በአራቱም የዓለም ማዕዘን የሚገኙ ታላላቅ የእግር ኳስ ክለቦች ይፋለሙበታል። ይሁን እንጂ ታላቁ የክለቦች መድረክ፤ በክለብ ባለቤቶች፣ በእግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር አስተዳደር እና በተጫዋቾች ማህበር አልተወደደም- የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ። የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ በዓለም ዋንጫ ቅርጽ እየተከናወነ ያለ ግዙፍ የክለቦች ውድድር ነው።
ውድድሩ የተጀመረው ከ24 ዓመታት በፊት በፈረንጆች ሚሊኒየም ነው። የፊፋ የዓለም ዋንጫ መጀመርን ተከትሎም እ.አ.አ 1960 እስከ 2004 ሲደረግ የነበረው አህጉራዊ ( ኢንተር ኮንትኔታል) ዋንጫ ተሰርዟል። በምትኩ እየተደረገ ያለው የፊፋ የዓለም ዋንጫም በወጥነት በሰባት ክለቦች መካከል ሲደረግ ቆይቷል።
የፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ቀስ በቀስ እንዲያድግ እና በየአራት ዓመቱ እንዲከናወን በ2016 እ.አ.አ ውሳኔ አስተላልፈው እንደነበር አይዘነጋም። በ2021ዱ መድረክም 24 ክለቦች መካከል መደረጉ የሚታወስ ነው። ታዲያ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ደግሞ በ32 ክለቦች መካከል የሚደረግ ይሆናል።
በዘንድሮው መድረክ ከስድስት አህጉራት የተውጣጡ ኃያላን ክለቦች ይሳተፋሉ። ከአውሮፓ 12፣ ከደቡብ አሜሪካ ስድስት፣ ከእስያ፣ አፍሪካ፣ ከሰሜን መካከለኛው አሜሪካ እና ከካሪቢያን ደግሞ አራት ክለቦች የሚሳተፉ ይሆናል። ከኦሺኒያ ደግሞ አንድ ክለብ ይካፈላል። ሁሉም ተሳታፊ ክለቦች በቅርቡ ተለይተው ታውቀዋል።
ከ2021 እስከ 2024 እ.አ.አ ባሉት ዓመታት ውስጥ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ኢሮፓ ሊግ ፣የኮፓሌበርታዶሬስ እና የአህጉራዊ ክለቦች ውድድር አሸናፊዎች ናቸው በውድድሩ የሚካፈሉት። 32ቱ ተሳታፊ ክለቦች በስምንት ምድብ ተደልድለው ጨዋታዎችን ያደርጋሉ። ከምድቡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የሚጨርሱ ክለቦች ቀጣዩን ዙር የሚቀላቀሉ ይሆናል። ከ33 ሀገራት የተውጣጡ 32 ክለቦችም በዚህ የውድድር ቅርጽ እንደሚፋለሙ የኤስፔን መረጃ ያመለክታል።
ውድድሩም በአሜሪካ የሚደረግ ሲሆን በ11 ከተሞች ይደረጋል። ውድድሩን ሳቢ እና ማራኪ ለማድረግ የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር መጨመሩ ለወትሮ ውድድሩ በማይዋጥላቸው በክለብ ባለቤቶች እና በተጫዋቾች ማህበር ተቃውሞ ገጥሞታል። የፊፋ የክለቦች የዓለም ዋንጫ በተጫዋቾች ላይ አዕምሯዊ እና አካላዊ ጫና ያደርሳል በሚል እየተኮነነ ይገኛል። ለአብነት በዘንድሮው የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ የሚሳተፈው ማንቸስተር ሲቲ እስከ ውድድሩ ፍጻሜ የሚቆይ ከሆነ በውድድር ዘመኑ 75 ጨዋታዎችን ለማድረግ ይገደዳል። ይህም በተጫዋቾ ላይ ከፍተኛ ድካም ይፈጥራል።
የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ውድድር ሀምሌ 13 የሚጠናቀቅ በመሆኑ በ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቅድመ ዝግጅት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ይህ ብቻ ሳይሆን ወቅቱ በሀገር ውስጥ በርካታ ውድድሮች የሚደረጉበት፣ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮችም የሚከናወኑበት ጊዜ በመሆኑ ውድድሩ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያጣ ይገኛል።
የላሊጋው ፕሬዝደንት ዣቬር ቴባስ ውድድሩ እንዲሰረዝ በይፋ የዓለም አቀፉን የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ጠይቀዋል። ፕሬዝዳንት ቴባስ ከ37 ሊጎች የተውጣጡት የዓለም አቀፉ የተጫዋቾች ማህበር (FIFA PRO) ጭምር እንደማይፈልጉት አስረድቷል። በመድረኩ የተሳታፊ ክለቦች ቁጥር መጨመራቸው ደግሞ በክለቦች ውድድር ታሪክ ረዥሙ ውድድር ይሆናል ብለዋል- የላሊጋው አለቃ።
