እግር ኳስ እያየ እና እየተጫወተ ነው ያደገ፤ ከደቡብ ሱዳናውያን ቤተሰቦቹ አውስትራሊያ ውስጥ ነው የተወለደው፤ ገና ከወዲሁ ክብረወሰኖችን እየሰባበረ አስደናቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፤ በ200 ሜትር ርቀት የአህጉሩ ባለክብረውሰን ነው፤ ብዙዎችም ከዩዜን ቦልት ጋር ያነጻጽሩታል። የመጪው ዘመን የአጭር ርቀት ንጉሥ ነው እየተባለ ይሞካሻል። በ200 ሜትር ርቀት የአህጉሩ ባለክበረውሰን ሯጭ ነው፤ በራሱ የሚተማመን፣ ጫናን የሚቋቋም፣ ብልህ እና ፈጣን እግሮችን የታደለ ወጣት አትሌት ነው። ክርስቲያኖ ሮናልዶን አርያዬ ነው ይላል- የአጭር ርቀት ሯጩ ጋውት ጋውት።
ጋውት ታህሳስ 29 ቀን 2007 እ.አ.አ በሰሜን ምስራቅ የአውስትራሊያ ኪዊንስላንድ ግዛት በኢፕስዊች ከተማ ነው የተወለደው። ቤተሰቦቹ በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ሀገራቸውን ደቡብ ሱዳንን በመልቀቅ ወደ ግብጽ በኋላም ወደ አውስትራሊያ አቅንተዋል። በ2006 እ.አ.አ ወደ አውስትራሊያ ከማምራታቸው በፊት ወደ ካናዳም የመሄድ ዕድል እንደነበራቸው የቢቢሲ መረጃ ያትታል።
በደቡብ ሱዳን የሕግ ምሩቅ የሆነው አባቱ ቦና በአውስትራሊያ ሆስፒታል ውስጥ የምግብ ባለሙያ ነው። በትርፍ ጊዜውም የታክሲ አገልግሎት እንደሚሰጥ መረጃው ያስነብባል። እናቱ ሞኒካ ደግሞ የጽዳት ሠራተኛ መሆኗን መረጃዎች ይነግሩናል። ልጃቸው በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ ትኩረት ማድረጉ ስኬታማ እንዲሆን አድረጎታል ይላሉ። ባዩት አስደናቂ ብቃትም መገረማቸውንም አልሸሸጉም። ጋውትም “ከቤተሰቦቼ ጠንካራ የሥራ ባህል መልመዴ ወደ ስኬት እንደንደረደር በር ከፍቶልኛል” ይላል።
ጋወት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለ ሩጫ እና እግር ኳስ ስፖርትን ቢያዘወትርም ፕሮፌሽናል ሯጭ የመሆን ህልም ግን አልነበረውም። በዘጠኝ ዓመቱ የሩጫ ክህሎቱን የተመለከተችው የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኟ ዲያ ሺፕርድ ክህሎቱን ዐይታ ወደ ሩጫው ዓለም እንዳስገባችው የግል የታሪክ ማህደሩ ያሳያል።
የካርኒ በዓል በሚከበርበት ወቅት በመቶ ሜትር የሩጫ ውድድር በመሳተፍ ወደ ፉክክሩ ብቅ ያለው ጋውት በትምህርት ቤት በሚደረጉ የአጭር ርቀት ፉክክሮች በተለይ ደግሞ በ100፣ በ200 እና በ400 ሜትር ርቀቶች እርሱን የሚቀድመው አልነበረም። አስራ አራት ዓመት ሲሞላውም ሩጫን የሙሉ ጊዜ ሥራው አደረገው። የመም እና የሜዳ ተግባራት ስልጠናዎችንም መከታተል ጀመረ። በወቅቱ በኪዊስላንድ የታዳጊዎች ውድድር ላይም በመቶ ሜትር መሳተፍ መጀመሩን መረጃዎች አመልክተዋል።
የአውስትራሊያ ብሄራዊ የትምህርት ቤቶች ሻምፒዮና ውድድርም የታዳጊው ማርሽ ቀያሪ መድረክ እንደነበር ከቢቢሲ ስፖርት ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ገልጿል። በዚህ ውድድር በ200 ሜትር ርቀት አሸንፏል። በአስራ ስድስት ዓመቱ በ100 እና 200 ሜትር ርቀት በአውስትራሊያ ምድር አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል። ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በመቶ እና በሁለት መቶ ሜትር ርቀት ምርጥ ብቃቱን እያሳየ ሲሆን በአውስትራሊያ ታሪክ ለ56 ዓመታት የቆየ ክብረወሰንም ሰብሯል።
ፒተር ሮርማን የ200 ሜትር ርቀት ክብረወሰንን ለ56 ዓመታት ይዞት መቆየቱ አይዘነጋም:: ፒተር ሮርማን በ1968 እ.አ.አ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ 20 ሴኮንድ ከስድስት ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በ200 ሜትር ርቀት ክብረወሰኑን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ይዞት የቆየ ሲሆን አሁን ላይ ጋውት ርቀቱን በሁለት ማይክሮ ሴኮንድ በማሻሻል ባለክብረወሰን ሆኗል።
በፔሩ ሊማ በተደረገው በ2024 እ.አ.አ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዩናም በ100 ሜትር ርቀት ዐስር ሴኮንድ ከ48 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በበላይነት አጠናቋል። በዚሁ መድረክ በ200 ሜትር ርቀት ደግሞ የብር ሜዳሊያን ማሸነፉ ይታወሳል። በታዳጊዎች የዓለም ሻምፒዮና መድረክ ባስመዘገበው ውጤት እና ባሳየው ድንቅ ብቃት ምክንያት ከአዲዳስ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጋር የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ለመፈረም በቅቷል።
በዚህ ዓመት በሀገሩ አውስትራሊያ በኪዊንስላንድ የመም እና የሜዳ ተግባራት ሻምፒዮና ላይ በ200 ሜትር እና 400 ሜትር ርቀት አሸንፏል። ጋውት ከ18 ዓመት በታች ውድድር በ200 ሜትር ርቀት ከዩዜን ቦልት ቀጥሎ ሁለተኛው የፈጣን ሰዓት ባለቤት ጭምር ነው። በ60 ሜትር ስድስት ሴኮንድ ከ68 ማይክሮ ሴኮንድ፣ በ100 ሜትር ዐስር ሴኮንድ ከ17 ማይክሮ ሴኮንድ፣ በ200 ሜትር 20 ሴኮንድ እና ከሁለት ማይክሮ ሴኮንድ እና በ400 ሜትር 46 ሴኮንድ ከ20 ማይክሮ ሴኮንድ ያስመዘገባቸው ፈጣን ሰዓቶች ናቸው። እ.አ.አ በ2024 ዩዜን ቦልት በኢንስታግራም ገጹ “ጋውት ወጣትነቴን ያስታውሰኛል” በማለት የወጣቱን እምቅ ችሎታ መስክሯል።
ጋውት በአውሮፓ ምድር የመጀመሪያውን ውድድር ያደረገው ባሳለፍነው ሰኔ ወር ነው። በቼክ ሪፐፕሊክ በተደረገው በጎልደን ስፖይክ ኦስትራቭ ውድድር ሲሆን የ200 ሜትር ፉክክሩንም በበላይነት ማጠናቀቅ ችሏል።
ቦልት በ2006 እ.አ.አ በጎልደን ስፓይክ ውድድር የመጀመሪያውን የ200 ሜትር ውድድር 20 ሴኮንድ ከ28 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ነበር ያሸነፈው። ያኔ ጋውት ጋውት የስድስት ወር ህጻን እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። ታዲያ ከ17 ዓመታት በኋላ ጋውት የጎልደን ስፓይክ ውድድር ያደረገ ሲሆን በ20 ማይክሮ ሴኮንድ ቀድሞ መግባት ችሏል።
በዘንድሮው ከ23 ዓመት በታች የዲያመንድ ሊግ ውድድር በ200 ሜትር ርቀት ሞናኮ ላይ ማሸነፉ አይዘነጋም። አዲሱ የመጪው ዘመን የአጭር ርቀት ንጉሡ ጋውት ጋውት የተለያዩ ጋዜጦች እና መጽሔቶች የፊት ገጽ አድማቂ ሆኖ መሰንበቱም የሚታወስ ነው። በ16 ዓመቱ በ200ሜትር የታዳጊዎች ውድድር በሀገሩ ምድር ክብረወሰን የሰበረው ታዳጊው ከዚህ በፊት በእርሱ እድሜ ያንን ያደረገ ሯጭ ከዩዜን ቦልት በስተቀር የለም።
የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንቱ ሰባስቲያን ኮ እንዳሉት እንደዚህ ዓይነት ተሰጥኦን ልንከባከበው ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። ከአውስትራሊያ የምንጊዜም ሯጮች መካከል አንዱ የሆነው ማት ቨሪቪንግተንም ሀገሪቱ ካፈራቻቸው ስፖርተኞች ሁሉ ጋውት የላቀው አትሌት ይሆናል ሲል የታዳጊውን ተሰጥኦ ይመሰክራል። የ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ ቦትስዋና በታሪኳ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ያደረጋት ሌትሲል ቴቦጎ በበኩሉ ከዘ ጋርዲያን ጋር በነበረው ቃለ ምልልስ ጋውት ከምርጦች መካከል አንዱ ይሆናል ብሏል። “አሁን ባለው ከፍተኛ ተነሳሽነት ከቀጠለ ደግሞ በክብር መዝገብ የሚጻፍ ውጤት ያስመዘግባል ሲል ተሰጥኦውን አድንቋል።
አውስትራሊያ ከ32 ዓመታት በኋላ የ2032ትን ኦሎምፒክ ታዘጋጃለች። ታዲያ ያኔ ጋውት 24 ዓመት የሚሞላው ሲሆን ምርጥ አቋም ላይ የሚገኝበት ወቅት ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ሀገሩንም ከፍ ባለደረጃ ያስጠራል ተብሎ ይጠበቃል።
ህልሙም በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መደረክ መንገሥ እንደሆነ የሚናገረው ጋውት በቀጣይ መስከረም ወር በጃፓን ቶኪዮ ለሚደረገው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር ከወዲሁ እየተዘጋጀ ይገኛል። በሎስአንጀለስ በሚደረገው የ2028 እ.አ.አ ኦሎምፒክ 20 ዓመት እድሜ የሚሆነው ጋውት ከተጠባቂ አትሌቶች መካከል አንዱ ነው።
ከ14 ዓመት ጀምሮ እስከ 17 ዓመት እድሜ ያለውን የዩዜን ቦልት እና የጋውት ጋውትን የእድገት ደረጃ ያነጻጸርረ ኮሪርሜል ዶት ኮም የተባለው ድረገጽ ተቀራራቢ ብቃት ያላቸው መሆኑን ያስረዳል። ጋውት ገና 18 ዓመት እድሜ ስላልሞላው ከእርሱ በፊት ያሉትን የአምስት አትሌቶች ሰዓት የማሻሻል ከፍተኛ እድል አለው ተብሏል። ከ18 ዓመት በታች የምንጊዜም ፈጣን ሰዓት ባለቤት ሲሆን ዩዜን ቦልት ደግሞ ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል። ከ20 ዓመት በታች ደግሞ ጋውት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ስድስተኛው ፈጣን ሰዓት ያለው አትሌት ነው። ታዲያ የ17 ዓመቱ ወጣት በመጪው ሦስት ዓመታት ውስጥ በርቀቱ ሰዓቱን የማሻሻል ከፍተኛ እድል እንዳለው ብዙዎች እምነት አሳድረዋል።
በአትሌቲክስ ስፖርት አብዛኞቹ ሯጮች ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚደርሱት በ20ዎች የእድሜ አጋማሽ እና በኋላ ነው። ታዲያ ጋውት በአውስትራሊያ ምድር በሚደረገው የ2032 የኦሎምፒክ ውድድር ላይ 24 ዓመት ሲሞላው ምርጥ ብቃት ላይ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ሰዎች አርአያ የሚያደርጉት ሰው መሆን እንደሚፈልግም ታዳጊው የአትሌቲክስ ፈርጥ ተናግሯል። ታላላቅ አትሌቶች ብቻ ሳይሆን በየውድድሩ የሚያሸንፍ ሯጭ መሆን እንደሚፈልግም ጋውት ገልጿል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም