እስራኤል ከኢራን ጋር ወዳጅ መሆኗ አሁን ላለው ሰው እውን አይመስል ይሆናል። የሁለቱም ወታደሮች አንድ ላይ በጋራ ጠላታቸው ላይ ዘምተው ነበር። ወይም የሁለቱም ደህንነቶች ቁልፍ ሚስጢሮችን እና ወሳኝ መረጃዎችን እየተለዋወጡ ሲሰሩ ነበር። ሁለቱም በወታደራዊው ሆነ በኢኮኖሚያዊው ዘርፎች ተባብረው ይሰሩ ነበር ብሎ ለማውራት አሁን ያሉበት ሁኔታ አያስደፍር፣ አያሳምን ይሆናል። ነገር ግን ወዳጅ መሆናቸውን ውስጥ ለውስጥ እያራመዱ የሚፈልጉትን ሲጠቀሙ መቆየታቸው ሀቅ ነው።
በ1971 ዓ.ም ግን በኢራን የተካሄደው እስላማዊ አብዮት የእስራኤልን እና የኢራንን ግንኙነት አሻከረው። በአብዮቱ የተገረሰሰው የእስራኤል እና የምእራባውያን ወዳጅ የሻይት ሙስሊሞች ወገን የነበረው የሻህ አስተዳደር በሱኒ ሙሲሊሞች ቡድን በሆነው ፀረ እስራኤል እና ፀረ ምእራባውያን አቋም በያዘው በአያቶላሕ ሆሞኒ አስተዳደር ሲተካ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ አደገኛ ጠላትነት አሽቆለቆለ።
አሜሪካን “ትልቋ ሰይጣን” እስራኤልን “ትንሿ ሰይጣን” ብሎ እስከመፈረጅ የደረሰ የጠላትነት ስሜት የሚሰብከው የአያቶላህ ሆሚኒ የኢራን አብዮት ዘብ የተባለው አስተዳደር ስልጣን ሲይዝ እንደነበረው አቋም መቀጠል አልቻለም። የጥላቻ ስሜቱ እንዳለ ቢሆንም የቀጠናው ፖለቲካ ከአብዮቱም በኋላ መጠነኛ በሆነ የትብብር ግንኙነት መቀጠል ነበረበት። ኢራንና እና እስራኤል የወሰን ጉዳይ በመካከላቸው የሌለ መሆን፣ ብሎም የአረብ ጎረቤቶቻቸው ሁለቱንም በጥሩ አመለካከት የማይመለከቱበት አግባብ እና በኢራንና ኢራቅ መካከል የተነሳው ጦርነት ሁለቱን ሀገራት እርስ በእርስ አስፈላጊ እንዲሆኑ ግድ ስላለ ትብብራቸው እስከ 1990ዎቹ ድረስ ቀጥሏል።
የኢራን ቀንደኛ ጠላቶች ታሊባን እና ሳዳም ሁሴን መሸነፍ ኢራንን የአካባቢው ተፅእኖ ፈጣሪ ተደርጋ የምትታሰብበት ሁኔታ መፈጠር መቻሉ የቀጠናውን የፖለቲካ ምህዳር የቀየረ ይመስላል። በዚህ ላይ የኢራን የኒኩሌር አቅሟን የመገንባት ፍላጎት እየጨመረ መምጣት እስራኤል ኢራንን በስጋትነት ማየት እንድትጀምር ሆነች። የኢራን የኒኩሌር መርሀ ግብር በተመለከተ እና በአካባቢው እያደገ በመጣው ቀጠናዊ ተፅእኖዋ የተነሳ የእስራኤል ስጋት ሲጨምር በእስራኤል እና በኢራን መካከል ቀጥተኛ ወታደራዊ ግጭት ይበልጥ የማይቀር ይመስል ነበር። በርግጥ በ1998 ዓ.ም በእስራኤል እና በሂዝቦላህ መካከል የተደረገው ጦርነት፣ በስፋት ይታመን የነበረው የእስራኤል እና የኢራን ጦርነት የተልእኮ ጦርነት ተብሎ ነበር። ምናልባትም ሁለቱ ባላንጣዎች የወደፊት እና የቀጥታ ግጭት መንደርደሪያ ነው።
በቀጠናው የኃይል ሚዛኑን ለመቆጣጠር ራሳቸውን ከሌሎች ጦርነቶች እና ግጭቶች ጀርባ ሆነው በመሳተፍ በመካከላቸው ውጥረት እንዲጨምር ሆኗል። ኢራን በቀጠናው ፀረ እስራኤል እና አሜሪካ ትግል የሚያደርጉ ታጣቂ ቡድኖችን መደገፍ ጀመረች። ሒዝቦላህን በሊባኖስ፣ ሐማስን በፍልስጤም እንዲሁም ሀውቲን በየመን በገንዘብ፣ በጦር መሳሪያ እና በወታደራዊ ስልጠናዎች የምትደግፈው ኢራን ነበረች።
በ1980ዎቹ አጋማሽ ውስጥ ከአብዮቱ በኋላ ተቋርጦ የነበረው የኢራን የሲቪላዊያን የኒኩሌር መርሀ ግብር በሩሲያ ረዳትነት እንደገና መጀመር እስራኤልን ክፉኛ አሳሰባት። በመሆኑም የእስራኤል አይኖች ከኢራን ኒኩሌር ፕሮግራም ላይ አለመነቀል ጀመሩ። ኢራን አበክራ ለሰላማዊ አላማ የጀመረችው መሆኑን ብታሳውቅም፤ እስራኤል ግን ኢራንን በስጋትነት መጠርጠር ቀጠለች። እስራኤል የኢራንን የኒኩሌር መርሃ ግብር ለማውደም ስለምትፈልግ፤ የማያባራ የሴራ ጥቃቶች በ2010ዎቹ ውስጥ ተፈፅመዋል። የኒኩሌር ሳይንቲስቶቿም ኢላማ ተደርገው ነበር።
