አወዛጋቢው ህንፃ

0
114

በኢኳዶር – ማቻላ በተሰኘች ከተማ ማእከላዊ ስፍራ በጠባብ ምድር ቤት ላይ ግራ እና ቀኝ  የተገነባው ባለ አራት ፎቅ ህንፃ ባልተለመደ አሰራሩ በተመልካች “ይፈርሳል” በመባሉ  ውዝግብ ማስነሳቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

በማቻላ ከተማ ቦኒቪስታ እና ፒቺንቻ ጐዳናዎች መካከል የተገነባው “የማይፈርሰው” በሚል ስያሜ የሚጠራው ህንፃ ላለፉት 30 ዓመታት ርዕደ መሬትን ተቁቁሞ መዝለቅ ችሏል፡፡ በከተማዋ በ2023 እ.አ.አ በሬክተር ስኬል ስድስት ነጥብ አምስት ዲግሪ በተለካው  ርእደ መሬት የደረሰበት ጉዳትም ኢምንት የሚባል እንደነበረ ተገልጿል፡፡

ህንፃው ከመሰረቱ እስከ አምስት ሜትር ከፍታ ከጐን እና ከፊት ለፊቱ ቋሚ ወይም ምሰሶ ሳይኖረው ተገንብቶ ከላይ መስፋቱ ወደፊት ተደፍቶ ሊደረመስ ይችላል የሚል ስጋት አሳድሯል፤ በአላፊ አግዳሚ ኗሪዎች፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚናፈሱ ስጋቶችን እና ቅሬታዎችን የሰሙት የህንፃው ባለቤት ዌልያም ምሳንቼዝም የሚነዙት ቅሬታዎች እና ስጋቶች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡  ባለሀብቱ የሰሙትን ቅሬታ እና ውዝግብ መነሻ አድርገው ወደ ህንፃ ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤት አምርተው የህንፃው ጥንካሬ በባለሙያ እንዲረጋገጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከተገኘው ውጤት ባለንብረቱ መሰረቱ ጥልቅ እና ጠንካራ መሆኑን ማረጋገጫ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በከተማዋ በደረሱት ርእደ መሬቶች ፍንክች አለማለቱ፣ ጠንካራ መሰረት ላይ ለመሰራቱ አብነት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ባለንብረቱ ህንፃው ከታች ቀጥኖ ከላይ መስፋቱን አምነው  ልምድ ባለው መሀንዲስ ታምኖበት እና  የተነሳው ስጋት መሰረተ ቢስ መሆኑ በባለሙያዎች ተፈትሾ መረጋገጡን አስምረውበታል፡፡

ባለንብረቱ ላለፉት 30 ዓመታት ፍንክች ያላለው ህንፃቸው ሲያዩት ያልተለመደ ቢመስልም በአንደኛ እና ሁለተኛ ፎቆች ላይ የንግድ፣ ሶስተኛ እና አራተኛ ፎቶች ላይ መኖሪያ ክፍሎችን ይዞ መዝለቁን ነው ያሰመሩበት፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የጥር 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here