አደሴቁኒ

0
142

ሳር፣ ጥራጥሬ እና ስራስር በመብላት ይታወቁ የነበሩት  አደሴቁን ወይምየሽኮኮ ዝርያዎች አይጥ እና መሰሎችንም አድነው እንደሚበሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በመረጋገጡ ሁሉን በል መሆናቸውን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ከዊስኮንሲን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ካደረጉት ጥናትና ምርምር ባሻገር በቀጣናው በሚገኝ ፓርክ ባካሄዷቸው ምልከታዎች ሽኮኮዎች አይጦችን አድነው ሲበሉ በቪዲዮ ቀርፀው በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡

ግኝቱ ቀደም ብሎ የነበረውን ሽኮኮዎች ቅጠላቅጠል እና ስራስር በል ናቸው የሚለውን አስተሳሰብ የለወጠ መሆኑን ያስታወቁት ተመራማሪዎቹ ከሰኔ 10 እስከ ሐምሌ 30/2024 እ.አ.አ ባደረጉት ምልከታ፣ ክትትል እና የምስል ቀረፃ አይጦችን አሳደው በመያዝ ገነጣጥለው እንደሚበሉ አረጋግጠዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት በዛፍ እና በአለታማ ገደል ላይ የሚኖሩ ሽኮኮዎች ፌንጣ፤ አንበጣ የመሳሰሉ ነፍሳትን እና የዓዕዋፍ እንቁላልን ሲበሉ መታየታቸውን እንደሚያውቁ ነው የገለጹት – ተመራማሪዎቹ፡፡ የተጠቀሰው እውነታ አልፎ አልፎ ነፍሳትን፣ እንቁላል መብላታቸው በዋናነት ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ እና ስራስር በልነታቸውን እንደማይቀይረው ወይም መሠረታዊ ለውጥ እንደማያስከትል ነበር የጠቆሙት፡፡

በ2024 እ.አ.አ ከሰኔ 10 እስከ ሐምሌ 30 በነበሩት 18 ቀናት የተመራማሪዎች ቡድኑ 27 ሽኮኮዎች አይጦችን አድነው ሲበሉ በቪዲዮ ቀርፆ በማስረጃነት መያዙን አስረድቷል፡፡ ስጋ በል ሽኮኮዎቹ አንዱ ከአንዱ የሞቱ አይጦችን ሲነጣጠቁ መታዘባቸውን የአስታወቁት ተመራማሪዎቹ ሁነቱ ያልጠበቁት እንግዳ እንደሆነባቸውም አስምረውበታል፡፡

ተመራማሪዎቹ ለተከሰተው አዲስ ሁነት በቀጣናው የአይጦች ብዛት ከመጨመሩ ጋር መገጣጠሙን እንደ ምክንያት አንስተዋል፡፡ ለዚህም  የአይጦች ቁጥር ወይም ብዛት ባለፉት 10 ዓመታት ከነበረው አማካይ ሰባት እጥፍ መብለጡ ለአመጋገብ ለውጡ መነሻነቱን አስረድተዋል፡፡

የጥናትና ምርምር ቡድኑ ተመራማሪዎች በደረሱበት ማደማደሚያ በካሊፎርኒያ ጥናትና ምርምሩ ትኩረት ባደረገበት ቀጣና ሽኮኮዎች ቅጠላቅጠል እና ስራስር በል ብቻ ሳይሆኑ ስጋ በልነትን የሚያካትቱ ሁሉን በል “ኦምኒቫረስ” መሆናቸውን ነው ያሰመሩበት፡፡::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የታኅሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here