በ2001 ዓ.ም ላይ ቴህራን ‘ስቱክስኔት’ በሚባል የኮምፒውተር ቫይረስ በመታገዝ የኒኩሌር መርሃ ግብሯን ስላስተጓጎሉባት የእስራኤልን እና የአሜሪካን ምስጢራዊ የስለላ ተቋማትን ኮንናለች። ለሰላማዊ አላማዎች የኒኩሌር ሀይል የመገንባት መብት እንዳላቸው የሚገልፁት ኢራናውያን፣ በተጨማሪም በኢራናውያኑ መዲና ውስጥ በርካታ የፊዚክስ ሊቆች እና ልዩ መሀንዲሶቿን በመግደል እስራኤልን ይከሳሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስቴር ቢኒያሚን ኔትያኒያሁ በበርካታ አጋጣሚዎች የአለማቀፉ ማህበረሰብ ኃላፊነቱን ካልተወጣ እስራኤል ኢራንን ልታጠቃ እንደምትችል ተናግረዋል። ኢራን በበኩሏ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማእቀቦች ውስጥ ናት፤ አሁን ለማንኛውም የእስራኤል ጥቃት አፀፋ ለመስጠት እንደማታመነታ ምላሽ ሰጥታ ነበር።
በዚህ ውጥረት ውስጥ ከእለት ተለት ወደ ማይቀር የቀጥታ ጦርነት የሚወስደውን መንገድ የተከተሉት ኢራን እና እስራኤል የቀጠናው ጠንቅ መሆናቸውን ቀጥለዋል። በውክልና ጦርነት በእጅ አዙር ዓመታትን እርስ በርስ እየተፋለሙ የዘለቁት እስራኤል እና ኢራን ፊት ለፊት በቀጥታ ጦርነት የሚገናኙባቸው አጋጣሚዎች እየታዩ መጥተዋል።
የኢራን እና የእስራኤል ግጭት ወደ ለየለት ጦርነት ማምራቱ የታየው በተለይ ከመስከረም 27 ቀን 2016 ዓ.ም የሃማስ ጥቃት በኋላ ነበር። እስራኤል የበቀል እርምጃ ስትል ከጥቃቱ ማግስት ጀምሮ በሃማስ ላይ ይፋዊ ጦርነት ስትከፍት አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ከእስራኤል ጎን ሲቆም ኢራን ጠንካራ ተቃውሞ ያሳየች ሀገር ነበረች። ለእስራኤልም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን በመስጠት መግለጫዎችን ስታወጣ ነበር። ለሀማስ በስውር ኢራን ታደርግ ስለነበረው ድጋፍም እስራኤል ስታስጠነቅቅ ነበር።
የእስራኤል ሰራዊት እና የኢራን ኃይሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙት በሶሪያ ነበር። የኢራን አል ቁድስ ኃይል ከደቡብ ሶሪያ ወደ የጎላን ተራሮች ለተኮሰው ምላሽ ለመስጠት እስራኤል ጥቃት ፈፅማለች- በአየር ድብደባ።
እስራኤል በሶሪያ የኢራን ኤምባሲን በማጥቃቷ እና የኢራን የጦር ጄኔራል መገደላቸውን ይፋ ማድረጓ በሁለቱ ሀገራት መካከል ፍጥጫው እያየለ እንዲሄድ አድርጓል። ጄኔራሉ ኢራን በሊባኖስ ለሚገኘው ሒዝቦላ ሚሳየሎች እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ለማገዝ የምታደርገውን እንቅስቃሴ የሚያስኬዱ ዋና ሰው እንደነበሩም እስራኤል ይፋ አድርጋ ነበር። በዚህ ላይ የእስራኤል ረጅም እጆች በቴህራን ሚስጢራዊ ኦፕሬሽኖችን በመፈፀም ቁልፍ ሰዎቿን መግደል መቀጠሏ ውጥረቱን እያባባሰው በመጣበት፤ የኢራኑ ጠቅላይ ሚንስትር ከባለስልጣኖቻቸው ጋር በሄሊኮፍተር አደጋ የመሞታቸው አስደንጋጭ ዜና የማታ ማታ እጅን ወደ እስራኤል ሳያስጠቁም አልቀረም።
