አወዛጋቢዉ የጋዛ ጉዳይ

0
123

በአውሮፓዊያኑ ጥቅምት 7 ቀን 2023 ሐማስ  በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በእራኤል እና ሃማስ መካከል ጦርነት ማገርሸቱ ይታወሳል፤ ይህን ተከትሎ አሜሪካ እስራኤልን እየደገፈች ትገኛለች። አሜሪካ የጦር መርከቦችንና ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ወደ ምሥራቅ ሜዲትራኒያን ባሕር በመላክ እስራኤል ተጨማሪ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን እንድታገኝ እያደረገች ነው::

ከሰሞኑም የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ታግተው የሚገኙ እስራኤላዊያን በሙሉ እንዲፈቱና የሃማስ መሪዎች የጋዛ ሰርጥን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቀዋል:: እ.አ.አ ከ1997 በኋላ አሜሪካና ሃማስ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ መነጋገራቸውን ዋይት ሀውስ አረጋግጧል። ይሁንና አሜሪካ በአሸባሪነት ከዘረዘረቻቸው ቡድኖች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳትፈጥር የሚከለክል ፖሊሲ እንዳላት ቢቢሲ ዘግቧል::

ትራምፕ በቅርቡ በተኩስ አቁሙ ከተፈቱ ታጋቾች ጋር በዋይት ሀውስ ከተገናኙ በኋላ ሃማስ ያገታቸውን  እንዲለቅ  ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል:: ቀደም ሲል የፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸውን በታኅሣሥ ወር በተረከቡበት ወቅት ሃማስ ያገታቸውን ሁሉ ካልለቀቃቸው የሚከፍለው ዋጋ የከፋ እንደሚሆን አሳውቀው ነበር:: እስራኤል አሁንም በጋዛ 59 ታጋቾች እንደሚገኙና 24 የሚደርሱት ታጋቾች በሕይወት እንደሚገኙ ተናግራለች። ከታጋቾቹ መካከልም የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው እንደሚገኙበት መጠቆሙን ቢቢሲ ዘግቧል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ  አሜሪካና እስራኤል ከጦርነቱ  በኋላ ግብጽ  ያዘጋጀችውንና  የአረብ ሊግ ሀገራት ያጸደቁትን  የጋዛ ሰርጥ መልሶ ግንባታ ፕሮግራም ውድቅ አድርገውታል:: አሜሪካ  ግብጽ ያዘጋጀችው ዕቅድ “ጋዛ በአሁኑ ጊዜ ለመኖሪያነት አመቺ አለመሆኗን እንዲሁም ነዋሪዎቿ በፍርስራሾች እና ባልፈነዱ  ፈንጂዎች ውስጥ መኖር አይችሉም የሚለውን እውነታ  አልተመለከተም”  ብሏል።

የፍልስጤም ባለሥልጣናትና ሃማስም በጋዛ በጊዜያዊነት ገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲሰማሩ የሚጠይቀውን የአረብ ሀገራትን ዕቅድ ተቀብለዋል:: የግብጽ ዕቅድ  ሁለት ነጥብ አንድ  ሚሊዮን ፍልስጤማዊያን በጋዛ እንዲቆዩ ያስችላቸዋል።

የአረቡ ዓለም ግብጽ ያቀረበችውን የጋዛ ዕቅድ ማጽደቁንና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብና የፋይናንስ ተቋማት በፍጥነት እንዲደግፉት ጥሪ አቅርቧል።

ቀደም ሲል የአሜሪካዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ  ̋ጋዛን የመካከለኛዉ ምሥራቅ ውብ ቦታ አደርጋለሁ” በማለታቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ከአረብ ሀገራት አስተናግደዋል:: ፕሬዝደንት ትራምፕ ግብጽና ጆርዳን በጦርነት የወደመችው ጋዛ እስከምትጸዳና መልሳ እስከምትገነባ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማዊያንን እንዲያስጠልሏቸው ጫና ሲያደርጉም ሰንብተዋል። በግብጽ በኩል የተዘጋጀው ዕቅድ ታዲያ የትራምፕን ሀሳብ የሚገዳደር ነው::

53 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልገው ዕቅዱ (በግብጽ የቀረበው) ጋዛን በአምስት ዓመታት ውስጥ መልሶ ለመገንባት ያስችላል:: በዕቅዱ መሠረትም የመጀመሪያዉ ስድስት ወራት የማገገሚያ ምዕራፍ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን በዚህም የጽዳት ሥራ ይከናወንበታል:: በሦስት ቢሊዮን ዶላር ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶች ይገነቡበታል:: በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ሁለት መቶ ሺህ መኖሪያ ቤቶች ይገነባሉ:: እ.አ.አ በ2030 ለሦስት ሚሊዮን ሰዎች   አዳዲስ የቤቶች ግንባታ፣ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ ሆቴሎች እና መናፈሻ ፓርኮች ግንባታዎች ይከናወናሉ:: ጋዛም መልሳ ትሠራለች::

በሌላ በኩል ከአንድ ወር በላይ የዘለቀውን የጋዛውን የተኩስ አቁም የመጀመሪያ ምዕራፍ መጠናቀቁን ተከትሎ የተኩስ አቁሙን ለማራዘም በግብጽ ተደርጎ የነበረው ስብሰባ ያለስምምነት ተጠናቋል::

