አካባቢን ከጉስቁልና ለመታደግ …

0
67

እ.አ.አ በ2019 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአካባቢ ሕጎች ተፈፃሚነት ላይ ባደረገው ግምገማ አካባቢ ጥበቃን የተመለከቱ ሕጎች ካለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት ወዲህ በዓለማችን ላይ የተሻለ ዕድገት እንደታየባቸው አረጋግጧል። ይህም የማኅበረሰቡ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት፣ የጤና፣ የማኅበራዊ ትስስር እና ሁለንተናዊ ደህንነት ከሚኖርበት አካባቢ ጋር ያለው ቁርኝት ግንዛቤ ውስጥ የገባ መሆኑን አመላክቷል።

 

በሪፖርቱ መሠረት “176 ሀገሮች አካባቢ ጥበቃ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሕጎችን በማውጣት የተገበሩ ሲሆን እነዚህም ሕጎች የአካባቢ መጎሳቆልን ለመቀነስ የሚያስፈልጉ እና በተወሰነ ደረጃ ጉዳቱን ሊቀለብሱ የሚያስችሉ እንደነበሩ የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል። “ይሁን እንጂ ሕግን ማውጣት ብቻውን በቂ አይደለም።” ሲል ነው ያከለው።

በኢትዮጵያ እየተስፋፉ ያሉ ኢንዱስትሪዎች እና ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች በምርት ሂደት በሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች እና የምርቶች አያያዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድ ምክንያት የሚፈጠሩ ቆሻሻዎች በአግባቡ ተይዘው ካልተወገዱ አካባቢን ይበክላሉ፤ ይህም የሰውን ጤና ብሎም ምጣኔ ሀብቱን ክፉኛ ይጎዳል።

 

ከኢንዱስትሪዎች የሚመነጭ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻ ከምንጩ እንዲቀንስ ካልተደረገ ወይም በአግባቡ ካልተያዘ በአካባቢው የሚገኙ የውኃ አካላት፣ አፈር እና ካባቢ አየርን በቀላሉ ሊበክሉ እንደሚችሉ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጥር 2010 ዓ.ም ባሳተመው ዓመታዊ መጽሔቱ ላይ አስነብቧል።

መጽሔቱ አክሎም በኢትዮጵያ የሚገኙት የተወሰኑ ኢንዱስትሪዎች ብክለትን ለመቀነስ እና ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን ስለማያካሂዱ እና ያረጁ ማምረቻ መሳሪያዎች የሚጠቀሙ በመሆናቸው ያለምንም የማጣራት ሂደት ወደ አካባቢው በሚለቀቁ በካይ ንጥረ ነገሮች በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ማለትም በውኃ፣ በአፈር፣ በአየር፣ በሰዎች እና በእንስሳት  ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያስከተሉ እንደሚገኙ አስፍሯል።

 

የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ተፅዕኖ ኦዲት ባለሙያ አበበ ሞላ እንደተናገሩት ማኅበረሰቡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ከሚለው ብሂል ወጥቶ ተፈጥሮን በአግባቡ ጠብቆ እና ተንከባክቦ ለመጪው ትውልድ ምቹ ምድርን ማስተላለፍ ይጠበቅበታል። ምድርን ከብክለት በንቃት የሚጠብቅ ትውልድ እንዲፈጠር መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል። ባለሙያው ለበኩር ጋዜጣ እንዳብራሩት ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፤ የአካባቢ ብክለትን እና ብክነትን መቆጣጠር፣ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ፣ የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና ብክለት ማስወገድ ላይ የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ክትትል ማድረግ እንዲሁም የአካባቢ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ምርመራ ማድረግ የባለሥልጣኑ ግንባር ቀደም ተግባራት ናቸው። በተጨማሪም በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ይሠራልም ብለዋል።

 

