አንድ ኖቤል ለሦስት

0
8

የአልፍሮድ ኖቤል ሽልማት በ1893 ዓ.ም ጀምሮ ለዓለም ሠላም እና ምርምር የላቀ አስተዋፅኦ ያረከቱ ግለሰቦችን እውቀና የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ በየ አመቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩ ተመራማሪዎችን፣ ፖለቲከኞችን፣ አንቂዎችን በመምረጥ በሽልማት ያበቃል፡፡ ፖለቲከኞችን አንቂዎችን በመምረጥ ለሽልማት ያበቃል፡፡

ይህ አበረታች ሽልማትም እስከዛሬ የዘለቀ  ተግባር ነው፡፡ በታሪክ ውስጥ በሠላም፤ በኢኮኖሚክስ፣ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በስነፅሁፍ እና ሌሎቹም ዘርፎች አያሌ ሽልማቶች ተሰጥተዋል፡፡ የሽልማት ኮሚቴው መሥፈርቱን ተከትሎ የመረጣቸው ተሸላሚዎች የሰላም ሎሬትነት ክብርን ይጎናፀፋሉ፡፡ ዓላማው ለዓለም ሰላም፣ ለሰብዓዊነት መከበር፣ አዳዲስ የምርመራ ስራዎችን ማበረታታት ነው፡፡ ታዲያ በኖቤል ሽልማት ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡ  የተለዩ ክስተቶች ውስጥ አንዱን ሽልማት ለሦስት ግለሰቦች የተሰጠበት ታሪክ እናስነብባችሁ፡፡

ጥቅምት 4 ቀን 1986 ዓ.ም የሰላም ሽልማቱ እስከ ዛሬ ሠላም ለራቀው የመካከለኛው ምስራቅ ሦስት ታሪካዊ ሰዎች እንደሚበረከት ተሰማ፡፡ ለፍልስጥኤም እና ለእስራኤል ሰዎች መሆኑ ደግሞ የዓለምን ቀልብ  ስቦት አነጋግሮም ነበር፡፡

የቀድሞው የፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅት () መሪ ያሲር አረፋት፣ በወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ይሳቅ ራቢን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሹሜን ፔሬዝ በጋር የሰላም የኖቤል ሽልማቱን አሸንፈዋል፡፡

በ1940 ዓ.ም እስራኤል ሉዓላዊ ሀገር ሆና ከተመሰረተች እለት ጀምሮ በእስራኤላውያን እና ፍልስጥኤማውያን መካከል የተጫረው ግጭት እስከ ዛሬ ዋነኛው የቃጣናው ሥጋት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ፍልስጥኤማውያን ለሉዓላዊ ነፃነት፣ እስራኤል ለህልውና እና ለግዛት መስፋፋት በሚል አላማ አየሌ ደም አፋሳሽ ጦርነቶችን አካሂደዋል፡፡ እነሆ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ያስቆጠረው ግጭት የቃጣናውን ሠላም አቃውሶታል፡፡ ዜጐች በሠላም ወጥቶ መግባት ብርቅ እስኪሆን የዓመፆች፣ የውጥረት፣ እና የሽብር መነሃሪያ ሆኗል፡፡

በአስራኤል እና በፍልስጥኤም መካከል ያለው ጠላትነት በመካከለኛው ምስራቅ ክልል ላይ እየጋረጠ የመጣውን የረጅም ጊዜ የሠላም እጦት ለማስተካከል የሁለቱም ተቀናቃኝ መሪዎች የየራቸውን ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ በጋራ መክረው ያውቃሉ፤ ታሪካዊ ስምምንቶችንም ተፈራርመው የነበሩባቸው በርካታ አጎጣሚዎች በታሪክ ተመዝግበዋል፡፡ በአንድም በሌላ መንገድ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የአረብ ሀገራት መሪዎች ጋርም አያሌ ድርድሮችና ስምምነቶች ተደርገው ነበር፡፡ በብዛት በአሜሪካ ሸምጋይነት ሁለቱ ባላንጣዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው የተወያዩበት፣ የተፈራረሙበት እና እጅ ለእጅ የተጨባበጡባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ተሰተናግደዋል፡፡ ለአብነት በ1970 ዓ.ም ላይ በእስራኤል እና በግብፅ መካከል በአሜሪካ ሀገር የተፈረመው የካምኘ ዴቪድ ስምምነት የቃጣናው የሰላም ፈር ቀዳጅ ስምምነት ይጠቀሳል፡፡ በአስራ አምስት ዓመታት በኋላም ዮርዳኖሥ እና እስራኤል በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን አደራዳሪነት የሰላም ስምምነት ማድረጋቸው ሌላው የቃጣናው የሰላም እምርታ ነበር፡፡

