ዝምተኛ ነው፤ በልምምድ ቦታ ቀድሞ እንደሚገኝ አሰልጣኞች ይመሰክሩለታል፤ በባህሪው የተመሰገነ፣ ለሙያው የተገዛ እና ታታሪ አትሌት ነው። ቀነኒሳ በቀለን አርአያዬ ነው ይለዋል፣ በመካከለኛ ርቀት ጀምሮ አምስት እና ዐስር ሺህ ርቀቶችን አሸንፎ አሁን ላይ አዲሱ የማራቶን ንጉሥ ለመሆን መንገዱን ጀምሯል፤ በቅርቡም በመጀመሪያ የማራቶን ውድድሩ ድልን ተጎናጽፏል- አትሌት ሰለሞን ባረጋ።
ለዘመናት የተገነባው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት እንዳይደበዝዝ ተስፋ ከሚሰጡ ድንቅ አትሌቶች መካከል መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጎዳና ላይ ውድድር የአትሌቲክስ ቤተሰቡን እያስፈነደቁ ከሚገኙ ሯጮች ውስጥም አንዱ ነው። አትሌት ሰለሞን ባረጋ ትውልድ እና እድገቱ በደቡብ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ ነው። ሩጫን የጀመረውም የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለ እንደሆነ የኢትዮ ራነር ዶት ኦርግ መረጃ ያስነብባል።
አትሌት ሰለሞን በልጅነቱ ኳስ ይወድ እንደነበር የተናገረ ሲሆን ይህም ወደ ሩጫው ዓለም ለመግባት ምክንያት እንደሆነው ከኢትዮ ራነር ዶት ኦርግ ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ተናግሯል። እግር ኳስ ከመጫወት ባሻገር እግር ኳስ ይመለከታል፤ የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ እንደነበር የሚናገረው አትሌቱ ጨዋታውን ለማየት ከአንድ ስዓት በላይ በእግሬ እጓዝ ነበር ብሏል። ይህም ለሩጫ ህይወቱ እንዳገዘው ያስረዳል።
በትምህርት ቤት ውስጥ በተለያዩ የተማሪዎች ውድድሮች ላይ በመሳተፍ አሸናፊ በመሆኑ በአካባቢው የሚገኘውን የአትሌቲክስ ፕሮጀክት በ2004 ዓ.ም ተቀላቅሏል። በተወለደበት አካባቢ ያለውን የአትሌቲክስ ፕሮጀክት በይፋ ከተቀላቀለ በኋላ የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ስላሴን፣ የቀነኒሳ በቀለን እና የዘረሰናይ ታደሰን ታሪክ እና የሩጫ ክህሎት አጥንቷል። እንደ አፈ ታሪክ የሚነገረውን የእነዚህን አትሌቶች ብቃት እና ጀግንነትም ለታዳጊው ሯጭ ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮለታል። “ከሁሉም ብዙ ተምሬአለህ፤ ስልት፣ጽናት እና ፍጥነት ከእያንዳንዳቸው የሆነ ነገር አግኝቻለሁ” ሲል ተናግሯል።
በ2005 ዓ.ም የሀገር አቀፉ የፕሮጀክት ውድድር ሲካሄድ ሰለሞን ባረጋ የደቡብ ክልልን ወክሎ ተሳትፏል። በሦስት ሺህ ሜትር ርቀት ሁለተኛ ደረጃን ይዞም አጠናቋል። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ የደቡብ ፖሊስ አትሌቲክስ ክለብን ተቀላቅሏል።አትሌት ሰለሞን በአትሌቲክስ ክለቡ የፖሊስ ኢንስፔክተር ማዕረግ ያገኘ በእድሜ ትንሹ አትሌት እንደሆነ ጭምር ነው መረጃው የሚያስረዳው። ታታሪነቱ፣ ትጋቱ እና ቁርጠኝነቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ አብቅቶታል። የእርሱ ስኬት በቤተሰቡ እና በአካባቢው ባሉ ታዳጊዎች በጎ ተጽእኖ ፈጥሯል።
አትሌቱ ዓለም አቀፍ ውድድር ማድረግ የጀመረው በ2016 እ.አ.አ ነው። ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በፖላንድ በተደረገው የዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና በአምስት ሺህ ሜትር የመጀመሪያ ውድድሩን አድርጎ አሸንፏል። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ኬኒያ ላይ በተደረገው ከ20 እና 18 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማሳካት ችሏል። በ2018 እ.አ.አ በኋላ በለንደን በተከናወነው የአዋቂዎች የዓለም ሻምፒዮና መሳተፍ እንደጀመረ የዓለም አትሌቲክስ ያስነብባል። ነገር ግን ሜዳሊያ ውስጥ ሳይገባ ሀገሩ መመለሱንም መረጃው ያስገነዝባል።
በዚሁ ዓመት በቤልጂየም ብራስልስ በተከናወነው ከ20 ዓመት በታች የዲያመንድ ሊግ ውድድር አምስተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። 12 ደቂቃ 43 ሴኮንድ ሁለት ማይክሮ ሴኮንድ የገባበት ስዓት ነው። ይህም ከጆሹዋ ቼፕቴጌ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ኃይሌ ገብረ ስላሴ እና ዳንኤል ኮማን ቀጥሎ አምስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። በ2018ቱ የዲያመንድ ሊግ ውድድርም አምስት ሺህ ሜትር ርቀትን በበላይነት አጠናቋል። 12 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ከሁለት ማይክሮ ሴኮንድ የገባበት ሰዓት ሲሆን አራተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ እስካሁን ተመዝግቧል።
