ይህ የእግር ኳስ ፍልስፍና ስፔናዊው ታክቲሺያን እንደሚከተለው ፖዚሽናል ፕሌይ ዐይነት አጨዋወት አይደለም። በተጋጣሚ ብልጫ በመውሰድ እና ተቃራኒ ቡድንን በመውረር ግብ የማስቆጠር ሂደትም አይደለም። እንደ ጀርመናዊው አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በመልሶ ማጥቃት ተጋጣሚ ቡድንን በመውረር ትንፋሽ የማሳጣት ገገን ፕሬሲንግ ፍልስፍናም አይደለም። ይልቁንስ ወደ ኋላ አፈግፍጎ በመጫወት ከክንፍ መስመር ተጫዋቾች ይልቅ የመሀል አማካዮች አስፍተው የሚጫወቱበት እንደሆነ የጎል ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል።
አውቶቡሱን ማቆም (Parking the bus) ወይም ጥብቅ መከላከል አንድ ቡድን ወደ ኋላ አፈግፍጎ የሚጫወትበት የእግር ኳስ ፍልስፍና ነው። ጠንካራ መከላከል(Ultra defensive) ስልት ነው፤ ሙሉ ቡድኑ ትኩረቱ ግብ እንዳይቆጠርበት መከላከል ነው። አውቶቡሱን ማቆም ተቃራኒ ቡድን ወደ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ሰብሮ የሚገባበትን ክፍተት መድፈን ነው። አጥቂዎችም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ግብ የሚያስቆጥሩበት የቆየ የእግር ኳስ ፍልስፍና ነው። የአውቶቡስ ማቆም ሜዳ ላይ አሰላለፍ 4-4-2 ወይም 4-1-4-1 ዐይነት ነው። ይህ የእግር ኳስ ፍልስፍና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ እና ዲያጎ ሲሞኒ ጋር የተያያዘ ነው።
ይህን የእግር ኳስ ፍልስፍና ብዙ ባለሙያዎች ፀረ እግር ኳስ ነው ይሉታል። ፍልስፍናው በጣም አሰልቺ የእግር ኳስ አስተሳሰብ ይሁን እንጂ ሜዳ ውስጥ ተጋጣሚን አሸንፎ ውጤታማ ለመሆን ግን ትልቅ መሳሪያ እንደሆነ ታላላቅ አሰልጣኞች ይመሰክሩለታል። ለዚህም ነው የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን “ጨዋታን ለማሸነፍ ማጥቃት፤ ሻምፒዮን ለመሆን ግን መከላከል” ሲሉ የተናገሩት።
እግር ኳስ ሁሌም የታክቲክ ጨዋታ ቢሆንም እንደ አውቶቡሱን ማቆም ያሉ ጥቂት የእግር ኳስ አቀራረቦች ወይም ፍልስፍናዎች ግን ውዝግብ እና ክርክር አስነስተዋል። በዓለም እግር ኳስ ታሪክ በዚህ ፍልስፍና የተካኑ በረካታ ስመጥር አሰልጣኞች አሉ። በጥልቀት የመከላከል የእግር ኳስ ታክቲክ በፈረንጆች ሚሊኒዬም ድጋሚ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር የጊቭ ሚ ስፖርት መረጃ ያመለክታል። አውቶቡሱን የማቆሚያ ጥበብ በወቅቱ በርካታ አሰልጣኞችን ውጤታማ አድርጓል፤ የአሰልጣኝነት ህይወታቸውንም ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋግሯል።
ይህ ፍልስፍና በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም ሳም አላርዳይስ እና ቶኒ ፑሊስን የመሳሰሉ አሰልጣኞችም ተግባራዊ ሲያደርጉት ነበር። በርካታ የአውሮፓ አሰልጣኞች በጥብቅ የመከላከል ስልት ውጤታማ ሆነዋል፤ አሁንም እየሆኑ ነው። በዓለም ላይ በዚህ የእግር ኳስ ፍልስፍና በስፋት ከሚታወቁት አሰልጣኞች መካከል ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ አንዱ ናቸው። አወዛጋቢው አሰልጣኝ በዓለም ላይ በጥብቅ የመከላከል ስልት የሚታወቁ ቀዳሚ ሰው ናቸው። አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ በ2003/4 እ.አ.አ ፖርቶን ይዘው በጥብቅ መከላከል ኢንተርሚላንን በመርታት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን በማሸነፍ ስማቸው ናኝቷል።
አውቶቡሱን በማቆም የሚታወቁቱ ሞሪንሆ በወቅቱ ራሳቸውን “ልዩ ሰው”(The special one) ብለው የጠሩበት ዘመንም ነው። ስታንፎርድ ብሪጅ ከደረሱ በኋላ በ2004 እ.አ.አ በፕሪሚየር ሊጉ ከቶትናሀም ሆትስፐርስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በአጨዋወታቸው በእንግሊዝ ጋዜጦች ክፉኛ ሲብጠለጠሉ እንደነበረ የሚታወስ ነው። አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ ግን በዚህ የእግር ኳስ ታክቲክ ከፊታቸው የሚቆም ቡድን እንደማይኖር ደጋግሞው ተናግረዋል። “ሁሌም እንደምለው አውቶቡሱን ፊት ለፊታቸው እናቆማለን፤ ከዚያም አውቶቡሱን ለቀው ይወጣሉ” ሲሉ በአንድ ወቅት ተደምጠዋል። ሆዜ ሞሪንሆ በዚህ ፍልስፍና ከፖርቶ እና ከቸልሲ በተጨማሪ በሪያል ማድሪድም ስኬታማ ጊዜ ማሳለፋቸው አይዘነጋም።
የአውቶቡሱን ማቆም ወይም በጥልቀት መከላከል የእግር ኳስ ፍልስፍና ፈጣሪ እንደሆኑ ይነገራል- ሄሌኒዮ ሄሬራ። ጣሊያናዊው የቀድሞ አሰልጣኝ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦችን አሰልጥነዋል። በኢንተርሚላን፣ በባርሰሎና እና በአትሌቲኮ ማድሪድ በጠንካራ መከላከል ስልት ውጤታማ ሆነዋል። ሄሌኒዮ ሄሬራ በ1960ዎች በኢንተር ሚላን “ካቴና መቆለፍ” በሚል በጥብቅ የመከላከል ስልት አዲስ የእግር ኳስ አብዮት ፈጥረዋል። በሚከተሉት የእግር ኳስ ስልትም የጣሊያን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ቁንጮ ክለብ መሆን ችለዋል።
ሄሬራ አዙሪዎቹን የሦስት የሴሪኤ ዋንጫ ባለቤት ሲያደርግ የአውሮፓ ዋንጫ (የአሁኑ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን) ጭምር አሳክቷል። በዚህ የእግር ኳስ ታክቲክ ክለቡ አነስተኛ ግቦች እንደተቆጠሩበት መረጃዎች አስነብበዋል። የአውቶቡሱን ማቆም የእግር ኳስ ፍልስፍና መሰረት የተጣለው በዚያን ወቅት መሆኑንም የጊቭ ሚ ስፖርት መረጃ ያስነብባል። በእርግጥ ከጣሊያናዊው አሰልጣኝ በፊት እ.አ.አ በ1930 ኦስትሪያዊው አሰልጣኝ ካርል ራፔን ተመሳሳይ የእግር ኳስ ፍልስፍና ይዞ ብቅ ብሎ እንደነበር ይነገራል።
