የአማራ ክልል የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ከዞን፣ ከከተማ አሥተዳደሮች፣ ከማሕበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ ጽ/ቤት የዘርፉ መሪዎች እና ከብሔራዊ ፓርኮች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የስምንት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም እንዲሁም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በተመለከተ በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ ተስፋሁን ዓለምነህ “ዛሬ ያለንን ሀብት በአግባቡ መጠበቅ ካልቻልን ነገ ለውጤት መብቃት አንችልም” ብለዋል። ኃላፊው እንዳሉት የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ለትውልድ የሚሻገር በመሆኑ በነቃ እና በበቃ ሁኔታ መሥራት ይገባል። ከዚህ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ መሆኑን በማንሳት የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል አካባቢን መጠበቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት። በሠው ሠራሽ እና በተፈጥሮ የሚከሰቱ እንደ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና መሠል ችግሮችን አካባቢን በመጠበቅ መከላከል እንደሚቻል አመላክተዋል።
አካባቢን በዘላቂነት ለመጠበቅ እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዓለምነህ ጣና ሐይቅ፣ ዓባይ ወንዝ እና ሌሎች የውኃ ሀብቶችን በመጠበቅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ለማግኘትም በትጋት እየተሠራ መሆኑን ነው አብነት ያነሱት። ከዚህ በተጨማሪም ፓርኮችን እና ደኖችን በመጠበቅ ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዓለምነህ ማብራሪያ የአካባቢ ጥበቃ በቅንጅት መሥራትን ይጠይቃል፤ በክልሉ በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ደግሞ በጥብቅ ሥፍራዎች ላይ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ፣ የሰደድ እሳት እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጋርጠውበት ነበር። በመሆኑም ጉዳት የደረሰባቸውን ጥብቅ ሥፍራዎች በልዩ ትኩረት እንዲያገግሙ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ የማሳደግ ኃላፊነት አለብን ያሉት አቶ ተስፋሁን ብዝኃ ህይወቱን ከጉዳት ለመታደግ በትብብር እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
በቀጣይ ወራት በዕቅዱ ያልተከናወኑ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ትኩረት መሠጠቱን አብራርተዋል። ለዚህም ከተቋማት ጋር ለመሥራት ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል።
በክልሉ በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሄክታር መሬት የተፈጥሮ ደን በመከለል እንዲጠበቅ እየተደረገ መሆኑን የአካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኃላፊው በልስቲ ፈጠነ ተናግረዋል። በክልሉ በተመረጡ አካባቢዎች ከዐሥር በላይ የማሕበረሰብ ጥብቅ ሥፍራዎች እና ብሔራዊ ፓርኮችን በመጠበቅ ለትውልዱ ለማስተላለፍ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የደን ዘርፉ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት የተናገሩት አቶ በልስቲ ለዚህ ተግባር የሚውሉትን የደን አይነቶች መለየት እና ለአርሶ አደሮች የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል። ክልልሉ ከእርሻ እና እንስሳት እርባታ በተጨማሪ የደን ልማትን አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ አድርጎ እየሠራ መሆኑንም አስረድተዋል። ከውጭ ሀገር የሚገባን የደን ውጤትም በሀገር ውስጥ እንዲመረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ይህም የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ እና የሥራ ዕድል በመፍጠር ሚናው የላቀ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ከደን ውጤቶች እና ግብይት በየዓመቱ ከ200 ሚሊዮን በላይ ገቢ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ተግባራት መከናዎናቸውንም ተናግረዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም