አዲሡ ምርታማነትን የማሳደግ ምክረ ሐሳብ

0
75

ከ80 በመቶ በላይ ለሚሆነው የሀገራችን ሕዝብ መተዳደሪያ፣ 40 ከመቶ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አስተዋፅኦ የሚያደርግ፣ ለውጪ ገበያ ከሚቀርቡት ምርቶች ውስጥ 80 ከመቶ ድርሻ የሚወስድ ነው – ግብርና፡፡ ከዚህ አኳያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ እና በዓለም ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በሚፈለገው መጠን እና ጥራት ማምረት ይገባል፡፡ ለዚህም በግብርና ዘርፉ ላይ የተደቀኑ ችግሮችን መለየት፣ ተከታትሎ መፍትሔ መስጠት እና አሠራርን ማዘመን እንደሚገባ እንደ ብራዚል በግብርና ያደጉ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል፡፡

የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር ደግሞ ለግብርናው ዘርፍ መዘመን የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአማራ ክልል በክልሉ ከሚመነጨው ኢኮኖሚ ውስጥ ከ45 በመቶ በላይ ድርሻ ለሚያበረክተው እና በዋና ዋና የምግብ ሰብሎችም የሀገሪቱን 33 በመቶ የምርት አስተዋጽአ ለሚያደርገው ግብርና ችግሮች ማብቂያ በየጊዜው የሚመክረው፡፡

 

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮም በግብርናው ዘርፍ ያንዣበቡ ችግሮችን በዘላቂነት ፈትቶ ምርታማነትን ለማረጋገጥ ከአርሶ አደር ጀምሮ ጥናት እና ምርምር የሚያካሂዱ ባለሙያዎች፣ ተቋማት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ አካላት የተቀናጁበት ከባለድርሻ አካላት ግንኙነት አማካሪ ካውንስል ጋር ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡ አማካሪ ካውንስሉ በዕለቱ ባካሄደው 11ኛ ጉባኤ ላይ የአርሶ አደር ተወካዮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ በመድረኩ  ምርት እና ምርታማነት እንዳያድግ በግብርናው ዘርፍ ካንዣበቡ በርካታ ችግሮች ውስጥ በዕለቱ አንገብጋቢ እና በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል ብሎ የተነጋገረባቸው የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቃምን በአዲስ ማሻሻል እና የምርጥ ዘር አቅርቦትን ካለፉት ዓመታት በተሸለ ተደራሽ ማድረግ  ናቸው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ አሰፋ ወርቁ ሕዝቡ በምግብ ራሱን እንዲችል በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ በተደጋጋሚ በድርቅ ይመታል፡፡ እንደ ቡድን መሪው ገለጻ እነዚህ ችግሮች ደግሞ በአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ ይህም በምርታማነት ላይ አሉታዊ ጫናን ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡

 

ብሔረሰብ አስተዳደሩ የአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም እንዲሻሻል ከማድረግ ጀምሮ የአካባቢውን ሁኔታ መሠረት ያደረጉ ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ማድረጉን ቡድን መሪው  ያስረዳሉ፡፡  በዓመት ከ45 ቀናት በላይ ዝናብ የማይጥልባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ቡድን መሪው፣ የሰቆጣ ዝናብ አጠር ምርምር ማዕከል ያስተዋወቀው የእንቁ ዳጉሳ ዝርያ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ እስከ 70 ቀናት ለምርት የሚደርሰው እንቁ ዳጉሳ  የተጀመረው በአምስት ሄክታር እና በ20 አርሶ አደሮች ቢሆንም አሁን ላይ ከሦስት ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ምርጫቸው አድርገው እያመረቱት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከአንድ ሺህ 560 ሄክታር በላይ መሬት ላይ እየተመረተ ካለው እንቁ ዳጉሳ በተጨማሪ የአካባቢውን ሥነምህዳር መሠረት ያደረጉ ሌሎች ዝርያዎችንም በምርምር በማውጣት ሕዝቡን ከጠባቂነት ማውጣት ላይ ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

 