ሰለሞን ባረጋ በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ በዐስር ሺህ ሜትር ርቀት ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቡ አይዘነጋም። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ2008 እ.አ.አ በርቀቱ ለመጨረሻ ጊዜ ወርቅ ካሳካ በኋላ አትሌት ሰለሞን ከ12 ዓመታት በኋላ የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ አምጥቷል። በኦሎምፒክ በዐስር ሺህ ሜትር ርቀት ወርቅ ያመጣ አራተኛው አትሌት ነው። ከምሩጽ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረ ስላሴ እና ከቀነኒሳ በቀለ በኋላ በኦሎምፒክ ታሪክ በርቀቱ ወርቅ ያገኘ አትሌት ነው። አትሌቱ በ2024ቱ የፓሪስ ኢሎምፒክ ግን በርቀቱ ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ አይዘነጋም።
በ2022 በተደረገው የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በሦስት ሺህ ሜትር ሀገራችንን የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቡ አይዘነጋም። ሰለሞን ባረጋ በስፔን ሲቪያ በተደረገው የማራቶን ውድድር አሸንፏል። ሁለት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ከ14 ሴኮንድ የገባበት ሰዓት ነው።
በ2023ቱ የቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና በርቀቱ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ መጨረሱ ይታወሳል። ከረዥም ርቀት በተጨማሪ መካከለኛ ርቀት በመሮጥ ስኬታማ ሆኗል። በ2020 እ.አ.አ በኳታር ዱሃ እና በ2023 እ.አ.አ በአሜሪካን ዩጂን በተደረገው የሦስት ሺህ ሜትር ርቀት የራሱን ምርጥ ሰዓት ጭምር በማስመዝገብ ነው ያሸነፈው።
እ.አ.አ በ2018 በብራስልስ በተደረገው የዐስር ሺህ ሜትር ርቀት 26 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ ከ73 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት የራሱን ፈጣን ሰዓት በማሻሻል አሸንፏል። በዚሁ ዓመት በቫሌንሺያ በተደረገው የግማሽ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉ የሚታወስ ነው። አትሌቱ በግማሽ ማራቶን ውድድር ከምንጊዜም ምርጥ ስድስት የግማሽ ማራቶን ሯጭም አንዱ ነው።
ሲቪያ በተደረገው የ2025ቱ የማራቶን ውድድር ሁለት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ከ15 ሴኮንድ በመግባት የራሱን ሰዓት በማሻሻል አሸንፏል። የገባበት ሰዓት በማራቶን ውድድር ታሪክ ከምንዜም ምርጥ 12 አትሌቶች መካከል አንዱ አድርጎታል።
አትሌቱ አክሰስ ዘ አርካይቭ ለተባለ ድረገጽ በሰጠው ቃለ ምልልስ “የመጀመሪያውን የማራቶን ውድድር አሸንፌያለሁ፤ ከዚህ በኋላ ሰዓት ለማሻሻል እሮጣለሁ ሲል መደመጡን መረጃዎች አስነብበዋል። ይህም የልጁን የአዕምሮ ጥንካሬ እንደሚያሳይ መረጃው አመልክቷል።
የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ደረጃ የሰጠው የሲቪያ ማራቶንን አሸንፏል። ከውድድሩ በኋላ በራሞን ሳንቼዝ ፒጁዋን ስቴዲየም በ25ኛ ሳምንት የስፔን ላሊጋ ሲቪያ ከማዮርካ ያደረጉትን ጨዋታ በክብር አስጀምሯል። የሲቪያ እግር ኳስ ክለብ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽም “Two champions” Navas Selemon Barega” የሚል ጽሁፍ አስነብቧል። የአትሌቱ አቅም እና ጉልበት እንዳይባክንም ከቀድሞ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ጨምሮ ብዙዎቹ የተመጠኑ ውድድሮችን እንዲያደርግ ምክር ለግሰውታል። አትሌቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህም በሁሉም ውድድሮች ባለመካፈል ጉልበቱን በአግባቡ እየተጠቀመ ይገኛል።
ከ2016 እ.አ.አ ጀምሮ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት 16 ጊዜ ሀገራችንን ወክሎ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲሳተፍ በርካታ የግል ውድድሮችንም አድርጓል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን ጋር ሀገራችንን በመወከል በኦሎምፒክ፣ በዓለም ሻምፒዮና፣ በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና፣ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር፣ በአፍሪካ ሻምፒዮና እና በዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ውድድር ተከፍሏል። ከእነዚህ ውስጥም አምስት የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፏል፤ ሦስት የብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ አሳክቷል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም