አይረሴዎቹ

0
174

ዓለማችን በ2016 ዓ.ም አያሌ አወንታዊ እና አሉታዊ ክስተቶችን እንዳስተናገደች የመጀመሪያው ክፍል ጠቁሞ ነበር። በመቀጠልም ዓለማችን በተለይም ከሃገር መሪዎች ጋር በተያያዘ በቀደሙት ዓመታት ያሳለፈቻቸውን ክስተቶች አስታውሶናል። ቀጣዩ የመጨረሻ ክፍልም እንደሚከተለው ቀርቧል።

ወደ ሕንድ ስናቅና ሞሃንዳስ ካራማቻንድ ጋንዲን እናገኛለን። ጋንዲ ፀረ እንግሊዝ አገዛዝ ላይ የታገለውን የሕንድ ብሔራዊ ንቅናቄን የመሩ እና የሀገራቸውም አባት ተብለው ይታሰባሉ። ጋንዲ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ለውጥን ለማሳካት ሰላማዊ ተቃዉሞ ማድረግ በሚል አስተምህሯቸው በአለማቀፍ ደረጃ ክብርን ተጎናፅፈዋል። ነገር ግን ጋንዲ በሕይወታቸው ትልቁ ያሳዘናቸው ጉዳይ የሕንድ ነፃነት እውን የሆነው የሕንድ አንድነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ መሆኑ ነበር።

ጋንዲ እና ጓዶቻቸው ወህኒ ተወርውረው በነበሩበት አጋጣሚ የሙስሊም ተገንጣይ አራማጆች ትልቅ አቅም አግኝተው ነበር። እንዲሁም ከ1938-1939 ዓ.ም የመጨረሻው የሕገ መንግስት ማሻሻያ ውይይት ሲደረግ፣ በሙስሊሞች እና በሂንዱዎች መካከል የተቀሰቀሰው አመፅ በሚያሳዝን ሁኔታ የጋንዲን ምክንያታዊነት እና ፍትህ፤ መቻቻል እና መተማመንን የሚመክሩ አስተምህሮዎቻቸውን የመሰማት እድል የቀነሰ ሁኔታን ፈጥሯል።

ከእርሳቸው ምክር በተቃራኒው የሀገሪቱ መከፈል ተቀባይነት ሲያገኝ፣ ጋንዲ ሙሉ ነፍሳቸውን አሰባስበው የማህበረሰቡን የግጭት ጠባሳዎች በመፈወስ ተግባር ላይ ተሰማሩ፣  በአመፅ የተጎዱትን የቤንጋል እና የባይሃር አካባቢዎችን ጎበኙ፣ አክራሪዎቹን ለመገሰፅ፣ ተጎጅዎችን ማፅናናት፣ እና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ሞከሩ።

በዚያ ወቅት የነበረው በጥላቻ እና በጥርጣሬ የተሞላው ድባብ፣ ይህን ለመከወን አስቸጋሪ እና ልብ ሰባሪ ስራ አድርጎታል። ጋንዲ በሁለቱም ማህበረሰቦች አክራሪ ደጋፊዎች በኩል ተወቅሰዋል። ለማሳመን ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ሲቀር ጋንዲ ወደ ፆም ፀሎት ገቡ።

በ1939 ዓ.ም ቢያንስ ሁለት አስደናቂ ድሎችን አስመዝግበው ነበር፥ በመስከረም 1939 ዓ.ም ላይ ጋንዲ ያደረጉት የፆም ፀሎት ተግባር ካልካታ ውስጥ የነበረውን አመፅ አስቁሟል፣ እንዲሁም ጥር 1940 ዓ.ም ላይ የደልሂ ከተማን ወደ ማህበረሰባዊ እርቅ አስገብቶ ነበር። ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ጥር 21ቀን 1940 ዓ.ም  ደልሂ ውስጥ ወደ ሚደረግ አንድ የምሽት የፀሎት ስብሰባ ለመገኘት፣ በመሄድ ላይ ሳሉ፣ ድንገት ናቱራም ጎዶሴ በተባለ አንድ ወጣት አክራሪ ሂንዱ በተተኮሰ ጥይት እንደተመቱ ብሪታኒካ በታሪክ ገፁ ዘግቦት ይገኛል።

ናቱራም ጎዶሴ፣ ጋንዲ ከሂንዱዎች በበለጠ ለሙስሊሞች ከፍተኛ ክብር ሰጥተዋል ብሎ ያምን ነበር። ለምሳሌ፣ በሂንዱ ቤተመቅደሶች ውስጥ ቅዱስ ቁርአንን በአስተምህሮዎቻቸው በማካተት ሲያስተምሩ፣ ነገር ግን የሂንዱን በሃጋቫድ ጊታን በየመስጊዶች አያካትቱም ነበር። በተጨማሪም ጎዶሴ ጋንዲን ሀገሪቱ በምትከፈልበት ወቅት እና በኋላ በሕንድ ብሔራዊ ኮንግረስ ውስጥ ውጤታማ ያልሆነ ስልጣን በመጠቀማቸው በጣም ይኮንናቸው ነበር። ጎዶሴ በተኮሳቸው ሦስት ጥይቶች ጋንዲ ወዲያውኑ እንደሞቱ እና ጎዶሴም ወዲያው ተይዟል። ከወራት በኋላ በተለቀቀው አንድ መግለጫ ላይም፤ ጎዶሶ ከመተኮሱ በፊት በጋንዲ ፊት ጎንበስ ብሎ እንደሰገደ እና መልካም ምኞቱን ገልፆላቸው እንደነበር ይፋ ሆኗል።

የእናት እና ልጅ ጠቅላይ ሚንስትሮች ተመሳሳይ መጨረሻ፤ ሕንድ ሌላም ተመሳሳይ የታሪክ ክስተቶችን አስተናግዳ ነበር።

ኢንድራ ጋንዲ እና ራጃቭ ጋንዲ እናት እና ልጅ ጠቅላይ ሚንስትሮች ሆነው ሀገራቸውን ያገለገሉ፣ ተመሳሳይ መጨረሻም ያላቸው ናቸው።  ኢንድራ ጋንዲ ሕንድን ከ1958 -1969 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ተከታታይ ዙሮች እንዲሁም አራተኛ ዙሯን ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ እስከተገደለችበት 1976 ዓ.ም ድረስ ሕንድን በጠቅላይ ሚንስትርነት መርታለች። ኢንድራ ጋንዲ ከሕንድ ነፃነት በኋላ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት ጃዋሃራላል ነሂሩ ብቸኛ ልጅ ነበረች። ነሂሩ በ1956 ዓ.ም ከሞቱ በኋላ ላ ባሃዱር ሻስትሪ  ተተክቶ በድንገት ሕይወቱ እስካለፈ ድረስ በጠቅላይ ሚንስትር አገልግሏል። ሻስትሪ ጥር ወር 1958 ዓ.ም ከሞተ በኋላ፤ ጋንዲ ከ1945 ዓ.ም ጀምሮ በአባልነት ስታገለግል የቆየችበት የኮንግረስ ፖርቲ መሪ እንደሆነች እና በተመሳሳይም በፖርቲው የግራ እና የቀኝ ክንፎች ስምምነት መሰረት ጠቅላይ ሚንስትር ልትሆን እንደበቃች ታሪኳ ያሳያል።

ጋንዲ እና የኮንግረስ ፓርቲዋ እስከ 1969 ዓ.ም ድረስ በስልጣን ቆይተዋል።  በዚሁ ዓመት በዋነኛ ተቃዋሚው ጃናታ ፓርቲ ከተሸነፈች በኋላ፤ በጋንዲ የሚመራው ኮንግረስ ፓርቲ ከዜሮ ራሱን እንደገና አደራጅቶ በ1972 ዓ.ም እንደገና ወደ ስልጣን ተመልሷል። ኢንድራ ጋንዲም በድጋሜ የሀገሪቱ መሪ ሆና ብቅ አለች።

የ1970ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ታዲያ ጋንዲ አያሌ የፖለቲካዊ አለመረጋጋት ችግሮችን የተጋፈጠችባቸው ነበሩ። ከማእከላዊ መንግሥት ነፃነታቸውን የሚፈልጉ በርካታ ክልሎች መበራከት እና በፑንጃብ ደግሞ ራስ ገዝነትን የጠየቁ የሳይክህ ተገንጣይ ቡድኖች ሀይል ተጠቀሙ። ለዚህ ምላሽም ጋንዲ ሰኔ ወር 1976 ዓ.ም  ለወታደራዊ ሀይሏ፤ አርሚፃር ውስጥ ባለው ሀርማንዲር ሳሂብ (ወርቃማው የቤተመቅደስ) በተባለው በሳይኮች ቅዱስ ስፍራ ላይ ጥቃት እንዲፈፅም ትዕዛዝ ሰጠች።

በጥቃቱ ከ450 በላይ ሳይክህዎች ተገደሉ። ይህ ከሆነ ከአምስት ወራት በኋላ ግን በመኖሪያ ቤቷ የአትክልት ስፍራ  ከሳይክህ ወገን በሆኑ ሁለት የግል ጠባቂዎቿ፤ የወርቃማው ቤተመቅደስ ጥቃትን ለመበቀል በሚል በተኩስ እሩምታ ተገደለች።

