አካገራ ብሔራዊ ፓርክ

0
56

አካገራ ብሔራዊ ፓርክ በሩዋንዳ ነው የሚገኘው፡፡ ፓርኩ ሀገሪቱ በሰሜን ምሥራቅ ከታንዛኒያ በምትዋሰንበት ድንበር በ1934 እ.አ.አ ነው የተመሰረተው:: በ2010 እ.አ.አ የሩዋንዳ መንግሥት የአፍሪካ ፓርኮች አስተዳደር ከሀገሪቱ የልማት ቦርድ ጋር በመተባበር የፓርኩን ጥበቃ እና አስተዳደር በማሻሻል፣ የጐብኚዎችን ቆይታ በማራዘም ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት የሚኖረውን አበርክቶ ለማሳደግ ጥሪ አቅርቦ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባራትን ከውኗል::

አካገራ ብሔራዊ ፓርክ ስፋቱ 2500 ስኩዌር ኪሎሜትር ተለክቷል፡፡ በመልካም  ድራዊ  አቀማመጡም   የሳር ምድር፣ ሰንሰለታማ ተራራዎች፣ ረግረጋማ እና በደን የተሸፈኑ ቀጣናዎችን አካቶ ይዟል:: ፓርኩ መጠሪያውን ያገኘው በቀጣናው ከሚፈሰው አካገራ ወንዝ ነው፡፡ ሀገሪቱ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ከፍተኛ አደጋ ደርሶበታል፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የፓርኩ ክልል ከፊሉ በሰፋሪዎች ተይዞበት ነበርና ነው:: የፓርኩ አስተዳደር በ2015 እ.አ.አ ሰባት አንበሳዎችን በ2017 እ.አ.አ 20 ጥቁር አውራሪሶችን በቀጣናው እንዲጠለሉ አድርጓል:: በፓርኩ ከዱር አራዊት በአካል ግዝፈት ያላቸው አንበሳ፣ ዝሆን፣ አውራሪስ፣ አቦ ሸማኔ፣ ቀጭኔ፣ ጐሽ፣ የሜዳ ፍየል እና የሜዳ አህያ ተጠልለው ይገኛሉ:: ከእፅዋት 500 ዝርያዎች  እንደሚገኙም ተመዝግቧል- በፓርኩ፡፡

ግራር በሚበዛው ሳር ለበስ ሜዳ ከ550 በላይ የዓዕዋፍ ዝርያዎች  እንደሚገኙ ነው በድረገፆች የሰፈረው:: አካገራ ብሔራዊ ፓርክ ምእራባዊ ቀጣናው ከ1600 እስከ 1800 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ምሥራቃዊው ቀጣና ደግሞ ሰፊ ረግረጋማ ቦታዎችን አቅፏል፡፡ በዚሁ ቀጣና የሚገኘው ካጌራ ወንዝ በቀጣናው ያሉ ኃይቆችን እና ረግረጋማ ሜዳዎችን ያረሰርሳል -የምንጮች መነሻ ሆኖም ያገለግላል::

አካገራ ብሔራዊ ፓርክ ለመድረስ  ከሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓት በተሽከርካሪ መጓዝን ብቻ ነው የሚጠየቅው፡፡ በፓርኩ ቀጣና ውስጥ ለውስጥ ተንቀሳቅሶ ለመጐብኘት ከፊል ክፍት ባለ አራት ጐማ ተሽከርካሪ መያዝን ግድ ይላል::  ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት አፍሪካን ፓርክስ ዶት ኦርግ፣ ጆርኒ ባይዲዛይን እና ሩዋንዳ ፓርክስ ድረገፆችን ተጠቅመናል::

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም 19 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here