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ቀኝአዝማች መስፍን እንደተናገሩት ምርታማነት እንዲያድግ የግብርና ሥራዎች በቴክኖሎጂ እና በምርምር መደገፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም ባለድርሻ አካላትን ለይቶ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ያምናሉ፡፡

“የግብርና ችግሮች ብዙ ናቸው” የሚሉት አቶ ቀኝአዝማች፤ ሁሉንም ችግሮች ግን በአንድ ጀምበር መፍታት እንደማይቻል ያምናሉ፡፡ አማካሪ ካውንስሉ በዓመት ሁለት ጊዜ ሲገናኝ አንገብጋቢ ችግር ናቸው ብሎ በለያቸው ከአንድ እስከ ሦስት በሚደርሱ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጉባኤም አማካሪ ካውንስሉ የተነጋገረው የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ምክረ ሐሳብን ማሻሻል፣ የምርጥ ዘር ማምረት  እና አቀርቦትን ማሻሻል እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

 

ጥራት ያለውን ዘር በመጠቀም የሰብል ምርትን ከ30 እስከ 50 በመቶ ማሳደግ እንደሚቻል የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡ የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትም በየጊዜው የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በየጊዜው ያስተዋውቃል፡፡ ነገር ግን ወደ ምርት የተሸጋገሩት በጣት የሚቆጠሩ እንደሆኑ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ቀኝአዝማች ያስገነዝባሉ፡፡ ማሳያ አድርገው ያነሱትም የምርምር ማዕከሉ 173 የሰብል ዝርያዎች እንዳሉት ቢያሳውቅም በተግባር በምርት ውስጥ የሚገኙት ከ20 የበለጡ አለመሆናቸውን ነው፡፡ በስንዴ 22 እና በጤፍ 21 ዝርያዎች እንዳሉ ቢገለጽም በእያንዳንዱ የዘር አይነት መሬት ላይ በተግባር የወረደው ግን ከሁለት ዝርያዎች አለመብለጡ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባ ማንቂያ አድርገው አንስተውታል፡፡

 

ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት እና ለአማራ ክልል ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከት ከተፈለገ  የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት ማጠናከር እንደሚገባ አቶ ቀኝአዝማች አሳስበዋል፡፡ “በአማራ ክልል በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች… አሉ፤ ነገር ግን እስካሁን ሁሉም በየራሱ ይባዝናል፡፡ አዋጪው መንገድ ተቀናጅቶ መሥራት ነው፡፡ ስንቀናጅ የምንፈታው ችግር ብዙ ነው” በማለትም አንዱ ለሌላው የቤት ሥራ ሰጥቶ ራሱን ከማግለል አስተሳሰብ እንዲወጣ  አሳስበዋል፡፡

በልሂቃኑ የሚነሱ ችግሮች የአርሶ አደሩም እንደሆኑ ለማወቅ፣ እኛ ችግር ናቸው ብለን ያላየናቸው ካሉ በቀጥታ አርሶ አደሩ እንዲያነሳቸው፣ ሀገር በቀል ዕውቀቱን አቀናጅቶ በመጠቀም በግብርና ዘርፉ ላይ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስወገድ በየአካባቢው የሚኖሩ የአርሶ አደር ተወካዮች በጉባኤው እንዲሳተፉ መደረጉንም አቶ ቀኝአዝማች አስረድተዋል፡፡

 

በጉባኤው ላይ ተሳታፊ ሆነው በመድረኩ የተገኙት የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አምሳሉ ጋሼ ቀድመው ለሚዘሩ ሰብሎች የሚውል የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ገዝተው የዘር ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዘንደሮዉ መኸር ወቅት ዋነኛው ፈተና የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መጨመር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የግብርና ምርቶች ገበያ ማጣት እና የዋጋ መቀነስ ደግሞ አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ በበቂ መጠን እንዳይጠቀም ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ይህ ምናልባት በቀጣይ የምርታማነት መቀነስን እንዳያስከትል ስጋታቸው መሆኑን አስጠንቅዋል፡፡

