ የሚገኙ እንጂ በመቆም አይደለም።
በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ቢለያይም እንኳን ለቅሶ የሰርግ ያህል የሚደምቅባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ያደግሁበትን አካባቢ ለቅሶ ስመረምር የገባኝ አንድ ነገር ለቅሶ የሚደምቅበት ምክንያት ነገ በሚል ብዙዎች ለቤተሰብ፣ ለልጅ፣ ለወላጅ፣ ለወዳጅ የሚገባውን ጊዜ አይሰጡትም። በግል ጉዳያቸው ሲሯሯጡ በመሐል ድንገት የሚወዱት ሰው በሞት ይጠራል። ያን ጊዜ የለቅሶ ግጥሞች በጸጸት የተሞሉ ይሆናሉ። ሳላደርግለት/ሳላደርግላት፤ ብነግራት ኖሮ/ብነግረው ኖሮ፤ ሳላስብ ተነጠቅሁ የሚሉ ይሆናሉ። ይህ አንድ ቀን የሚል እሳቤ የሚፈጥረው ዛሬን በነገ የመነጠቅ ጸጸት ድምጽ ነው። ለቅሶን የሰርግ ያህል የሚያደምቀው ጸጸት ነው። ጸጸት ደግሞ በትናንትናው መቆጨት ነው።
ከአንድ ቀን ምኞት አዙሪት ለመውጣት ሁለት ምርጫዎች ከፊታችን ይቀርባሉ። ባለንበት መልካም አጋጣሚዎችን መጠበቅ ወይም ሕልማችንን መኖር መጀመር።
ኒልስ ሳልዝበርግ ፕሮክራስቲኔሽን በሚለው መጽሐፍ ላይ እንዳሰፈረው ነገ የሚል ምኞት ከስሜት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ ሰው ምን ይለኛል߹ እወድቃለሁ߹ በትክክል ባላደርገውስ የሚሉ ስሜቶች ጋር በቀጥታ ይገናኛል፡፡ የረጂም ጊዜ ደስታን ወደ ኋላ በመግፋት በጊዜያዊ ደስታ የመጠመድ አባዜንም ያስይዛል፡፡ ኒልስ የሚለው ደስታችሁን ለነገ ስትሉ አዘግዩት፤ በአጭር ጊዜ የሚደሰት ሰው አሁን መስራት ያለበትን አይሰራም፤ መክፈል ያለበትን ዋጋ አይከፍልም ነው።
ዛሬ ነገ በማለት የመወላወል አባዜ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊከተሏቸው ይገባሉ ያላቸውን ዘዴዎች ኒልስ አስፍሯል፡፡
አውቆ ማቀድ߹ እቅዱን ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራትን በትንሽ በትንሽ መጠን ማከናወን፣ የሕይወት ጉዟችንን እየተዝናናንበት ማለፍ ተገቢ ነው ይላል፡፡ ብዙ ሰው በስራው ውጤት ላይ በማተኮር በስራው ሒደት አይደሰትም፡፡ ውጤቱን ማሰብ የመንገዱን ርቀት አሳይቶ ሊያደክም ይችላል፡፡ ለዚህ ነው በጉዞው መደሰት ተገቢ የሚሆነው፡፡ አርሶ አደር ማሳውን እያየ የማይደሰት ከሆነ ምርቱን ብቻ ሲያስብ ጉልበት ያጣል፡፡ በሂደቱ ተደሰት፤ ውጤቱ በራሱ ይመጣል ነው የሚለው ኒልስ፡፡
ጊዜን ለጉዳዮች ከፋፍሎ ማስቀመጥም የበለጠ ትኩረት የሚገባውን ተግባር እንድናስቀድም እድል ይሰጠናል፡፡ የተበጀተ߹ የተመደበ እና ለጉዳዮች ተከፋፍሎ የተቀመጠ ከሆነ በከንቱ አይባክንም፡፡ አካባቢን ምቹ ማድረግ ቀጥሎ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ የተረጋጋ߹ ምቹ እና ለትኩረት የሚረዳ አካባቢን መፍጠር ዛሬ እንድንጀምር የሚያግዘን ርምጃ ነው፡፡
ሜል ሮቢንስ የ “ሀው ቱ ስቶፕ ፕሮክራስቲኔሽን” መጽሐፍ ጸሐፊ ናት። በዚህ መጸሐፏ ነገ እጀምራለሁ ማለት የውዝግብ እና ጭንቀት ማስታገሻ ኪኒን ነው ትላለች። ይህም ሲደጋገም ወደ ልማድ ያድግና በየ ዓመቱ ከርሞ እጀምራለሁ፤ አንድ ቀን እሰራለሁ ወደ ሚል ልማድ ያድጋል ብላለች። ብዙ መስራት ያሉብን ስራዎች ይኖራሉ፤ ለመጀመር የሚያስፈሩን ምክንያቶች አሉ። ስራውን ለመጀመር አስበን እንቆማለን፤ በሐሳብ ተወጥረን ጭንቀት ውስጥ ስንገባ አዕምሯችን ሰላም ያጣል። ያን ጊዜ “በቃ የሆነ ቀን እጀምራለሁ” ብሎ ከጊዜያዊ ጭንቀቱ ረፍት ያገኛል። ለዚህ ነው ነገ ማለት የጭንቀት ማስታገሻ ኪኒን ነው የምትለው ሜል ሮቢንስ።
የሰው ልጆች በነገ እና አንድ ቀን አድርጋለሁ ምኞት ታጥረው እንዳይቀሩ ሜል የመፍትሔ ሐሳቦችንም ትናገራለች። የመጀመሪያው የሚያስጨንቀንን ጉዳይ መረዳት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከአምስት ጀምሮ ወደ አንድ መቁጠር ነው። አምስት፣ አራት፣ሦስት፣ ሁለት፣ አንድ ብለን ቆጥረን ለድርጊት መወሰን እና በውሳኔያችን ጸንተን መቀጠል አለብን ትላለች።
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም