አካል ጉዳተኞች  እና ልዩ ፍላጐቶቻቸው

0
53

የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት በጋራ ሆነው እጅግ መሠረታዊ እና ሀገራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር  የሀሳብ ልዩነቶች ወይም አለመግባባቶች ሲከሰቱ የመፍትሔ ሀሳቦችን አመንጭቶ መግባባት ላይ ማድረስ የኢትዮጵያ ሀገራዊ  ምክክር ኮሚሽን ተግባርና ኃላፊነት ነው:: በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ በሀገሪቱ  ተቋቁሙ በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንዲሁም በሕዝብ እና በመንግሥት በኩል ያለውን ግንኙነት በማሻሻል መተማመን የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እየሠራ መሆኑን ኮሚሽኑ  በበራሪ ጽሑፉ አስታውቋል::

ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፓለቲካ ባህል ለማዳበር እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታዎች መደላደል ለመፍጠር ወቅታዊ ችግሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ መፍትሔ አግኝተው  አስተማማኝ ሠላም ለመፍጠር እና ለሀገረ መንግሥት ምስረታ ጽኑ መሰረት ለመጣል ሀገራዊ ምክክር ሚናው ጉልህ መሆኑንም መረጃው አመላክቷል:: እጅግ መሰረታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም የሀሳብ ልዩነቶች ወይም አለመግባባቶች በሚታዩባቸው ጉዳዮች ላይ የምክክር አጀንዳዎችን ከተሳታፊዎች እና ከጥናቶች ሰብስቦ ኮሚሽኑ ይቀርጻል::

በሀገራዊ ምክክሩም ዲያስፖራው፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የፓለቲካና የሀሳብ መሪዎች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማኅበራት፣አካልጉዳተኞች እንዲሁም የመንግሥት አካላት ይሳተፋሉ::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ በ2024 ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ 17 ነጥብ 6 በመቶ/30 ሚሊዮን/ የሚሸፍኑት አካል ጉዳተኞች መሆናቸውን አመላክቷል::

ታዲያ በሀገራዊ ውይይቱ ከሚሳተፉት መካከል አካል ጉዳተኞች ተጠቃሽ ናቸው:: ከእነዚህ አካል ጉዳተኞች ውስጥ በክልሉ በሁሉም ዞኖች ከ25 እስከ 30 ውክልና ተሰጥቷቸዋል:: ከነዚህ ውስጥም አምስቱ አካል ጉዳተኛ ሴቶች መሆናቸውን ኮሚሽኑ በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ አረጋግጧል:: በውይይቱም በክልሉ  ከሁሉም  አካባቢ ውክልና የተሰጣቸው አካል ጉዳተኞች ተገኝተው ለኮሚሽን ሀሳብ እና አስተያየታቸውን አሰምተዋል::

ተሳታፊዎችም  በሀገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን  አድንቀዉ ይሁንና በምክክር ኮሚሽኑ ተለይተው ከተያዙት 180 አጀንዳዎች መካከል የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ራሱ አካል ጉዳተኛውን  የፓለቲካ ውክልና ተሳትፎ ግምት ውስጥ ያስገባ/ቁጥራቸውን/ እና ተቋማዊ አደረጃጀት እንዳልተፈጠረላቸዉ ጠቁመዉ እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል::

ይህ ማለት በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚወጡ ሕጐች የተበጣጠሱ፣ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ፣ በአካል ጉዳተኞች የሚመራ አንድ መንግሥታዊ ተቋም  የራሱ በጀት፣ የተደራጀ የሰው ኀይል… እንደሚያስፈልገው ጠይቀዋል:: የሕግ ማእቀፎችም የምልክት ቋንቋን ጨምሮ በሚወጡ ሕጐች እንዲካተቱ ጠይቀዋል::

ወ/ሮ ዝማምነሽ አባይ የሰሜን ጐንደር ዞን አካል  ጉዳተኛ ፌዴሬሽን ም/ ቤት ኘሬዝዳንት ናቸው:: እርሳቸውም የምክክር ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ተገኝተው በሰጡት አስተያየት  “በኮሚሽኑ ስብሰባ የተገኘሁት ለሦስተኛ ጊዜ ነው::  ምክክሩ አካታች እና አሳታፊ ነው:: አካል ጉዳተኛውም አለኝ የሚለውን ሀሳብ አቅርቦ በአጀንዳ እንዲያዝለት እያደረገ ነው:: ሀገራችን ሠላም እንድትሆን በመመካከር እና በመነጋገር  ችግሮችን እንፍታ፤ ተራርቀን በመነጋገር እርቅ አውርደን፣ ተሳስበን አንድ ካልሆን ሠላም አይመጣም:: ኮሚሽኑ ሀሳባችን እንዲካተት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል:: በቀጣይ ኮሚሽኑ ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል፤ እኛም የወከልነውን የኅብረተሰብ ክፍል ሀሳብ ይዘን በንቃት በመሳተፍ ድምጻችንን ማሰማት አለብን:: ለኮሚሽኑ ሕግና ሥርዓትም ተገዥ መሆን አለብን” በማለት አብራርተዋል::

እንደ ወ/ሮ ዝማም ገለጻ ከወረዳ ጀምሮ  ተሳታፊዎች የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል:: በውክልና ደረጃም በክልል ለ30 እንዲሁም በፌዴራል ደግሞ ለአምስት አካል ጉዳተኞች ውክልና ተሰጥቷል::  ከዚህ ውስጥ ሦስት ሴቶች ለሀገር አቀፉ የምክክር ኮሚሽን ውክልና ተሰጥቷል::

የሀገረሰብ አስተዳደር የአካል ጉዳተኞች  ማኅበራት ፌዴሬሽን ኘሬዝዳንት አቶ ደሳለኝ ዳኛው  በበኩላቸው ሀገራዊ ኮሚሽኑ ካሁን በፊት ከኅብረተሰቡ ጋር  አካቶ እና  በተናጠል በየዞኑ አካል ጉዳተኞች የየራሳችን አጀንዳ በማንሳት በጥልቅ ተወያይተው እንዲያቀርቡ አድርጓል::  ካሁን ቀደም በውይይቱ የሚሳተፉት  አካል ጉዳተኞች በቁጥር ጥቂቶች እንደነበሩ ጠቅሰዋል፤ በቀጣይ ግን ቁጥሩ እንዲጨምር ጠይቀዋል:: ምክንያታቸው ደግሞ በሚካሄው ውይይት ሁሉ  አካል ጉዳተኛው መሳተፉ  የኔ ነው የሚለውን ችግር ለምክክር ኮሚሽኑ በማቅረብ የነበሩ ችግሮች ቀርበው ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ያስችላል::

“አካል ጉዳተኝነት የነበረ፣ ያለ እና የሚኖር ነው:: እናም በቀጣይ ሀገራዊ ምክክሩ  ጉባኤው ሲካሄድ  አብዛኞቹ ረዳት ስለሚያስፈልጋቸው  ቀድሞ ታስቦበት  እንዲመቻች፣ ጉባኤው የሚካሄድበት ቦታ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ  እንዲሆን፤  ፎቅ ላይ ከሆነ ደግሞ አሳንሰር/ሊፍት/ እንዲኖረው ጠይቀዋል:: “አካል ጉዳተኞች መሳተፋቸው “ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” ነውና የአካል ጉዳተኞችን ችግር ነቅሶ ለማውጣት ራሳቸው አካል ጉዳተኞች መሆናቸው ይመረጣል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::

ሌላው አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው “እስካሁን ከመጣንበት የሕይወት ልምድ ‘አካል ጉዳተኞች በሽተኛ ስለሆኑ የሚያስፈልጋቸው ህክምና ነው፤ አካል ጉዳተኛ መራመድ፣ መሥራት አይችልም፣ ማሰብ አይችልም ….‘ በሚል አስተሳሰብ እንደ ሰው ተቆጥሮ ሰብአዊ መብቱ ሳይከበር ቆይቷል:: ችግሩን የፈጠረው ደግሞ ማኅበረሰቡ መሆኑን በማወቅ በቀጣይ  የተሳሳተ ግንዛቤ ስለሆነ  ሊወገድ እንደሚገባ ጠይቀዋል::

አካል ጉዳተኞች ልዩ ፍላጐታቸው ምላሽ እንዲያገኝ፣ ማኅበራዊ ትስስር ለመፍጠር፣ ችሎታቸውን ለሀገራዊ እድገት  እንዲያበረክቱ…” በሀገራዊ ምክክር መሳተፋቸው ጥሩ ጅምር መሆኑን ጠቁመዋል::

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር አካል ጉዳተኞችን ወክለው   የተገኙት ግለሰብ በበኩላቸው   የአካል ጉዳተኞች ችግር በአካል ጉዳተኛ  እንጅ በሌላው የኅብረተሰብ ክፍል በአግባቡ እንደማይገለጽ ተናግረዋል:: ሀገር ሠላም ስትሆን ቀዳሚ ተጐጂዎች አካል ጉዳተኞች በመሆናቸው ካሁን በፊት በሚካሄዱ ውይይቶች   በቀጥታ አለመሳተፋቸው አግባብ እንዳልነበር አንስተዋል:: “የሴቶች፣ የአረጋዊያን፣ የሕፃናት….” ተቋማት አሉ:: አካል ጉዳተኞችን በቀጥታ የሚወክል ማኅበር ግን የለንም፤ ጉዳታችን ታይቶ ውክልናችን አልተረጋገጠም:: አሁን ጅምሩ መልካም ነው “ብለዋል::

“የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ውይይት የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያ እንዳሉት በኢትዮጵያ ውስጥ ከጠቅላላው  ሕዝብ አንድ አምስተኛው አካል ጉዳተኛ ናቸው:: እነዚህን አካላት ያላሳተፈ ሀገራዊ ምክክር ሁሉንም አካቷል ለማለት እንደማይቻል ጠቁመዋል::

እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ሀገራዊ ምክክር የሚያስፈልገው ሀገር ጥያቄ ውስጥ ስትገባ፣ የሀገር ህልውና አስጊ ሁኔታ ውስጥ ሲሆን፣ ልዩነቶች ሲፈጠሩ ችግሩን በውይይት ለመፍታት፣ በማኅብራዊ ውክልን ለማደስ እና እሴቶችን ለመፍጠር ነው:: ሀገራዊ ምክክር አካታች /ሃይማኖትን፣ ብሔርን፣ ሴቶች እና ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን…/ ማካተት እንዳለበት ባለሙያዋ ጠቁመዋል:: እነዚህን አካላት ተሳታፊ በማድረግ ደግሞ ትርጉም ባለው ሁኔታ ሀሳባቸው ተካቶ ድምጻቸው መሰማት እንዳለበት አስረድተዋል::

መረጃ

የሀገራዊ ምክክር ከድርድር እና

ከክርክር በምን ይለያል?

ሀገራዊ ምክክር እንደ ድርድር ዜጎች ሊያሳኩ በሚያስቧቸው ውስን የሆኑ ፍላጎቶች ላይ ስምምነቶች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ይልቅ ዜጎች ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ችግሮቻቸውን በዘላቂነት የሚፈቱበትን መደላድል ይፈጥራል፤

ድርድር የሚታዩ ወይም የማይታዩ ይዞታዎችን በማከፋፈል፣ የራስ ጥቅምን በማስጠበቅ፣ ለአንደኛው ወገን በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ ሙዓለ ንዋይን በመስጠት ግጭትን ለማብረድ የሚያገለግል ሂደት ነው:: ምክክር ደግሞ የሰዎችን ግንኙነት እና ትብብርን በመገንባት በሰዎች መካከል የመከባባር፣ የመተማመን እና የመተሳሰብ ባህል በማዳባር የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ይሠራል፤

በክርክር ውስጥ የሚዘወተረው አንዱ የሌላውን ሀሳብ ውድቅ በማድረግ የበላይነትን ለማሳየት ሲሆን በምክክር ሂደት ውስጥ ግን አንዱ የሌላውን ወገን ህመም በመስማት ለሌኛውም ወገን ችግር በጋራ መፍትሔን ለመፈለግ በጋራ ይሠራል::

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here