በ2016 ዓ.ም በመስከረም ወር ማብቂያ በኢራን ከሚደገፉት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሐማስ በጋዛ የፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ኢራንን እና በዙሪያዋ ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን አንድ ላይ ለማጥቃት የሚያስችላት አጋጣሚ የተፈጠረላት ይመስላል።
ባለፈው አንድ ዓመት የእስራኤል ዱላ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ኢራንን አቁስሏታል። ይህንን ተከትሎ ሚያዚያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም እና መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ኢራን በእስራኤል ላይ የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶችን ፈጽማለች።
ምንም እንኳን ኢራን በእስራኤል ላይ የሰነዘረቻቸው ድንበር ተሻጋሪ የድሮን እና የሚሳኤል ጥቃቶች ይህ ነው የሚባል ጉዳት ባያደርሱም፤ ኢራን ከርቀት በእስራኤል ላይ ጥቃት የመፈጸም ብቃት እንዳላት አሳይታለች።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል እንዳሳወቀው ግን አብዛኞቹ ሚሳዔሎች “በእስራኤል እና በዩናይትድ ስቴትስ በሚመራው የመከላከያ ጥምረት” አንዲከሽፉ ተደርገዋል። በመካከለኛው እና በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ “አነስተኛ ጥቃቶች” እንደነበሩ ግን አልሸሸገም።
ኢራን ቀደም ሲል 110 የባላስቲክ ሚሳኤሎችን እና 30 የመርከብ ሚሳኤሎችን ተኩሳ ነበር። የአሁኑ ጥቃት ላይ ግን ኢራን ከምንገዜውም በላይ በቁጥር በርከት ያሉ ሚሳኤሎችን ተኩሳለች:: ስለ ኢራን ጥቃት ዝግጅት አሜሪካ ምንም አይነት ዕውቅና አልነበራትም።
የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ጥቃቱ የኢራንን ጥቅም እና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የተደረገ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል:: የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በበኩላቸው ኢራን ከባድ ስህተት ፈፅማለች በማለት ጠቅሰው፤ ከበደ ያለ የአፀፋ ምላሽ እንደሚጠብቃት ዝተዋል:: ኢራንም እስራኤል አፀፋ እመልሳለሁ ካለች ከዚህ የላቀ ጥቃት ይከተላታል ብለው ማስጠንቀቃቸው ተሰምቶ ነበር።
የእስራኤል መከላከያ በኢራን ላይ ስለሚወሰደው አፀፋዊ እርምጃ በደንብ ከመከረ በኋላ አዘናግቶ በኢራን ላይ ከፍተኛ የሚሳየል ጥቃት በተመረጡ የኢራን ወታደራዊ ማእከላት ላይ መፈፀሟን እስራኤል ሰሞኑን አሳውቃለች። እስራኤል በዚህ ኢራን ላይ በፈፀመችው ጥቃት ከፍተኛ ውድመት እንዳደረሰች እና ከስድስት ቀን ጦርነቱ ወዲህ የበለጠ የሚባል ወታደራዊ ጀብዱ የተፈፀመበት ወታደራዊ ኦፕሬሽን መሆኑን በኩራት ይፋ አድርጋለች።
ኢራን በበኩሏ የእስራኤልን ጥቃት በቀላሉ የመከተችው እና ምንም ጉዳት ያላደረሰባት አስመስላ ለማለፍ ብትሞክርም በሳተላይት እየወጡ የነበሩ መረጃች ግን ቀላል የማይባል ጉዳት ማስተናገዷን አሳብቀውባታል። ማንም የሀገሪቱ የሚዲያ አውታሮች ኢራን ስለደረሰባት ጉዳት እንዳይዘግቡ የሚከለክል አስገዳጅ ሕግ ማውጣቷም ሲያነጋግር ቆይቷል።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር የጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ዓ.ም ዕትም