አርሶ አደሩ በዋናነት በስፋት የሚያመርቱት የበቆሎ ሰብል ነው፡፡ የበቆሎ ምርጥ ዘር እጥረት እንዳላጋጠማቸው ሲገልጹ የፍላጎት ክፍተት ግን መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ የአርሶ አደሩ ፍላጎት ሊሞ የተሰኘ የበቆሎ ምርጥ ዘር ቢሆንም በዚህ ዓመት ማግኘት አለመቻላቸው ግን ከዚህ በፊት ያገኙት የነበረውን የምርት መጠን ላያገኙ እንደሚችሉ ስጋት እንደፈጠረባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከአፈር ማዳበሪያ እና ከምርጥ ዘር አቅርቦት  እና በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚስተዋሉ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ውይይቶች ግን አርሶ አደሩ የሚያነሳቸውን ችግሮች በአግባቡ የሚፈቱ ሊሆኑ እንደሚገባም ያምናሉ፡፡ አማካሪ ካውንስሉ ከአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ማሻሻያ እና ከምርጥ ዘር ማፍለቅ ጋር   በተገናኘ በተነጋገራቸው ጉዳዮች ትልቅ ውጤት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል፡፡

 

በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተሩ ዓለማየሁ አሰፋ (ዶ/ር) ምርታማነትን በተግባር ማረጋገጥ ካስፈለገ ሁሉም ባለድርሻ አካል ኃላፊነቱን አውቆ በቅንጅት መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ምክረ ሐሳብ እንዲሻሻል ያስፈለገበትን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡ የቀደመው የአፈር ማዳበሪያ (ዳፕ) በፎስፈረስ፣ ዩሪያ ደግሞ በናይትሮጂን የበለጸጉ ናቸው፡፡ ይህ የአፈር ማዳበሪያ አፈሩ ያነሰውን ንጥረ ነገር የያዘ በመሆኑ ለዘመናት የምርታማነት ማሳደጊያ የአፈር ማዳበሪያ አማራጭ ሆኖ ሲሠራበት በቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ዚንክ፣ ቦሮን እና ፖታሺየም የገባባቸው ቅይጥ ማዳበሪያዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውን ዶ/ር ዓለማየሁ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ  እነዚህ ቅይጥ የአፈር ማዳበሪያ አይነቶች በምርምር ሲረጋገጡ ምርታማነትን በመጨመር ረገድ አስተዋጽኦ አልነበራቸውም፡፡ ስለሆነም የምርምር ኢንስቲትዩቱ ምክረ ሐሳብ በምርታማነት ላይ የጎላ ተጽእኖ በማይፈጥሩ ማዳበሪያዎች አርሶ አደሩ ዋጋ እንዳይከፍል እና ቀድሞ ወደ ነበረው የአፈር ማዳበሪያ እንዲመለስ ነው፡፡

 

ቅይጥ የአፈር ማዳበሪያዎች ከግብርና ሥራ እንዲወጡ ሲደረግ ጥቅማቸው ዜሮ ሆኖ ሳይሆን አፈሩ ተጨማሪ የለምነት ማስጠበቂያ ንጥረ ነገር ባለመፈለጉ እንደሆነ ዶ/ር ዓለማየሁ የተሻሻለበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቃልኪዳን ሽፈራው የክልሉን የግብርና ልማት በማሳደግ ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ አሠራሮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ “የክልሉን ምርታማነት ለማሳደግ በዓመት ምን ያህል ምርት እንጨምር? ምን አይነት አሠራሮችን እንከተል? የግብዓት አጠቃቀማችን እንዴት እና በምን አይነት አግባብ መሆን አለበት”? የሚሉትን ከባለድርሻ አካላት ጋር ሀሳብ የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የክልሉ የማምረት አቅም ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ መምጣቱም ተጠቁሟል፡፡ ለአብነት ባለፈው ዓመት 170 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡ ይህም ከዕቅዱ አንጻር ሲታይ የአንድ ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው፡፡ ለስኬቱም አዳዲስ አሠራሮች እና ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ መደረጋቸው እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

 

በምግብ ራስን ለመቻል የሚያስችሉ ሰብሎችን እና የዓለም የገበያ ፍላጎትን ሊመልሱ የሚችሉ ሰብሎችን ማምረት፣ ሰፋፊ የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን መከተል፣ የግብርና ምርትን የሚጠቀሙ አግሮ ኢንዱስትሪዎች በስፋት መገንባት…ለውጤቱ መገኘት ምክንያት ናቸው፡፡  በመሆኑም እነዚህን ኢንዱስትሪዎች በበቂ መጠን ሊመግቡ የሚችሉ ሰብሎችን መርጦ በስፋት ማምረት ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት አኩሪ አተር፣ ስንዴ፣ ሰሊጥ እና ሌሎች ሰብሎች ትኩረት ተሰጠቶ የተሠራባቸው ናቸው፡፡

አብዛኛዎቹ የቅባት እና የጥራጥሬ ምርቶች እንደ ክልል ለውጭ ገበያ /ኤክስፖርት/ የሚላኩ ናቸው፡፡ በመሆኑም የኤክስፖርት ፍላጎትን በከፍተኛ መጠን በማሟላት ሀገራዊ ገቢን ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡

 

የግብርና ሥራው በምግብ ራስን እንዲያስችል፣ አግሮ ኢንዱስትሪዎችን መመገብ እንዲችል እና የኤክስፖርት ምርትን በእጅጉ የማሻሻል ግብን ዕውን ለማድረግ ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ አሠራሮችን ትኩረት ሰጥቶ መተግበር ይገባል፡፡ የመጀመሪያው የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀምን ማሻሻል እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ይህም ከዓመት ዓመት ከፍተኛ መሻሻል እየተመዘገበበት ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ያደረጉት ባለፈው ዓመት ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መጠቀም መቻሉን ነው፡፡ ይህ መጠን በ2015 ዓ.ም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አሳይቷል፡፡ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም እየተሻሻለ መምጣቱ የክልሉ ምርታማነት በሄክታር አራት ኩንታል ጭማሪ እንዲመዘገብ አድርጓል፡፡

የአግሮ ኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት በበቂ መጠን ለመመለስ፣ ዘላቂ በሆነ መንገድ በምግብ ራስን ለመቻል እና በውጪ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በስፋት በማምረት የውጪ ምንዛሪ እጥረትን ለመፍታት የኩታገጠም የአመራረት ዘዴ መከተል እንደሚገባ አቶ ቃልኪዳን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በየዓመቱ እስከ ሦስት ሺህ ሄክታር መሬትን በክላስተር በመሸፈን ከግለሰብ እስከ ኢንዱስትሪዎች ያለውን ፍላጎት መመለስ እየተቻለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 

አቶ ቃልኪዳን የምርታማነት ሌላው መሠረት ተደርጎ እየተሠራበት ነው ያሉት የምርጥ ዘር አቅርቦት እና ስርጭትን ማሻሻል ነው፡፡ የአማራ ክልል በዋና ዋና ሰብሎች በዘር ራስን ለመቻል እና ለአግሮ ኢኮሎጂው ተስማሚ የሆኑ ዝርያዎችን ለማምረት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አቶ ቃልኪዳን አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም እያንዳንዱ ዞን ከራሱ ዋና ዋና ሰብሎች ምርጠ ዘር እንዲችል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በ2017/18 የምርት ዘመንም ከአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን 187 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ በከፍተኛ ትጋት እየተሠራ ነው፡፡ ተጠባቂ ምርቱ ከባለፈው ዓመት በ27 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ጭማሪ አለው፡፡ የዘንድሮውን ተጠባቂ ምርት ለማሳካት አማካይ ምርታማነትን በሄክታር 34 ኩንታል ማድረስ እንደሚገባ አቶ ቃልኪዳን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦ ከማሰራጨት ጀምሮ ሰፋፊ የኩታገጠም አስተራረስ ተግባራዊ ማድረግ፣ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ማሻሻል፣ የእርሻ ሜካናይዜሽንን መተግበር ላይ በትኩረት ይሠራል ተብሏል፡፡

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here