በመጀመሪያዉ የተኩስ አቁም ስምምነት 33 እስራኤላዊያን ታጋቾችና አምስት የታይላንድ ዜጎች ሲለቀቁ ወደ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማዊያን እስረኞችም ተፈትተዋል:: በአሜሪካ የቀረበው የጋዛ የተኩስ አቁም አንደኛ ምዕራፍ የማራዘም ሃሳብን ሃማስ አልተቀበለም:: ታጣቂ ቡድኑ እስራኤል በፍጥነት ወደ ሁለተኛዉ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ድርድር እንድትገባ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጫና እንዲያሳድርባት ጠይቋል። ይሁንና የእስራኤል ባለሥልጣናት ከዚህ ቀደም እስራኤል ቀሪ ታጋቾቿ ካልተመለሱ በጋዛ ጦርነቱን እንደምትቀጥል አሳውቃ ነበር::

የተኩስ አቁሙ አለመቀጠሉ ጋር ተያይዞ  እስራኤል ወደ ጋዛ የሚገባን ማንኛውንም ተሽከርካሪ ከልክላለች:: ይህን ተከትሎ ፍልስጤማዊያን ለከፍተኛ ዋጋ ጭማሪና ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል:: የዓለም የምግብ ፕሮግራም በጋዛ ያለው ምግብ ከሁለት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሊያልቅ እንደሚችልም አስጠንቅቋል።

አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው የእስራኤል የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድኃኒት እና ሌሎች አቅርቦቶችን ሁለት ሚሊዮን ለሚሆነው የጋዛ ሕዝብ ማቋረጧ የዋጋ ንረትንና የሰብአዊ ቀውስን ያባብሳል:: ዕርዳታ መቆሙ የረድኤት ሠራተኞቹ ላለፉት ስድስት ሳምንታት እስራኤል እና ሃማስ በጥር ወር በተስማሙት በምዕራፍ አንድ የተኩስ አቁም ስምምነት ረሃብን ለመታደግ የሠሩትን ሥራ የሚያጨናግፍ ነው::

እንደሚታወቀው ከ 16 ወራት በላይ ከዘለቀው ጦርነት በኋላ የጋዛ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ምግቡንም ሆነ ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን የሚያገኘው በእርዳታ ነው:: አብዛኞቹ ከመኖሪያ ቤታቸው በመፈናቀላቸው መጠለያ ያስፈልጋቸዋል። ሆስፒታሎችን፣ የውኃ መሳቢያዎችን፣ ዳቦ መጋገሪያዎችን እና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች እንዲሁም እርዳታ የሚያደርሱ የጭነት መኪናዎች እንዲሠሩ ለማድረግ ነዳጅ ያስፈልጋል።

እስራኤል የክልከላው ዓላማ ሃማስ የተኩስ አቁም ሃሳቡን እንዲቀበል ግፊት ለማድረግ ነው ትላለች። እስራኤል ይህን ትበል እንጂ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል በጦርነት በወደመችው ጋዛ ማንኛውም ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ መከልከሏን አውግዟል::

የዓለም ምግብ  ፕሮግራም በጋዛ ምንም አይነት የምግብ ክምችት እንደሌለው ነው ያስታወቀው::

በመሆኑም  በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን ለመድረስ  ሲል ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረውን የሰብዓዊ አቅርቦት መጠን ለመቀነስ ሊገደድ እንደሚችል አስታውቋል። ዳቦ ቤቶችን ለማስኬድ እና ምግብ ለማጓጓዝ አስፈላጊ የሆነው የነዳጅ ክምችቱ በቅርቡ ካልሞላ ለጥቂት ሳምንታት ብቻ እንደሚቆይ ነው ያስታወቀው:: የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት የኮሙኒኬሽን አማካሪ የሆኑት ሻይና ሎው እንዳሉት በጋዛ ውስጥ ምንም አይነት ትልቅ የቁሳቁስ የድንኳን ክምችት የለም። “በተኩስ አቁም የመጀመርያዉ ምዕራፍ ውስጥ የገቡት የመጠለያ ቁሶች ሁሉንም ፍላጎቶች ለማሟላት በቂ ቦታ አልነበራቸውም” ስትል ተናግራለች። የመጠለያ ቁሶች፣ ሙቀት የሚለግሱ ልብሶች እና ተገቢ የሕክምና መሣሪያዎች ባለመኖራቸው ምክንያት   ሕፃናት ለሞት መዳረጋቸውንም አማካሪዋ ተናግራለች::

በተኩስ አቁም የመጀመሪያዉ ምዕራፍ በሰብአዊ ኤጀንሲዎች በአማካይ በቀን 600 ያህል የጭነት መኪናዎች ወደ ጋዛ ይገቡ ነበር። የእርዳታ ሠራተኞች ተጨማሪ የምግብ ኩሽናዎችን፣ የጤና ጣቢያዎችን እና የውኃ ማከፋፈያ ቦታዎችን አቋቁመዋል። ተጨማሪ ነዳጅ ወደ ውስጥ ሲገባ ከጉድጓድ የሚሰበሰበውን የውኃ መጠን በእጥፍ ሊጨምሩ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ኤጀንሲ ገልጿል።

በሃማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው እስራኤል በጋዛ ላይ በፈጸመችው ድብደባ 48 ሺህ 440 ፍልስጤማዊያን ሲገደሉ  111 ሺህ 845 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል። በሌላ በኩል በሃማስ መሪነት በእስራኤል በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ አንድ ሺህ 200 ያህል እስራኤላዊያን ሲሞቱ አምስት ሺህ 431 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል::

(ሳባ ሙሉጌታ )

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here