አንገብጋቢዉ የሕዝብ ጥያቄ

0
163

የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም

ከተቀሰቀሰ 16ኛ ወራትን ያስቆጠረው የአማራ ክልል የሰላም መታጣት አሁንም ትኩረትን የሚሻ ነው::መንግሥት ችግሩን በሰላም ስምምነት ለመቋጨት ለአንድ ዓመት ሲያደርግ የነበረው ጥረት ባለመሳካቱ በአሁኑ ወቅት በሕግ ማስከበር እርምጃ የክልሉን ሰላም ለመመለስ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል::ሰላምን ለመመለስ የሚደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች ደግሞ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል::ሕዝቡ ካለፈው አንድ ዓመት ጊዜ በላይ በግጭቱ ምክንያት የደረሰበትን ሰብዓዊ ኪሳራ፣ ምጣኔ ሐብታዊ ድቀት እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ሲገልጽ ለመጭው ጊዜ ሰላም መሆን ይረዳሉ ያላቸውን የመፍትሄ ሐሳቦችንም ጠቁሟል::

ከጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጋር በተደረገው ውይይት ሕዝቡ ለሰላም ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል::ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተገኙበት በተደረገው ውይይት የሀገር ሰላምን ለማጽናት፤ ሰላም ከእያንዳንዱ ቤት ሊጀመር እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል::ሕዝቡ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ማኅበራዊ እንቅስቃሴውን እንዲያስቀጥል፣ የልማት ሥራዎችንም ማጠናከረ ከተፈለገ ሕዝቡ ለአካባቢው የሰላም ዘብ ሊሆን እንደሚገባ ተመላክቷል::

ነዋሪዎቹ “ችግርን በፈጠረው አስተሳሰብ ችግር አይፈታም፤ የሰላም እጦት ባመጣው አስተሳሰብም ሰላም አይገኝም፤ የገደለን በመግደል ግድያ አይቆምም፤ የወጋን በመውጋት ውጊያ አይቆምም” ብለዋል::የሰው ልጅ ከፍራፍሬ ለቀማ አሁን እስከደረሰበት የመረጃ ዘመን ድረስ ለውጥ የመጣው በመተቃቀፍ እንጂ በመነቃቀፍ እና በመገፋፋት እንዳልሆነም ተመላክቷል::“ነብር ወደ ቤት ከገባ በኋላ ማነው የላከብኝ ብለን ቆመን የምናይበት ጊዜ አይኖረንም፤ ምክንያቱም ነብሩ የማሰቢያ ጊዜ ሳይሰጠን ሊበላን ነው የመጣውና።” በጦርነቱ ሕጻናት ታግተው ለሽያጭ ጨራታ ወጥቶባቸዋል፤ ተገድለው መንገድ ላይ ተጥለዋል የሚሉ ድምጾችም ተስተጋብተዋል። በመሆኑም ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ሁሉንም ነገር ወደ ውጪ ከመግፋት ወደ ውስጥ ማየት እና መመርመር እንደሚገባ ተገልጧል::

አሁን እየተፈጠረ ያለው ነገር ከኢትዮጵያዊ ባሕል፣ ወግ እና ሥርዓት ያፈነገጠ መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸው አውግዘዋል::የተፈጠረው ችግር የጎንደርን ነባር ታሪካዊ መታወቂያ እያደበዘዘ ብሎም እያጠፋ በመሆኑ የጠፋውን ሰላም ለመመለስ ጊዜው አሁን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

ጦርነቱ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም የተጀመረው የልማት ሥራ ደግሞ የሚበረታታ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል::በመሆኑም ሕዝቡ የተጀመረው የልማት ሥራ ዳር ደርሶ በልማቱ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ ሰላምን ሊጠብቅ እንደሚገባም ተጠይቋል::ሰላምን የማረጋገጥ ኅላፊነት የአንድ ወገን ብቻ ሊሆን እንደማይገባ ተመላክቷል::በተለይ የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ለሰላም መረጋገጥ በትኩረት እንዲሰሩ የውይይቱ ተካፋዮች ጠይቀዋል::ቤተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች የሕገ ወጥ ግለሰቦች መደበቂያ መሆን የለባቸውም ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ለዚህም የሃይማኖት አባቶች የቤተ እምነቶችን ክብር እና ልዕልና አስከብሮ ዘመናትን የማሻገር ኅላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠይቀዋል::ትምህርት ቤቶችን ተከታትሎ ወደ ሥራ ማስገባት፣ በትምህርት ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ተማሪዎችን እና መምህራን የት እንዳሉ ማጥናት እና ወደ ትምህርት ሥራቸው እንዲመለሱ ማስቻል ለሰላም መሠረት መሆናቸውንም ተጠቁሟል::