የአካባቢ ብክለትን በመቆጣጠር በኩል እየተሠሩ ባሉ መልካም ሥራዎች የማኅበረሰቡ ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልፀዋል። እንደ አቶ አበበ ገለፃ ብክለት ማለት በመሬትም ሆነ በማንኛውም አካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርስ፣ በሰዎች ጤና ላይ ጠንቅ የሚያስከትል፣ በአኗኗር ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር ወይም በተፈጥሯዊ ሥነ ምሕዳር ላይ ለውጥ የሚያስከትል ችግር በሙሉ ብክለት (pollution) ነው።

የሰው ልጅ አይነተኛ ችግር ለህይወት ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን በአካባቢ ብክለት እና ብክነት ማጣት ነው፤ ይህም የሚከናወነው በዋናነት በሰው ልጅ የአካባቢ አያያዝ ችግር ሲሆን ሌላው ደግሞ  በተፈጥሮ በሚከሰቱ ክስተቶች ነው፡፡

 

ብክነት ሲባል የአካባቢ ሀብቶች፣ በተለይም የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግብቡ አለመያዝ እና አለመጠቀም ማለት ነው፡፡ ብክለት ደግሞ የአንድን አካባቢ (አፈር፣ ውኃ፣ አየር፣ ድምፅ …) ፊዚካላዊና ስነ ህይወታዊ ይዘቶችን ማጥፋት ወይም ማበላሸት ማለት ነው፡፡

ብክለት የተፈጥሮን ወይም ሰው ሠራሽ ሀብቶችን በመበከል በሰው፣ በእንስሳት፣ በእፅዋት እና በሌሎች ህይወታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ጉዳት ማድረስን ያጠቃልላል፡፡ በተለይ በሰው እና በእንስሳት ጤና እና ደህንነት፣ በእፅዋት፣ በአፈር፣ በአየር ንብረት፣ በአጠቃላይ ግዑዝ አካል እና ብዝኃ ህይወት ላይ ያልተፈለገ ውጤትን ያስከትላል፡፡

 

ማንኛውም ሰው የመኖሪያ ቤቱን ሲገነባ (ሲሠራ) የመፀዳጃ ቤቱን ታሳቢ አድርጎ እንደሚሠራ ሁሉ ትልልቅ ፋብሪካዎች እና ኢንዱስትሪዎች ሲገነቡ የፈሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቴክኖሎጂን (ሴፍቲ ታንከር) መጠቀም እንዳለበት አቶ አበበ አሳስበዋል።

የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በዋናነት የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ አመላክተዋል። የመገናኛ ብዙኃን በተገቢው መንገድ ብክለትን መከላከል ላይ ለማኅበረሰቡ መረጃ መስጠት፣ ማሳወቅ እና ማስተማር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል። ከዚህ አኳያ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) እየሠራቸው ያሉ ዘገባዎችን በአብነት አንስተው አመስግነዋል።

 

ሌላው ከግንዛቤ ፈጠራው ባሻገር ያነሱት ሃሳብ  በአካባቢ ጥበቃ ላይ የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ አስተዳድራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ነው። ለዚህ ደግሞ ጤና፣ ውኃ እና መሬት አስተዳደር ቢሮዎች እንዲሁም የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን እና ሌሎች ተቋማት በተቀናጀ መልኩ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

እንደ ባለሙያው ገለፃ ውኃ ከመኖሪያ ቤት፣ ከተቋማት፣ ከንግድ ድርጅቶች እና ከኢንዱስትሪዎች በሚወጡ (በሚለቀቁ) ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ይበከላል።

አቶ አበበ እንዳስገነዘቡት ያለ በቂ ጥናት የሚካሄድ የከተሞች መስፋፋት እና የኢንዱስትሪዎች ልማት  ወንዞችን እና ትናንሽ ጅረቶችን እንደ ፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ በመጠቀም የሚለቁት ቆሻሻ ሰዎችን ለውኃ ወለድ በሽታዎች ይዳርጋሉ። ለአብነትም ታይፎይድ፣ አሜባ፣ ጃርድያ እና ሌሎች በሽታዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ችግሩ ዜጎችን ለተጨማሪ ወጪ  (ለሕክምና እና መድኃኒት መግዣ) ያጋልጣል። ገቢያቸው እንዲያሽቆለቁል እና የሀገር ምጣኔ ሀብት ዕድገት እንዲጓተትም ያደርጋል። በመሆኑም አካባቢን በመጠበቅ “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚለውን ብሂል መተግበር ይገባል ብለዋል።

