አዋኪዉ

0
120

በሩሲያ ቮልጎግራድ ከተማ በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ህንፃ የራሱን ድርሻ ገዝቶ በአንድ ክፍል ይኖር የነበረ ጐልማሳ ከአንድ ዓመት ወዲህ  ጐረቤት የሚያውክ ሙዚቃ እና አስፈሪ የእንስሳት ጩኽትን በድምፅ ማጉያ በመልቀቅ  በማሸበር ላይ መሆኑን  ኦዲቲ ሴንትራል ድረገ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቷል፡፡

ማክሲም የተሰኘው ግለሰብ በአስፈሪ ድምፅ ጐረቤቱን ማሸበር የጀመረው ከአለፈው ዓመት የካቲት 5,2024 እ.አ.አ ጀምሮ መሆኑን ያስነበበው ጽሁፉ  የ “2”ኤ” ክፍል ኗሪው ከጧት እስከ ማታ በሚያሰማው የድምፅ ብክለት መቸገራቸውን ለፀጥታ ኃይል ቢያመለክቱም መፍትሄ አለማግኘታቸውን ነው ያስታወቁት- የጋራ መኖሪያ ህንፃ ኗሪዎች፡፡

ግለሰቡ የሀገር ፍቅር ዘፈኖች፣ የውሻ ጩኽት የመሳሰሉትን በከፍተኛ የድምፅ መጠን እንደሚለቅ ለፓሊስ ካመለከቱት መካከል የ46 ዓመቷ ስቬትላና ኩችሚና አንዷ ናቸው፡፡ ኗሪዋ የግለሰቡ ሁከት የመፍጠር ምክንያቱ ሌላ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

ኗሪዋ ስቬትላና ከአንድ ዓመት በፊት ጐልማሳው ወደ እርሳቸው ቀርቦ በጋራ መኖሪያ ህንፃው የያዙትን ድርሻ እንዲሸጡለት እና የራሱ ማድረግ እንደሚፈልግ የጠየቃቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኗሪዋ ድርሻቸውን ሸጠው ቤተሰባቸውን ይዘው የትም መሄድ እንደማይፈልጉ እና እንደማያደርጉት ደግመው ሲነግሩት በሁከት አስመርሮ ኑሯቸውን ሲኦል እንደሚያደርግባቸው ዝቶ መሄዱን አስረድተዋል፡፡

ኗሪዋ በተደጋጋሚ ለፓሊስ በፃፉት ሁከት ይወገድልኝ ማመልከቻ መፍትሄ አለማግኘታቸውንም ነው የገለጹት፡፡ ግለሰቡ ማክሲም ሲሻው በክፍሉ በር ላይ ድምፅ ማጉያውን ሰቅሎ በርቀት መቆጣጠሪያ (ሪሞት ኮንትሮል) ማጫዎቻውን እየቀያየረ እንዳማረራቸው አልሸሸጉም፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤት ጐረቤቷ ስቬትላና ከእለታት አንድ ቀን ተሸሽገው የኤሌክትሪክ መስመሩን ኃይል ቢያቋርጡበትም ከፀሀይ ኃይል መሰብሰቢያ  ንጣፍ ጋር አገናኝቶ ማወኩን የገፉበት መሆኑን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

ከሩሲያ የዜና አውታሮች አንዱ ግለሰቡን ማለትም ማክሲምን አፈላልጐ በአደረገለት ቃለ መጠይቅ ብዙ ጊዜ ወደ ራሱ ክፍል ሲገባ የጐረቤቱ ውሻ እየጨኽ ስለሚረብሸው ለመበቀል መፈፀሙን ነው የተናገረው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመጋቢት 15 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here