ራጃቭ ጋንዲ፤ የኢንድራ ጋንዲ ወንድ ልጅ፤ የእናቱን መገደል ተከትሎ ከ1976 ዓ.ም እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን አገለገለ። ሳንጃቭ የተባለ ወንድሙ በሕይወት እያለ፤ ራጃቭ ከፖለቲካ ራሱን ያገለለ ነበር። ነገር ግን በፖለቲካው የገዘፈ ስም የነበረው ሳንጃቭ፣ በሰኔ ወር 1972 ዓ.ም በአውሮፕላን አደጋ ሲሞት፤ በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበረችው ኢንድራ ጋንዲ፤ ለራጃቭ የፖለቲካ ኃላፊነት ሰጠችው። በ1973 ዓ.ም የፖርላማ አባል ሆኖ ተመረጠ፣ እንዲሁም በዚያው ዓመት የሕንድ የወጣት ኮንግረስ አስፈፃሚ አባል ሆነ።

ወንድሙ ሳንጃቭ፣ በፖለቲካ ጉዳይ በምህረት የለሽ እና ግትርነቱ ይገለጻል፣ በሌላ በኩል ራጃቭ ግን የተቃዋሚ ፖርቲ አባላትን የሚያማክር እና ከችኩል ውሳኔ የተቆጠበ በመሆኑ ይከበር ነበር።  እናቱ ጥቅምት 20 ቀን 1976 ዓ.ም በተገደለችበት በዚያው እለት የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን ቃለ መሀላ መፈፀሙን እና ከጥቂት ቀናት በኋላም የኮንግረስ ፓርቲው ሊቀመንበር እንዲሆን  መመረጡን ታሪኩ ያስረዳል። በታህሳስ ወር 1976 ዓ.ም  በተደረገ ምርጫ የኮንግረስ ፓርቲውን በከፍተኛ ድምፅ አሸናፊ አድርጓል፣ እንዲሁም የእርሱ አስተዳደር በመንግሥት ቢሮክራሲ ላይ በርካታ የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ እና ኢኮኖሚውን ወደ ነፃ ገበያነት እንዲሸጋገር አድርጓል። ነገር ግን እናቱ ጋንዲ እንዲዳከም ጥረት ስታደርግባቸው የነበሩት የፑንጃብ እና ካሽሚር የመገንጠል እንቅስቃሴዎች በእርሱ አስተዳደር ዘመን እንደገና አገረሹ። ከዚያም መንግሥቱ በአያሌ የገንዘብ ነክ ቅሌቶች ከተዘፈቀ በኋላ አቅመቢስ በመሆን ተዳከመ። እናም በሕዳር ወር 1981 ዓ.ም በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን ለመልቀቅ በቅቷል። ይሁን እንጅ የፓርቲው ሊቀመንበር እንደሆነ ቀጠለ።

ራጃቭ ጋንዲ በታሚል ናዲ ውስጥ ለመጪው የፓርላማ ምርጫ ቅስቀሳ እያደረገ ነበር፤ ከታሚል ታይገር ሸማቂዎች ጋር ግንኙነት ያላት ቦንብ የተደበቀበት የአበባ መያዢያ ቅርጫት በተሸከመች አንድ ሴት አማካይነት በፈነዳ ቦምብ እርሱ እና ሌሎች 26 ሰዎች የተገደሉበት። መላዋን ሕንድ በሐዘን ድባብ ውስጥ የከተታት አስደንጋጭ ክስተት በ1983 ዓ.ም ተፈፀመ። በ1990 ዓ.ም የሕንድ ፍርድ ቤት ራጃቭን በመግደል ወንጀል በ26 ሰዎች ላይ ፍርድ አስተላለፈ። ሴራውን ጠንሳሾቹ ከሲሪላንካ የመጡ የታሚል አማፂያንን እና የሕንድ አጋሮቻቸውን ያካተተ እና ራጃቭ በስሪላንካ ይደረግ የነበረውን የሰላም ስምምነት ለማገዝ የላካቸው የሕንድ ወታደሮች መጨረሻቸው የታሚል ተገንጣይ አማፂያኑን በመውጋታቸው ምክንያት በራጃቭ ላይ የበቀል እርምጃ መውሰዳቸው ነበር የተነገረው።

በመጨረሻም ሞቱ ለመጀመሪያው የዓለም ጦርነት መጀመር ዋና ምክንያት የሆነውን የኦስትሪያውን መስፍን የፍራንሲስ ፈርዲናንድን ታሪካዊ የግድያ ክስተት እናነሳለን። ፍራንሲስ ፈርዲናንድ የኦስትሪያ ንጉሠ ነገሥት የፍራንሲስ ጆሴፍ  ወንድም የነበረው የልዑል ቻርልስ ሉዊስ ታላቅ ልጅ ነበር። ቀጥተኛ ወራሽ የነበረው ልዑል ሩዶልፍ በ1881 ዓ.ም መሞቱ፣ ፍራንሲስ ፈርዲናንድንን ከአባቱ ቀጥሎ በኦስትሪያ ሀናጋሪ ላይ ቀጣዩ አልጋ ወራሽ አደረገው።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here