አይቀሬዉ  ሕግ

0
29

   የስነ ልቦና ባለሙያው ካርል ዩንግ ለውጥን በሚመለከት “አንድን ነገር ካልተቀበልነው መለወጥ አንችልም:: ለውጥን መሸሽ ይጨቁናል እንጂ ነጻ አያወጣም” ብሏል::

ለውጥ በዚህ ዓለም ውስጥ ቋሚ ነገር ነው:: ግን ለሰው ልጆች ከባዱ ትግል ሆኖ ቀጥሏል:: አዲስ ነገር እንፈልጋለን:: ደግሞ ከለመድነው ጋር ተጣብቀን መኖርን እንመርጣለን:: ይህ ተቃርኖ በግልና በሙያዊ ሕይወታችን ውስጥ የሚገኝ ሐቅ ነው:: ለውጥ ለምን ከባድ እንደሆነ፣ ለእድገት ለምን የግድ አስፈላጊ እንደሆነ፣ እና እንዴት ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች ይህን ሂደት ማለፍ እንደምንችል ለመረዳት ወደ ሥነ-ልቦናችን ጠለቅ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል:: ዛሬ የምናደርገው ይህን ነው::

ሕይወት ከለውጥ ጋር ተመሳሳይ ነው:: በነበሩበት መቆም (መገተር) የመበስበስ ምልክት ነው:: ደራሲና ንግግር አዋቂው አላን ዋትስ በተደጋጋሚ የሚለው አባባል ነበረው:: “ሕይወት እንደ ወንዝ ነው:: ለመግታት መሞከር የባህሪውን ዋና ነገር መርሳት ነው:: ለለውጥ እምቢ ማለት ይህን ፍሰት ለመግታት እንደ መሞከር ነው:: ይህም ወደ ጫና፣ መሰበር እና በመጨረሻም ወደ ውድቀት ያመራል” ብሎ ነበር:: በባህሪው ለውጥ የሚቀር ወይም የሚቆም አይደለም::

ያለ ለውጥ አዕምሯዊ፣ ስሜታዊ እና መንፈሳዊ እድገት ማምጣት የሚቻል ነገር አይደለም:: ከአካባቢው ጋር የማይላመዱ ስራዎች ይወድቃሉ:: የማይሻሻሉ ግንኙነቶች ይከስማሉ:: የማይማሩና ራሳቸውን የማያስተካክሉ ግለሰቦች የቀድሞ ማንነታቸው ጥላ ብቻ ሆኖ ይከተላቸዋል:: ለውጥ ምርጫ ሳይሆን፣ ትርጉም ላለውና ለሚያድግ ሕይወት መግቢያ በር ነው::

ታዲያ ለውጥ ይህን ያህል አስፈላጊ ከሆነ ለምን ይከብደናል? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው:: ለውጥን የሚቃወም ስሜታችን በነርቭ ባዮሎጂያችን ውስጥ የተመሰረተ ነው:: አንጎላችን ሂደቶችን በራሱ ኃይል ለመቆጠብ የተነደፈ ነው:: ቻርለስ ዱሂግ የልማድ ኃይል በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዳብራራው ልማዶች ውስብስብ ባህሪያትን ሳናስብ እንድናከናውን የሚያስችሉን የነርቭ ቀለበቶች ናቸው::

ልማድን ለመለወጥ መሞከር ከእነዚህ በጥልቀት ከተገነቡ ኃይል ቆጣቢ ቀለበቶች ጋር መታገል ማለት ነው:: ልማዳችን ኃይል እንድንቆጥብ ያደርገናል:: አንጎላችን ነገሮችን ማቅለልን ይመርጣል:: በለመደው መፍሰስን ያዘወትራል:: ይህ ሂደት ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀመውን የአንጎላችን ዋና ክፍል የሆነውን ፕሪፍሮንታል ኮርቴክስ ማንቃትን ይጠይቃል:: ይህም አሁን ላለንበት ሁኔታ እንድንወግን ጠንካራ ባዮሎጂያዊ ዝንባሌ ይፈጥራል:: ፕሪፍሮንታል ኮርቴክስ የተለመደውን ይዞ መቀጠል የሚመርጥ ክፍል ነው::

በተጨማሪም እንደ ዳንኤል ካህነማን ያሉ የባህሪ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች “የኪሳራ ፍራቻ” ብለው የሰየሙትን መርህ አስቀምጠዋል:: አንድን ነገር የማጣት ስሜት፣ ተመሳሳይ ዋጋ ያለውን ነገር ከማግኘት ደስታ በስነ-ልቦና ደረጃ በእጥፍ ይበልጣል:: እያንዳንዱ ለውጥ፣ አዎንታዊ ቢሆንም እንኳ፤ ኪሳራን ያካትታል:: የለመድነውን የዕለት ተዕለት ተግባር፣ የድሮ ማንነትን ወይም ምቹ የዓለም እይታን ማጣት ማለት ነው:: ኪሳራን በመፍራት ለለውጥ ግትሮች እንሆናለን:: ለዚህም እንፈራለን::

ለውጥ ለሁሉም የሚሰራ አንድ አይነት ቀመር የለውም:: ለውጥ ግለሰባዊ የሕይወት ጉዞ ነው:: ከዋና ማንነታችን ጋር መገናኘት ይኖርበታል:: ይህም ጄምስ ክሌር አቶሚክ ሀቢትስ በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ ያነሳው ማዕከላዊ ሐሳብ ሆኖ እናገኘዋለን:: ክሌር እንደሚለው፣ እውነተኛ የባህሪ ለውጥ የማንነት ለውጥ ነው:: ግቡ “ማጨስ ማቆም” ብቻ ሳይሆን “ሲጋራ የማያጨስ ሰው” መሆን ነው:: “ማራቶን መሮጥ” ሳይሆን “ሯጭ” መሆን ነው:: አዲሱ ባህሪ ከምንፈልገው ማንነት ጋር ሲተሳሰር፣ ተነሳሽነቱ ከውስጥ ይመነጫል:: ጥያቄውም “ምን ማድረግ አለብኝ?” ከሚለው ወደ “ምን መሆን እፈልጋለሁ?” ይቀየራል::

ይህ ውስጣዊ መስተጋብር ወሳኝ ነው:: ምክንያቱም ውጫዊ ግፊቶች ብዙውን ጊዜ ውጤታማ አይደሉም:: አንድ ሐኪም ለታካሚው ክብደት እንዲቀንስ ቢነግረው ለጊዜው ሊተገበረው ይችላል:: ነገር ግን ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው ታካሚው “እኔ ጤንነቴን የምንከባከብና ለሰውነቴ ዋጋ የምሰጥ ሰው ነኝ” ብሎ በግሉ ሲወስን ነው:: እናም አምኖ መኖር ሲጀምር ነው:: ይህ ውስጣዊ ታሪክ በመንገድ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችንና መሰናክሎችን ለማለፍ የሚያስችል ጉልበት ይሰጣል:: ጉልበት ከእምት ይመጣልና::

አንድን ሰው በግድ ለመለወጥ ከመሞከር ይልቅ፣ በጣም ውጤታማው መንገድ በዙሪያው ያለውን አካባቢ መቀየር ነው:: ጄምስ ክሌር ይህንን “የአካባቢ ምህዳርን ማስተካከል” ብሎ ይጠራዋል:: በዚህም አንድ የቤተሰባችን አባል ጤናማ ምግብ እንዲመገብ ከፈለግን ከመስበክ ይልቅ ወጥ ቤቱን ጤናማና በቀላሉ በሚገኙ ምግቦች መሙላት፤ ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን ደግሞ ለማግኘት አስቸጋሪ ማድረግን ይመከራል::

ሌላው ጠንካራ ዘዴ ተፈላጊውን ለውጥ ዓርዓያ በመሆን በተግባር ማሳየት ነው:: በዓርዓያነት መምራት በትዕዛዝ ከመምራት የበለጠ ተጽዕኖ አለው:: ሰዎች የእኛን ለውጥ አዎንታዊ ውጤቶች፣ ጉልበታችንን፣ ደስታችንን እና ስኬታችንን ሲመለከቱ ከሚገፋ ይልቅ የሚስብ ኃይል ይፈጠራል:: ፍሬያችንን የሚያዩ ሰዎች እኛን ተመልክተው ይለወጣሉ፤ ይከተሉናል::

ጀምስ ክሌር እንደሚለው ትልልቅ ግቦችን የማሳካት መንገድ የተገነባው በአንድ ጊዜ በሚደረጉ ትልልቅና ዘላቂነት በሌላቸው ጥረቶች ሳይሆን፤ በትናንሽና ወጥ በሆኑ ድርጊቶች ነው:: “ጠብታ ውኃ አለት ትሰብራለች” እንደሚባለው አንድን ነገር በትንሽ መጠን ሳያቋርጡ ማድረግ የለውጥ ልምምድ እና ፍሬ ላይ ያደርሰናል::

አንድ ግለሰብ ሰዓሊ የመሆን ህልም ሊኖረው ይችላል:: ነገር ግን ተሰጥኦ እንደሌለው አምኖ የሰዎችን ትችት ይፈራል:: ግቡ የማይቻል ይመስለዋል:: ለውጡ የሚጀምረው ማንነቱን “መሳል ከሚፈልግ ሰው” ወደ “ሰዓሊ” በመቀየር ነው:: ሰዓሊ ነኝ ብሎ በማመኑ ላይ ነው ቁም ነገሩ ያለው:: አቶሚክ ሀቢትስ መጽሐፍ መርሆዎችን በመከተል ብቻ መነሳሳት እስኪመጣ አይጠብቅም:: ልማድን መደርደር የተባለውን ዘዴ ይጠቀማል:: ይህም “የጠዋት ቡናዬን ከጠጣሁ በኋላ ለአምስት ደቂቃ ቀለም ቅብ እሰራለሁ” ማለት ሊሆን ይችላል::

ሸራውንና ቀለሞቹን ዝግጁ አድርጎ በማስቀመጥ አካባቢውን ያስተካክላል፤ ይህም መጀመርን የሚያከብዱ ነገሮችን ይቀንሳል:: ትኩረቱ ድንቅ ስራ መፍጠር ላይ ሳይሆን፤ በየቀኑ የመሞከር ሂደት ላይ ነው:: እነዚያ አምስት ደቂቃዎች ወደ አስር፤ ከዚያም አንድ ሰዓት ይሆናሉ:: ከዓመታት በኋላ አንድ ጊዜ በመጣ አስማት ሳይሆን በሺዎች በሚቆጠሩ ወጥና ትናንሽ ድርጊቶች ምክንያት የስራዎች ስብስብ ይኖረዋል:: ምርጥ ሰዓሊ የሚሆነው በዚህ ሒደት አልፎ ነው:: ብዙዎቻችን በእርምጃ ከመድረስ ይልቅ ለመሮጥ ስለምንሞከር ሳንደርስ ደክሞን እንወድቃለን::

በመጨረሻም ለውጥ የሕይወት ከባድ ነገር ግን አስፈላጊ ዳንስ ነው:: አንጎላችን ይቃወመዋል፣ ማንነታችን ይፈራዋል፣ ነገር ግን ወቅቱ ይፈልገዋል:: ዓለም ትፈልገዋለች:: ዋናው ቁልፍ ለውጡን ግላዊ ማድረግና ልንደርስበት ከምንመኘው ራዕይ ጋር ማቆራኘት ነው:: ሌሎችን ለመደገፍ በምንፈልግበት ጊዜ ደግሞ ሚናችን በኀይል ድንጋይ እንደሚጠርብ የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያ መሆን አይደለም:: ይልቁንስ ብርሃን፣ ለም አፈርና ከለላ በመስጠት ሰዎች በራሳቸው እንዲያድጉ የሚያደርግ እንደ አትክልተኛ ዓይነት ተንከባካቢ መሆን ነው::

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የህዳር 8 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here