አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ

0
140

አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ከስምጥ ሸለቆ ሰሜናዊ ቀጣና በኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ፓርኩ የተመሰረተው በ1958 ዓ.ም ሲሆን ስያሜውን ያገኘው በውስጡ ከሚፈሰው  የአዋሽ ወንዝ ነው፡፡

ፓርኩ ከአዲስ አበባ 225 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተካለለ ሲሆን ጠቅላላ ስፋቱም 756 ኪሎ  ሜትር ስኩዌር ተለክቷል፡፡

መልካ ምድራዊ አቀማመጡ ዝቅተኛው 700 ከፍተኛው 2000 ሜትር ተለክቷል፡፡ የአዋሽ ወንዝ ለመጓጓዣነት የፈጠረው ሸለቆ፣ የኢላላ ሜዳ እና ፍል ውኃዎች ተጠቃሽ ገፅታዎች ናቸው- ለፓርኩ፡፡ የፓርኩ ቀጣናም ከፊል በረሀማ ነው፡፡ የግራር ዛፍ እና ቁጥቋጦዎች የሚገኙበት  የተንጣለለ የሳር ምድርንም አካቷል፡፡

በፓርኩ ክልል 460 የዓዕዋፍ ዝርያዎች እንደሚገኙ ተመዝግቧል፡፡ ከዱር እንስሳት የ81 አጥቢ ዝርያዎች መገኛ ሲሆን ከነዚሁ መካከል ሳላ፣ ዝንጀሮ፣ የሜዳ ፍየል፣ አቦሸማኔ፣ የሜዳ አህያ፣ ጦጣ እና ቀበሮ ይጠቀሳሉ፡፡ የአዋሽ ወንዝ መውረጃ ዳርቻው ደግሞ የአዞዎች መገኛ ነው፡፡ በተጨማሪም 43 የሚደርሱ በወንዙ እና ዳርቻው የሚኖሩ እንስሳት መጠለያነቱን ድረ ገፆች አስፍረዋል፡፡

በቀጣናው ከሚገኙ ኗሪዎች የአፋሮች የአኗኗር ዘይቤ ጠንካራ፣ ራስ ቻይ ሲሆን የዳጉ ባህላቸው ደግሞ ከሁሉም የላቀ መሆኑን የድረ ገጽ ጽሁፎች አመላክተዋል፡፡ ለፓርኩ ስጋት ከሆኑት መካከል ለማገዶ እና ከሰል- የደን መመንጠር፣ ልቅ ግጦሽ፣ የእርሻ መሬት መስፋፋት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የፓርኩ ማእከላዊ ቀጣና 250 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የበላይ ጠባቂነት ነው የሚተዳደረው፡፡ ይህ በመሆኑም የዱር አራዊቱ እና እፅዋቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ ማስቻሉ በማጠቃለያነት ለንባብ በቅቷል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ኢትዮጵያን ቱር አሶሴሽን፣ ዋይልድ ላይፍ ወርልድ ዋይድ እና ሎንሊ ኘላኔት ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታህሣስ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here