የቀድሞው የፍልስጥኤም መሪ ነፍስ ሔር ያሲር አረፋት በጦርነት መካከል ሀገራቸውን እየመሩም ቢሆን ሕይወታቸውን ሙሉ ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ወደር የማይገኝለት ጥረት አድርገዋል፡፡ ከወደ እስራኤል ደግሞ ነፍስ ሔር ጠቅላይ ሚኒስትር ይሳቅ ራቢን እና እስራኤልን  ጉዳይ ሚኒስትርነት፣ በኘሬዝዳንትነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታዎች ያገለገሉት ሹሜን ፔሬዝ ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ያላሰለሰ ጥረት ያደርጉ እንደነበር በታሪክ ይጠቀሳል፡፡

ምንም እንኳ የሰላም ጥረቶች ቢኖሩም የታሰበውን ያህል ውጤት አስገኝተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ሆኖም የእነዚህ ሀገራቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውሰጥ እየመሩ ለአካባቢው ሰላም አብዝተው የሚጨነቁ መሪዎች ጥረት ያለ ምስጋና አልታለፈም፡፡ ይልቁኑም የ1986 ዓ.ም የኖቤል ሽልማት ለእነዚህ የመካከለኛው ምስራቅ ሦስቱ ብርቱ ሰዎች በመስጠት ዓለምን አስደምሟል፣ የሽልማት ኮሚቴው፡፡ በአንድ የሽልማት ዓመት አንድ ተመሳሳይ ሽልማት ለሦስት ተሸላሚዎች ሲሰጥ በወቅቱ 93ኛ ዓመቱን እስካስቆጠረው የሽልማት መርሃ ግብር ታሪክ ድረስ የመጀመሪያው ተብሎለታል፡፡ የሁለቱ  ባላንጣ ሀገራት መሪዎች ያሲረ አረፋት፣ ይሳቅ ራቢን እና ሹሜን ፔሬዝ ጎን ለጎን ቆመው ለመላው ዓለም እየታዩ ባለበት አጋጣሚ የሽልማት ኮሚቴው የዓለም ምርጥ የሠላም አርበኞች መሆናቸውን አውጆ ምርጡን የዓለማችንን ሽልማት አጎናፀፋቸው፡፡ በዚህም ዓለም ተደምሞ እንደበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ሽልማቱ ለእነዚህ ሰዎች መሰጠቱ ተሰምቶና አለም ተደንቆ ሳያበቃ፤ የመካከለኛው ምስራቅ ምድር ደስታውን አጣጥሞ ሳይጨርስ የኖቤል ሽልማቱን ሞገስ ሊያደበዝዝ የሞከረ አንዳች ክስተት ተፈጠረ፡፡ ከዓለም አቀፉ የሰላም ኖቤል ሽልማት ኮሚቴ አባላት መካከል አንደኛው ሽልማቱን በመቃወም ከኮሚቴ አባልነቱ ራሱን በይፋ አገለለ፡፡ ሁኔታውም በሽልማቱ ጥቁር ክብር ምሳሌ ላይ ጥላሸት አሳረፈበት፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ በ93 ዓመታት የሽልማቱ ታሪክ ውሰጥ እንደዚህ አንድ የኮሚቴ አባል በይፋ ሽልማቱን ተቃውሞ በገዛ ፍቃዱ ስልጣኑን በየፋ ሲለቅ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን የዚህ አለም አቀፍ ሽልማት ደግሞ ከሁለት ሰዎች በላይ ለሆኑ አሸናፊዎች ሲሰጥ የመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ይህ ኬር ክሪስተን ሰን የተባለው ራሱን ከሽልማት ኮሚቴ አባልነቱ ያገለለው አባል በወቅቱ ተቃውሞውን ሲገልፅ “ይህ የክብር ሽልማት ዜጎች በክፍተኛ ብጥብጥ እና ሽብር በሚሰቃዩበት ሁኔታ ታጥረው ሳለ በፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅት መሪው ያሲር አረፋት ሽልማቱ አይገባቸውም” ሲል ተቃሞውን በመግለፅ ነበር፡፡

ሽልማቱን ያደበዘው ሌላው ገጠመኝ ደግሞ በዚሁ እለት ምሽት ላይ በፍልስጥኤማውያን አጋቾች እጅ የወደቀን አንድ እሰራኤላዊ ወታደር ለማዳን የተደረገው ወታደራዊ ዘመቻ በመጥፎ ውጤት መጣናቀቁ ነበር፡፡

አጋቾቹ መሪያቸው ሸክ አህመድ ያሲንና በእስራኤል የታሰሩ 200 የሀማስ አክራሪ ወታደሮች እንደፈቱ ይጠይቁ ነበር፡፡ ጥያቄያቸው መልስ ካላገኘ ደግሞ በእጃቸው ያለውን የእስራኤል ወታደር እንደሚገድሉ ይዝቱ ነበር፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሳቅ ራቢን ግን ድርድር ማድረግ አልፈለጉም ነበር፡፡ እናም አጋቾቹ  ካስቀመጡት የጊዜ ገደብ አንድ ሰዓት ቀደም ብሎ ሚ/ር ራቢን ይህ የማዳን ዘመቻ እንዲፈፀም ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ግን አልተሳካም ታጋቹም አልዳነም፤ ለሌላ ተጨማሪ ህይወት መጥፋትም ምክንያት ሆነ፡፡

የእስራኤሉን ወታደር የማዳኑ ዘመን በአሳዛኝ ሁኔታ ከተደመደመ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሳቅ ራቢን ሲናገሩ፣ “… የኖቤል ሽልማቴን በዚህ ተግባር ለወደቁት ወተደሮች ህይወት መታሰቢያ ሳበረክት በደስታ ነው፡፡ ማንኛውም ሠላምን የማስፈን ፍላጎት አለን የሚል ሰው ሁሉ አክራሪ የሀማስ ሽብርተኛ ነፍሰ ገዳዮችን፣ አስላማዊ ጅሃድን እና  ሌሎች አፈንጋጮችን መዋጋት ግዴታው ነው፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የሰላም ገዳዮች ናቸው፡፡” በማለት ስሜታቸውን ገልፀው ነበር፡፡

ምንም እንኳ በሽልማቱ ወቅት እነዚህ አይነት ክስተቶችና ተቃውሞ በክስቱም የኖቤል ሽልማት ኮሚቴው መግለጫ ግን በሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ የሰላም ተነሳሽነት መኖሩ ከማበረታታትና በክልሉ ታሪካዊ የሰላም ችግር ሂደት ውሰጥ ወሳኝ የሰላም አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በኦስሎ ስምምነት ላይ  በተወሰነው መሰረት ሦስቱ መሪዎች ሊመረጡ መቻላቸውን ገልጿል፡፡ የአካባቢውን የሰላም ጥረት ሊያበረታታ ይችላል የሚል ግምት ፈጥሮ እንደነበርም እንዲሁ፡፡

ብቻ እነዚህ የአካባቢው ቁልፍ ሰዎች ያገኙት የሰላም ኖቤል ሽልማት  ለመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ሁለተኛው ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ያገኙት ግን በ1970 ዓ.ም የግብፅ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አንዋር ሣዳት ከወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ሜናቺም ቤጊን ጋር በጋራ የተበረከተላቸው መሆኑን ቢቢሲ ድረ ገፅ አስነብቧል፡፡

 

ሳምንቱ በታሪክ

እምየ ምኒልክ

የሸዋ ንጉሥ ዐፄ ምኒልክ በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድሰት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ እጅ ቅብዓ መንግሥት ተቀብተው ዳግማዊ ምኒልክ ተብለው የንጉሠ ነገስት ዘውድ ጫኑ፣፣

ዐፄ ምኒልክ ጥቅምት 25 ቀን  1882 ዓ.ም ነበር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው የነገሡት፣፣ የንግሥና በዓሉ በአዲስ አበባ እንዲሆን የተሰየመ ሲሆን ዐፄ ምኒሊክ በዋዜማው ጥቅምት 24 ቀን ከእንጦጦ ነማሪያም ቤተ ክርስቲያን ሄደው እንዳደሩ ታሪክ ያስታውሳል፤፤

ሌሊቱን ስርዓተ ንግሱ ተጀምሮ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ጳጳሱ የወርቅ ሰይፍ ባርከው አስታጠቋቸው፤፤ ከዚያም በወርቅ ስቦ የታሸቡ ሁለት ጦሮች አስይዘዋቸዋል፤፤ ይህ ከሆነ  በኋላ ቅብዓ መንሥቱን ተቀብተው የወርቅ ዘውድ እንደደፉላቸው ጳውሎስ ኞኞ በአጤ ምኒልክ በተሰኘወው መጽሃፉ ከትቦታል፤፤

ሳዳም ሁሴን

የቀድሞው የኢራቅ መሪ የስቅላት ቃጣት የተፈፀመባቸው ጥቅምት 26 ቀን 1993 ዓ.ም ነበር፤፤ ሳዳም በሀገራቸው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው በቀረበባቸው በሰው ዘር ላይ ፈፅመዋል በተባሉባቸው ወንጀሎች ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦ በስቅላት እንዲቀጡ ተደርጎአል፡፡

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here