ለሰላም የሚደረገው ውይይት ከሰሜን ጎንደር ዞን የአዳርቃይ ወረዳ ነዋሪዎች ጋርም ቀጥሏል::የአዲአርቃይ ሕዝብ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ ተረጋግቶ መኖር እንዳቃተው ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት::ይህ የሆነው ደግሞ መፍትሄ ባልተሰጣቸው ግጭቶች ነው::የውይይቱ ተሳታፊዎች ቀደምት አባቶች ይህችን ሀገር ለአሁኑ ትውልድ ሲያስረክቡ የአሁኑ ትውልድ ክብሯን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስረክብ ነው ብለዋል::ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ እየተፈጠረ ያለው አለመደማመጥ እና ሁሉንም ወደ ትጥቅ ትግል መውሰድ ሀገር የማስቀጠል አደራችን ዕውን እንዳይሆን እያደረገ በመሆኑ ሁሉም ለሰላም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ሲሉ ለራሳቸው ኃላፊነትን ሰጥተዋል::

ግጭቱ በሁሉም ዘርፍ ያሳደረው ተጽእኖ ከፍተኛ ቢሆንም በተለይ በዛሬ ታዳጊዎች፣ በነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና አሁንም ሁሉም ከሰላም የሚበልጥ ነገር እንደሌለ ተገንዝቦ ለሰላማዊ ትግል ዝግጁ እንዲሆን የሚያሳይ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል::ሀገር እንደ ሀገር እንዲቀጥል ከተፈለገ የትውልድ ቅብብሎሽ ክፍተት እንዳይፈጠር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም በውይይቱ ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አዘጋጅቶት በነበረው የሰላም ግንባታ የውይይት መድረክ የተገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው እስካሁን መፍትሄ አጥተው በቀጠሉ ግጭቶች የደረሱ ጉዳቶች ከዚህ በላይ ቀጣይነት እንዳይኖራቸው ልዩነቶች በውይይት መቋጫ ሊያገኙ እንደሚገባ ጠይቀዋል::በውይይቱ የተገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በግጭቱ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ምክንያት ሕዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዳያገኝ ሆኗል::በርካታ ነፍሰ ጡር እናቶች ጤና ተቋም ሳይደርሱ ለሕልፈት መዳረጋቸውን ተናግረዋል::ግጭቶች የተማረ ትውልድ ቅብብሎሹ እንዲገታ እያደረጉ መሆኑን እና በቀጣይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ሰላማዊ የእልባት መንገድን የሚያመላክት ትውልድ እንዳይኖር በማድረግ በሀገር የወደ ፊት እጣ ፈንታ ላይ ትልቅ ጠባሳ እንደሚፈጥር ተሳታፊዎቹ አስታውቀዋል::በመሆኑም የግጭት ምክንያቶችን ለይቶ ዘላቂ መፍትሄ በማስቀመጥ ክልሉን ብሎም ሀገራችንን ከተደጋጋሚ የግጭት አዙሪት ለማውጣት የሐሳብ የበላይነት ቀዳሚው ገዥ ጉዳይ ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር  የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች የሕዝቡ ቀዳሚ ፍላጎት ሰላም እንደሆነ የተረጋገጠበት ነው ብለዋል::ሕዝቡ እርስ በእርስ መገዳደል እና መጠፋፋት፣ እገታ፣ ዝርፊያ እና የመደበኛ እንቅስቃሴ መስተጓጎል እንዲቆም በአጽንኦት መጠየቁንም ተናግረዋል::የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲቆሙ፣ ባለ ሐብቶችን የሚያሳድዱ እና ከቦታቸው የሚያስለቅቁ አካላት መኖራቸውን የሕዝብ ግንኙነት አማካሪዉ ጠቁመዋል::ከምንም በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው የትውልድ ቅብብሎሹ እንዲቋረጥ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች መኖራቸውንም ጠቁመዋል::ግጭቱ የፈጠረው እነዚህ ሁሉ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ሕዝቡ በስፋት ማንሳቱንም አስታውቀዋል::

ከሰላም ውጭ ያለው አማራጭ የአማራ ክልልን ሕዝብ የሚመጥን ባለመሆኑ እና ግጭት አክሳሪ፣ አውዳሚ እና አጥፊ በመሆኑ መንግሥት አሁንም ቀውሱ በሰላማዊ አማራጭ እንዲፈታ ጽኑ አቋም እንዳለው ጠቁመዋል::በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ ያሉ ኀይሎች በሐሳብ የበላይነት ጽኑ እምነትን አሳድረው ልዩነቶቻቸውን በውይይት መፍታትን እንዲያስቀድሙ ጠይቀዋል::ይህ ሐሳብ የሕዝብ ጥያቄ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ተኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ያረጋገጡትም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ቋጭቶ ኢትዮጵያን በጋራ ከፍታ ላይ ማውጣት ነው::በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ጋር ንግግር መኖሩን ገልጸው ነገር ግን በታጣቂ ኀሎች እና በመንግሥት በኩል ቆመው ጥረቱን ለማደናቀፍ የሚጥሩ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል::የሰላም ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ በሀገር ደረጃ አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር ሁሉም ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠይቋል::

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here