አካል ጉዳተኞች የቴክኖሎጂ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እየተሠራ ነው

0
106

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ አካል ጉዳተኛ የመንግሥት ሠራተኞች አካል ጉዳት ከሌለባቸዉ የመንግሥት ሠራተኞች እኩል ለደንበኞች አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የኮምፒውተር ስክሪን ማንበቢያ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቶ አስመርቋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ ስር ምድረ ገነት ቀበሌ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ባለሙያ ሊዲያ አስማማው የሥልጠናው ተሳታፊ እና ዐይነ ስውር ናት፡፡

በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥራ ሥራ ከጀመረች ጊዜ ጀምሮ ዐይናማ ሰዎች እያነበቡላት እና እየጻፉላት ሥራዎችን ሥትሠራ እንደነበር ነግራናልች፡፡

ለሥራ የሚያግዝ የተሟላ ኮምፒውተር እንደሌላትም ነው የገለጸችልን፡፡ በአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ቢሮ አማካኝነት በተሰጠው ሥልጠና ኮምፒውተር ከመክፈት ጀምሮ ጽሑፎችን ኮምፒውተር ላይ ጽፎ ማንበብ የሚያስችል ሥልጠና ማግኘቷን ተናግራለች፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ጽሕፈት ቤት የጎልማሶች ትምህርት ባለሙያ ሰናይ አማረ ደግሞ ሌላኛው የሥልጠናው ተሳታፊ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ኮምፒውተር ለመጠቀም የሚያስችል ዕውቀት እንዳልነበረው አንስቷል፡፡ ከዚህ በፊት በረዳት አማካኝነት መንግሥታዊ ሥራዎችን መከወኑ የተለያዩ ክፍተቶች ይፈጥርበት እንደነበርም ተናግሯል፡፡

ከዚህ በኋላ ግን ኮምፒውተር ካለ ማንኛውንም ሥራ ያለ ረዳት አካል ጉዳት እንደሌለባቸው የመንግሥት ሠራተኞች መሥራት እንደሚችልም አክሏል፡፡

ሥልጠናው ቀጣይነት እንዲኖረው ነው የጠየቀው።

የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገዬ በአማራ ክልል በርካታ መሰናክሎችን አልፈው በመንግሥት ሥራዎች ላይ ተሠማርተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ በርካታ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

አካል ጉዳተኛ የመንግሥት ሠራተኞች፣ አካል ጉዳት ከሌለባቸው ጋር ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና የክህሎት ሥልጠና ችግር እንዳለም አንስተዋል፡፡

በተለይ ደግሞ ዐይነ ስውራን እና መስማት የተሳናቸው አካል ጉዳተኞች በሌሎች ሰዎች አጋዥነት ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡

ቴክኖሎጂን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እና ተደራሽ በማድረግ ከሌሎች ሰዎች ጥገኝነት ነጻ ማድረግ ግን ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ዘመኑ የውድድር እና የቴክኖሎጂ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሁን ላይ ብዙ ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶች ዲጂታላይዜሽን እየሆኑ ነው፤ በመሆኑም ለአካል ጉዳተኛ የመንግሥት ሠራተኞች ምቹ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማቅረብ እና ሥልጠናዎችን ማዘገጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ይህንንም የሚያስገድዱ ሕጎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

በቀጣይ ዩኒቨርሲቲዎች እና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ከአጫጭር ሥልጠናዎች ባለፈ የአካል ጉዳተኞችን ሕይዎት የሚቀይሩ የቴክኖሎጂ ሥልጠናዎችን እና ውጤቶችን ማቅረብ ላይ በማተኮር እገዛ እንዲደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ የአቅም ግንባታ ባለሙያ ሀብታሙ ላቀ የመንግሥት ሠራተኛ አካል ጉዳተኞች በተለይም ደግሞ ዐይነ ስውራን ከቴክኖሎጂ የተገለሉበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ቢሮው በአሁኑ ወቅት ከሰጠው ሥልጠና በተጨማሪ እንዲህ አይነት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን በተለያየ ጊዜ ሲሰጥ መቆቱን ጠቅሰዋል፡፡

ጊዜው የዲጂታል ዓለም ነው ያሉት ባለሙያው አካል ጉዳተኞች የቴክኖሎጂ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ እየሠራን ነው ብለዋል።

ሠልጣኞች ከሥልጠናው በኋላ የኮምፒውተር ኪቦርድን በመጠቀም አጠቃላይ የኮምፒውተሩን ስክሪን በመቆጣጠር ይጽፋሉ፣ ያነባሉ፣ የሚፈልጉትን መረጃ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

በሥልጠናው በባሕር ዳር ከተማ በሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ተቀጥረው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ 20 አካል ጉዳተኛ የመንግሥት ሠራተኞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡

ሥልጠናው በአጋር አካሎች ተደግፎ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል አግባብ መቀጠል እንዲችል እገዛ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

(ሮዛ የሻነህ)

በኲር የህዳር  1  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here