አሰልጣኝ ሄሌኒዮ ሄሬራ ታክቲኩን የበለጠ ቀምሮ እና አሳድጎ በአውሮፓ አስፈሪ ቡድን በመገንባት ፍልስፍናውን ለዓለም አስተዋውቆታል። ጣሊያናዊው የቀድሞ አሰልጣኝ ከተከላካዮቹ ጀርባ ሽፋን የሚሰጥ ሌላ አንድ ተከላካይ በማቆምም የግብ ክልሉን ይበልጥ በካቴና ይቆልፈው እንደነበረ መረጃዎች አስነብበዋል። ከእርሱ የእግር ኳስ ታክቲክ በቀጥታ በመቅዳት አሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ እና ዲያጎ ሲሞኒ በዘመናዊ እግር ኳስ ተግባራዊ ያደረጉት ተጠቃሽ አሰልጣኞች ናቸው።
አትሌቲኮ ማድሪድ በአሰልጣኝ ዲያጎ ሲሞኒ ስር በጥልቀት በመከላከል ስልት የሚታወቅ ሌላኛው ክለብ ነው። ቡድኑ በደንብ የተደራጀ እና ታታሪ ነው። እቅዱን ሜዳ ላይ በሚገባ ተግባራዊ የሚያደርግ እና የተጋጣሚን እቅድ የሚያከሽፍ ጭምር ነው። ዲያጎ ሲሞኒ ክለቡን እ.አ.አ በ2011 ከተረከበ በኋላ በሁሉም ረገድ የተዋጣለት ክለብ በማድረግ በአውሮፓ አስፈሪ ቡድን አድርጎታል። በሚከተለው ጥብቅ የመከላከል ስልትም ሁለት የላሊጋ፣ ሁለት የኢሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን አሳክቷል። በታላቁ መድረክ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ ሁለት ጊዜ ፍጻሜ ደርሷል። ዲያጎ ሲሞኒ ስለሚከተለው የእግር ኳስ ፍልስፍና ሲናገር ይህን ነበር ያለው። “ቀጣናዬን ቆልፌ፣ ተጋጣሚ እንዲመጣ ሙሉ ፈቃዴን እሰጠዋለሁ፤ እኔ ሽንፈትን እፀየፋለሁ፡፡ የላቲን አሜሪካ ስነ ልቦና ያላቸውን፣ በአካል ብቃት የማይበገሩ ብረት ለባሽ ተጨዋቾችን እወዳለሁ፤ እኔም እንደዛው ነኝ:: ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ እና ራስን በመከላከል የህይዎት መንገዴ ነው፤እግር ኳሴም ይሄው ነው::” ሲል መናገሩ የሚታወስ ነው፡፡
ጣሊያናዊው አሰልጣኝ ፋቢዮ ካፔሎም የሚከላከል ቡድን በመገንባት ከተካኑ የዓለማችን ታላላቅ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ናቸው። አሰልጣኝ ፋቢዮ ካፔሎ ኤስሚላንን፣ ሪያል ማድሪድን እና የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድንን አሰልጥነዋል። በኤስሚላን የአሰልጣኝነት ዘመናቸው በጥልቀት የሚከላከል ቡድን ገንብተው ውጤታማ ሆነዋል። አሰልጣኙ በዚህ የእግር ኳስ አቀራረብ በሮማ እና ሪያል ማድሪድም ስኬታማ ነበሩ። ሁለቱ ጣሊያናውያን አሰልጣኞች አንቶኒዮ ኮንቴ እና ማስሚላኖ አሊግሪ፣ እንግሊዛዊው አሰልጣኝ ራፋ ቤኒቴዝ፣ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ፈርናንዶ ሳንቶስ እና የመሳሰሉት በጥልቀት የሚከላከል ቡድን በመገንባት የሚታወቁ ሌሎች የእግር ኳስ ሊቆች ናቸው። አውቶቡሱን ማቆም ምንም እንኳ ያረጀ እና ጊዜ ያለፈበት የእግር ኳስ አስተሳሰብ ነው ቢባልም አሁን ድረስ የዚህ ቀበኛ የሆኑ አሰልጣኞች ግን እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።፡፡
(ስለሸ ተሾመ)
በኲር የሚያዝያ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም