የጉበት በሽታ (ሂፐታይተስ) ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ በሽታ ነው። በሽታው ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ እንደሚተላፍ የአውሮፓ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ecdpc) መረጃ አመላክቷል። ከሰውነት ክፍላችን ውስጥ ከቆዳ ቀጥሎ ትልቅ ክብደት ያለው ጉበት አንድ ነጥብ አራት ኪሎ ግራም ይመዝናል። በሰው ልጅ የሆድ እቃ ውስጥ ትልቅ ሥራ ካላቸው የሰውነት ክፍሎች ውስጥም ጉበት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል። በርካታ ተግባራት ያሉት ጉበት ምግብም ሆነ መድኃኒት ስንወስድ ቀድሞ ይደርሰዋል። የደረሰውን አጣርቶ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ያሠራጫል።
በርካታ ተግባራት የተጣለበት ጉበት በጀርሞች፣ በቫይረሶች፣ በትላትሎች፣ በቫክቴሪያዎች፣ በፈንገሶች፣ በመድኃኒቶች፣ በአደንዛዥ እጾች (በሲጋራ፣ ጫት) እና በአልኮል ጉዳት ይደርስበታል። እነዚህ ወደ ጉበታችን ከደረሱ እንደየ መጠናቸው ጉዳት ያስከትላሉ።
ሄፕታይተስ ኤ፣ ቢ፣ ሲ እና ዲ የተባሉ ቫይረሶች ጉበትን በመጉዳት ከከፍተኛ ሕመም እስከ ሞት የሚያደርሱ ናቸው። ሄፕታይተስ ኤ የተባለው የሕጻናትን ጉበት የሚያጠቃ የቫይረስ ዓይነት ነው። በበቂ መጠን ንጹህ ውኃ በሌለበት እና ንጽሕናው ባልተጠበቀ አካባቢ የሚኖሩ ሕጻናት ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ።
ሄፕታይተስ ቢ እና ሲ የተባሉት ደግሞ አዋቂዎችን የሚያጠቁ የቫይረስ አይነቶች ናቸው፡፡ የሻገተ እንጀራ በተደጋጋሚ በመብላት፣ አልኮል በመጠቀም፣ ሲጋራ በማጨስ፣ ያልታዘዙ መድኃኒቶችን በተከታታይ በመውሰድ የሚመጡ ናቸው። ሄፕታይተስ ቢ እና ሲ የተባሉት የጉበት በሽታዎች ተላላፊ ናቸው፤ የመተላለፊያ መንገዳቸው ደግሞ ልቅ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ስለታማ ነገሮችን በጋራ በመጠቀም እና በጥንቃቄ ጉድለት የሚፈጠር የደም ንክኪ ናቸው።
ኤች አይ ቪ በሚተላለፍባቸው መንገዶች ሁሉ የጉበት ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል። ሂፐታይተስ ከኤች አይቪ ጋር ሲወዳደር ደግሞ እጅግ አደገኛ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕይወትን ሊያሳጣ ይችላል፡፡ በተለይ ሂፐታይተስ ቢ የተሰኘው የጉበት ቫይረስ እንደ ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ ይተላለፋል፡፡ በዚህም ምክንያት ለጨቅላ ሕጻናት ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ክትባት ተዘጋጅቶለታል፡፡
ይህን ከግምት በማስገባት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጉበት በሽታ (ሄፕታይተስ ቢ) የመከላከያ ክትባትን በባሕር ዳር ከተማ በሕዳር ወር መጨረሻ ሳምንት በይፋ አስጀምሯል። በወቅቱም አቶ አዲሱ ንብረት በባሕር ዳር ጤና ጣቢያ የተወለደ ጨቅላ ልጃቸውን ሲያስከትቡ አግኝተናቸዋል፡፡ አቶ አዲሱ እንዳሉት የጉበት በሽታ መኖሩን እንጅ ክትባት እንዳለው አያውቁም። ኅብረተሰቡም ግንዛቤው ኖሮት ሕጻናትን እንዲያስከትብ በጤና ባለሙያዎች በኩል ግንዛቤ ሊፈጠር እንደሚገባ ጠይቀዋል።
የወንድማቸውን ልጅ ሲያስከትቡ ያገኘናቸው ወይዘሮ ትዕግስት ገበየሁ ደግሞ የክትባትን ጠቀሜታ እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል። ልጆቻቸውንም አስከትበው እንዳሳደጉ አስታውሰዋል። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ለጉበት በሽታ ክትባት መኖሩን እንደማያውቁ ነው የጠቀሱት። ይህን መረጃ ግንዛቤው ለሌላቸው ለሌሎች ወላጆች እንደሚያስረዱ እና ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ እንደሚገፋፉም ቃል ገብተዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጌትነት አባት የሀገሪቱ የጤና ፖሊሲያ መከላከል ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ፖሊሲውን መሰረት በማድረግም የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ በተለያዩ ጊዜያት ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ያለው የጉበት በሽታ ገዳይነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ነው የገለጹት። ለመከላከልም ከሕጻናት መጀመር ስላለበት በከተማ አሥተዳደሩ በህዳር እና በታህሳስ ወር ለ14 ሺህ ሕጻናት ክትባቱን ለመስጠት መታቀዱን ጠቁመዋል። ኅብረተሰቡም ክትባቱ በአዲስ መጀመሩን አውቆ ሕጻናትን እንዲያስከትብ ምክትል ኃላፊው ጥሪ አስተላልፈዋል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራሞች አማካሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ በበኩላቸው ጉበትን ለጉዳት ከሚያጋልጡት መንስኤዎች መካከል ሄፒታይተስ ቢ ቫይረስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍልን የሚያጠቃው ሄፒታይተስ ቢ የተሰኘው የጉበት ቫይረስ ሕጻናትን እንደተወለዱ ክትባቱን በመስጠት ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ማድረግ እንደሚቻልም ገልጸዋል። ሕጻናት ከተቻለ እንደተወለዱ ወዲያውኑ ካልሆነም በ14 ቀናት ውስጥ መከተብ እንዳለባቸው አማካሪው አሳስበዋል።
የጉበት በሽታ ተላላፊ እና አደገኛ ነው ያሉት አቶ ወርቅነህ፤ በክትባት ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በሽታው በግብረ ሥጋ ግንኙነት እና በደም ንክኪ እንደሚተላለፍም አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።
እንደ አማካሪው ገለጻ ሄፒታይተስ ቢ የተሰኘው የጉበት ቫይረስ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የጤና ችግር እያስከተለ ነው፡፡ በሽታውን ለመከላከልም ከ800 ሺህ በላይ ሕጻናት ክትባቱን እንዲወስዱ ታቅዷል።
የጉበት በሽታ ከእናት ወደ ልጅ በሚተላለፍበት ወቅት ቀስ በቀስ ወደ ካንሰርነት የመቀየር አጋጣሚው ከፍተኛ ስለሆነ አስቀድሞ ለመከላከል ሕጻናትን የማስከተብን ጠቀሜታ አመላክተዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰባት በመቶ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል እና አምስት በመቶ ነፍሰጡሮች በበሽታው እንደሚጠቁ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው አቶ ወርቅነህ ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ የጉበት ቫይረስ በሰፊው እየተሠራጨ መሆኑን ተናግረዋል። በሆስፒታል ተኝተው ከሚታከሙ ህሙማን እና የሞት አደጋ ከሚያጋጥማቸው 35 በመቶ ያህሉ የጉበት ታማሚ እንደሆኑም ገልጸዋል። “ጉበትን ጨምሮ በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች 15 ደርሰዋል” ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ ኅብረተሰቡም የክትባቱ ተጠቃሚ እንዲሆን አሳስበዋል።
ብዙ ሰዎች በሂፐታይተስ ቢ ሲያዙ መጀመሪያ ምንም ዓይነት ምልክት አያሳዩም፤ ከነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ጉበታቸው ይጎዳል ወይም የጉበት ካንሰር ይይዛቸዋል። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች የበሽታው ተሸካሚዎች የሚባሉ ሲሆን ቫይረሱንም ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ ይችላሉ። የህመሙ ምልክቶች የቆዳ እና የዐይን ነጩ ክፍል ቢጫ መሆን (ጆንዲስ በመባል ይታወቃል)፣ የሽንት መጥቆር፣ የፊት መገርጣት፣ ድካም እና የሆድ እቃ ህመም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ እንዲሁም የመጋጠሚያ (የአንጓ) ህመም ናቸው፡፡
የሂፐታይተስ ቢ ቫይረስ በበሽታው በተያዘ ሰው ደም፣ ጉበት እና የሰውነት ፈሳሽ ውስጥ ይገኛል። ሂፐታይተስ ቢ ተሸካሚ የሆነች ሴት በእርግዝናዋ ወቅት ወይም በወሊድ ጊዜ ቫይረሱ ወደ ሕፃኑ ሊተላለፍ ይችላል።::
ጤና አዳም
የሂፐታይተስ ቢ ቫይረስ በሚከተለው ሁኔታ ሊሰራጭ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት የ2025 እ.አ.አ መረጃ ያሳያል፡፡
- ንጹሕ ባልሆኑ የመርፌ መውጊያ መሳሪያዎች፣ በቀዶ ሕክምና፣ ጥርስ ሲነቀል፣ ወይም በመነቀስ
- የሂፐታይተስ ቢ ቫይረስ ያለው የሰው ደም ሲሰጥዎት
- ሂፐታይተስ ቢ ቫይረስ ከተገኘበት ሰው ጋር ምላጩንና የጥርስ ብሩሹን (ደም ያለበት ሊሆን ይችላል) በመጠቀም።
- ሂፐታይተስ ቢ ካለው ሰው ጋር ያለኮንዶም የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ
የሂፐታይተስ ቢ ቫይረስ የተገኘበት ሰው ማድረግ የሌለበት፣
- አልኮል አለመጠጣት
- የተመጣጠነና ስብ ያልበዛበት ምግብ መመገብ
- ሳያቋርጡ መደበኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ
- በድካም ጊዜ እረፍት ማድረግ ይመከራል።
(ቢኒያም መስምን)
በኲር የታህሳስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