 

ሌላው በሐይቆች፣ በወንዞች እና በኩሬዎች የሚለቀቁ ቆሻሻዎች በብዝኃ ሕይወት ላይ አደጋ የደቀኑ ናቸው። በተለይም በሐይቆች የሚራቡ ብርቅዬ የሆኑ የዓሳ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ እንዲጋረጥባቸው ያደርጋል። በመሆኑም የቆሻሻ ማጣሪያ ቴክኖሎጂን እና ሌሎች መፍትሔዎችን መጠቀም እንደሚገባ ባለሙያው አመላክተዋል። ባለሙያው በአሁኑ ወቅት አካባቢያችን ከፍተኛ ቁጥር ባለው የፕላስቲክ ቆሻሻ እየተሞላ መሆኑን በማንሳት ይህም ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል ነው ያሉት። ችግሩ በዚህ ከቀጠለ የውኃ አካላት ጭምር በፕላስቲክ ቆሻሻ ክምችት ተበክለው የብዝኃ ሕይወት መቃወስ እንደሚገጥምም አስገንዝበዋል።

 

የክልሉ አካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን በተሰጠው አካባቢን የመጠበቅ ኃላፊነት መሰረት ዛሬን ሳይሆን ነገን ጭምር ታሳቢ በማድረግ ተፈጥሮን ምቹ የማድረግ ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል። ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን በየአካባቢው ከመጣል ይልቅ መልሶ የመጠቀም ልምድ እንዲያዳብር እያደረግን ነው ብለዋል። ይህም ቆሻሻን ወደ ሀብት በመቀየር የገቢ ምንጭ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ሌላው የአፈር ብክለት ነው፤ ብክለቱም ከኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ፍሳሾች እና የእርሻ ኬሚካሎች (ፀረ አረም እና ፀረ ተባይ) ኬሚካሎች እንዲሁም በአግባቡ የማይወገዱ ቆሻሻዎች አፈር ውስጥ ሲጨመሩ የሚከሰት እንደሆነ ባለሙያው አስረድተዋል። ይህም ምርትና ምርታማነትን በመቀነስ ለምጣኔ ሀብቱ ዕድገት እንቅፋት ይሆናል።

 

ከዚህ በተጨማሪም የአየር ብክለት ወደ ከባቢ አየር ውስጥ ከኢንዱስትሪ፣ ከተንቀሳቃሽ ሞተር እና በሌሎች አመካኝነት በካይ ጋዝ፣ ብናኝ እና ጭስ ሲገባ ብክለቱ ይፈጠራል፡፡ ይህም ለእፅዋት፣ ለእንስሳት እና ለሰው ልጅ ለመኖር አሰቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ችግሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሳሳቢ የጤና ጠንቅ መሆኑን በማንሳት ብዙ ነገሮችን እያሳጣን ነው ብለዋል።

በካይ ጋዞች በሰው ልጅ ላይ የሚያደርሱት ችግር የሳንባ እንቅስቃሴን ይቀንሳል፣ ዓይንን፣ አፍንጫን፣ ጉሮሮን፣ አፍን እና ሌሎች የመተንፈሻ አካሎችን በመጉዳት ለከፍተኛ ችግር ይዳርጋሉ።

 

ባለሙያው በመጨረሻም የመከላከያ መንገዶችን ዘርዝረዋል፤ ሁሉም ማኅበረሰብ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ ኃላፊነቱን መወጣት፣ የአካባቢ ብክለት እና ብክነትን በጋራ በመከላከል አካባቢን መጠበቅ፣ የወጡ ሕጎችን ተግባራዊ ማድረግ ባለሙያው የዘረዘሯቸው መፍትሔዎች ናቸው፡፡ ይህን በማድረግም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ አካባቢን መፍጠር እና ምጣኔ ሀብቱን  ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here