የላሊጋው ፕሬዝደንት የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ የተጫዋቾችን መብት እየተጋፋ መሆኑንም ገልጸዋል። “ተጫዋቾች አካላዊ እና አዕምሯዊ እረፍት እንዳያደርጉ ያደርጋል ብሏል”። በክረምቱ የዝውውር ወቅት ተጫዋቾች ከአንድ ክለብ ወደ ሌላ ክለብ የሚዘዋወሩበት በመሆኑ ዝውውሩ ላይ እንቅፋት ይፈጥራል። አውሮፓ ውስጥ ደግሞ የተጫዋቾች ውል የሚጠናቀቀው ሰኔ 30 በመሆኑ በውድድሩ ላይ የሚካፈሉ ተጫዋቾች እንዳይረጋጉ እና ትኩረታቸው እንዲበተን ያደርጋል።
እንደ ኤስፔን መረጃ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ ጠባቂ (ፊፋ) በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት እና የገንዘብ ድጎማም የሚያገኙበት በመሆኑ ከአሉታዊ ጎኑ ይልቅ አውንታዊ ጎኑ ያመዝናል ባይ ነው። በውድድሩ አንድ ክለብ ከሰባት ጨዋታዎች በላይ ሊያደርግ እንደማይችል በመግለጽ ያን ያህል ተጽዕኖ እንዳማያደርስም ያትታል።
ከዚህ በፊት ስፖንሰር በማጣት እና የቀጥታ ስርጭት አስተላላፊ የቴሌቭዥን ባለመብቶችን ባለማግኝት ብዙ የተፈተነው ውድድሩ ዘንድሮም እስካሁን ውል አለመፈራረሙ ተዘግቧል። የቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት አስተላላፊዎች በአሜሪካ፣ እስያ እና መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ተቋም የጨረታ ግብዣ ቢያቀርብም ስምምነት ላይ ግን መድረስ አልቻለም። የፊፋን ገንዘብ እንዳይጠቀም ደግሞ ከወዲሁ ትችት እየቀረበበት ነው።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ግን ከዚህ ውድድር ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በላይ ትርፍ ለማግኝት እየሠራ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል። በውድድሩ ለሚሳተፉ እና ዋንጫውን ለሚያሸንፈው ቡድን ዳጎስ ያለ ሸልማት ማዘጋጀቱ ተነግሯል። ደረጃ ውስጥ ገብተው ለሚያጠናቅቁት ክለቦች እያንዳንዳቸው ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ይበረከትላቸዋል። ሪያል ማድሪድ ባለፈው ዓመት ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሽልማት 131 ሚልዮን ዶላር ገንዘብ ወደ ካዝናው አስገብቷል።
የዘንድሮውን የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ የሚያሸንፍ ቡድን ግን ይህን ገንዘብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያገኝ ይሆናል። ይሁን እንጂ ፔፕ ጓርዲዮላ እና ካርሎ አንቸሎቲን የመሳሰሉት ታላላቅ አሰልጣኞች የውድድሩ መልካም ጎን አልታያቸው ብሎ ስጋት ገብቷቸዋል። ውድድሩ እንደማይሰረዝ በአቋሙ የጸናው ፊፋ ከሰኔ 15 እስከ ሀምሌ 13 ቀን 2025 እ.አ.አ ለማከናወን መረሀግብር አውጥቷል።
የ2023ቱን የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ማንቸስተር ሲቲ ማንሳቱ የሚታወስ ነው። ሪያል ማድሪድ በፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ በደረሰባቸው ሁሉም ጨዋታዎች ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ክለብ ነው። አምስት ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ባለክብረወሰን ክለብ ነው- ሪያል ማድሪድ። ሌላኛው የስፔኑ ኃያል ክለብ ባርሴሎና ደግሞ ሦስት ጊዜ ዋንጫ አሳክቷል። የብራዚሉ ኮረንቲያስ እና ባየርሙኒክ እኩል ሁለት ጊዜ አንስተዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም