አዲስ ዓመት

0
10

ልጆችዬ እንደምን ሰነበታችሁ? ደህና ናችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች በሀገራችን የዘመን አቆጣጠር መሠረት 2017 ዓ.ም አልቆ ወደ 2018 ዓ.ም እየገባን ነው፡፡

ልጆችዬ! ታዲያ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር  ኢትዮጵያውያን ብቻ የሚቆጥሩበት ሲሆን  በፈረንጆች አዲስ ዓመት  በጁሊያን ካሌንደር  ይቆጥራሉ። በዚህም በአመቱ  የተወሰኑ ወሪት የተለያየ ማለትም 30፣ 29 ወይም 28 ቀናት ይኖራቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን በአንድ ዓመት ውስጥ አስራ-ሁለት ባለሠላሣ ቀናት እና አንድ ባለ አምስት ወይም ስድስት ቀናት ያሉበት ጳጉሜ ወር አሉን ማለት ነው።

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ዓመታት ሁሉ በአራት መደባት ይዞራሉ፤ እነሱም ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ  እና ዘመነ ዮሐንስ ይባላሉ።

ልጆች የበዓላት አከባበር በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የሚከበሩ በዓላት ብዙውን ጊዜ ከግሪጎሪያን ዘመን አቆጣጠር በ7 ዓመታት ይዘገያሉ::ልጆችዬ! ታዲያ በኢትጵዮያ አዲስ አመት ሲገባ ለየት ያለ አደይ አበባ የተሠኘ በኢትዮጵያ የሚገኝ የአበባ ተክል የሚታይበትም ጊዜ ነው።  ኢትዮጵያ ውስጥ አደይ አበባ የዝናብ ወቅት ማብቃቱን እና የፀደይ ወቅት መጀመሩን  እንዲሁም የዓመቱን መጨረሻ እና የአዲሱን መጀመሪያ ያመለክታል፡፡

ለኢትዮጵያ አዲስ አመት( እንቁጣጣሽ )ታዳጊ ልጃገረዶች  አበባየሁሽ የተሰኘውን የባህል አዲስ አመት ዘፈን በመዘመር ለአዲሱ አመት የዕድል እና የበረከት ምልክት እንዲሆን ለወላጆቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው አደይ አበባን ይሰጡበታል።  ልጆችዬ! ታዲያ አበባየሁሽ ምን ተብሎ እንደሚዘፈን ታውቃላችሁ ?

ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን

ጌቶች አሉ ብለን

ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን

እሜቴ አሉ ብለን

አበባየሁሽ (ለምለም)

ባልንጀሮቼ (ለምለም) ቁሙ በተራ (ለምለም)

እንጨት ሰብሬ (ለምለም) ቤት እስክሰራ (ለምለም)

እንኳን ቤትና (ለምለም) የለኝም አጥር (ለምለም)

እደጅ አድራለሁ (ለምለም) ኮከብ ስቆጥር (ለምለም)

ኮከብ ቆጥሬ (ለምለም) ስገባ ቤቴ (ለምለም)

ትቆጣኛለች (ለምለም) የንጀራ እናቴ (ለምለም)

የንጀራ እናቴ (ለምለም)

አደይ የብር ሙዳይ ኮለል በይ

እቴ አበባ ሽታ አበባዬ (አዬ እቴ አበባዬ)

እቴ አበባሽ ስትለኝ ከርማ (አዬ እቴ አበባዬ)

ጥላኝ ሄደች በሀምሌ ጨለማ (አዬ እቴ አበባዬ)

ልጆችዬ! ከዚህ ዘፈን በኋላ የተሰጣቸውን ስጦታ  ተቀብለው ሲያበቁ ደግሞ

ከብረው ይቆዩን ከብረው

ባመት ወንድ ልጅ ወልደው

ሃምሳ ጥገቶች አስረው

ከብረው ይቆዩን ከብረው

ብለው በመመረቅ  ይሄዳሉ ማለት ነው፡፡ አሁን  አሁን ደግሞ አበባው ባይኖርም ልጆች በተለያየ ከለር ስዕል እየሳላችሁ እንኳን አደረሳችሁ  ትላላችሁ አይደል?

ልጆችዬ  እናንተም እንኳን ለመጭው አዲስ አመት በሰላም አደረሳችሁ ከወዲሁ እንላለን መልካም ሳምንት፡፡

ተረት

ላለመሰበር መተባበር

በድሮ ጊዜ አንድ አራት ወንድ ልጆቹን ብቻውን እያሳደገ የሚኖር አባት ነበር። ይህ አባት ልጆቹን ለማሳደግ ደከመኝ ሳይል ይሠራል። በተቃራኒው ልጆቹ ግን ርስበርሳቸው ስለማይስማሙ በየቀኑ እየተጣሉ ከባድ ፈተና ሆነውበታል። በየጊዜው ተዋደው፣ተከባብረውና ተባብረው ህይወታቸውን እንዲመሩ ቢመክራቸውም ፈፅሞ ሊሠሙት አልቻሉም።

አዛውንቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ህመሙ በርትቶበት ሆስፒታል ለመግባት ተገደደ። ከቀን ወደቀን ህመሙ እየተባባሰበት በመሄዱ በህይወት የሚቆይበት ጊዜ አጭር መሆኑን ተገነዘበ::ይህን አባት የሚያስጨንቀው ግን መታመሙ ወይም መሞቱ ሳይሆን የልጆቹ ርስበርስ አለመዋደድና አብሮ ለመኖር መቸገር ነበር። በመሆኑም ህይወቱ ከማለፉ በፊት አንድ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ሊያስተምራቸው በመፈለጉ ልጆቹን ቀጠን ቀጠን ያሉ ቁርጥራጭ እንጨቶችን እንዲያመጡለት አዘዛቸው። ልጆቹም አመጡለት።

በመቀጠልም “ሽልማት የሚያስገኝ አንድ ጨዋታ ላጫውታችሁ ነው! ” አላቸው። ልጆቹም ተስማሙ።  “ሁላችሁም  ከነዚህ እንጨቶች አንድ አንድ አንሱ! ከዚያም እንጨቶቹን በራሳችሁ ሀይል ለሁለት ስበሯቸው” ብሎ አዘዛቸው። ልጆቹም የተባሉትን በፍጥነት አደረጉ። ነገርግን አሁንም “ እኔ ነኝ ቶሎ የሰበርኩት እኔ ነኝ ትክክል!” እየተባባሉ መጣላታቸውን ቀጠሉ።

አባታቸውም “ ተረጋጉ ልጆቼ! ጨዋታው ገና አላበቃም! ” በማለት አራቱን እንጨቶች በአንድ ላይ በገመድ ካሰራቸው በኃላ ሁሉም በየተራ እንዲሰብሩት አዘዛቸው። ነገርግን ያለ ሀይላቸውን ተጠቅመው ቢሞክሩም አንዳቸውም ሊሰብሩት አልቻሉም።

በመጨረሻም አባት እንዲህ አለ “ አያችሁ ልጆቼ! እነዚህን እንጨቶች ለየብቻ መስበር ቀላል ነው። ነገርግን በአንድ ላይ ሲታሰሩ አይደለም አንድ ሰው በአንድ ላይ ሁናችሁ እንኳ ለመስበር  አይቻላችሁም። ምክንያቱም የፈለገ ጥንካሬ ቢኖር አንድነትን መስበር ከባድ ስለሆነ ነው! እናንተም እርስበርስ ተዋዳችሁ በአንድነት መቆም ከቻላችሁ ማንም በቀላሉ ሊያሸንፋችሁ አይችልም! እየተጣላችሁ ለየብቻ ከቆማችሁ ግን በተናጠል ተሰብራችሁ ትወድቃላችሁ! ”በማለት የልጆቹን አስተሳሰብ በቅፅበት የቀየረ ትምህርት ካስተማራቸው በኃላ ህይወቱ አለፈ!

ልጆች በህይወት ውስጥ የሚገጥሙንን ጉዞዎች ሁሉ ብቻችንን መጓዝ ስለማይቻለን ከሌሎች ጋር አብረን በአንድነት መቆም በሚያስፈልግበት ጊዜ መተባበር ይጠቅማል እሺ።

ምንጭ- ቡክ ፎር ኦል::

ይሞክሩ

  1. የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተው የት ነው?
  2. የአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ መቼ ነው።

3 . የሰው አካል በየቀኑ ምን ያህል ትንፋሽ ይወስዳል?

መልስ

  1. በጣሊያን ቦሎኛ ውስጥ 1088 እ.አ.አ ነው፡፡
  2. 1918 እ.አ.አ
  3. 20,000

ነገር በምሳሌ

ተሰብሮ ቢጠገን – እንደ ቀድሞው አይኾን።

አንዴ የተቆረጠ ነገር ከበፊቱ እንደነበረው መሆን አይችልም

ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው።

በሃሳብ ብቻ ከሆነ ሥራ ቀላል ነው፡፡

ጸጸት እያደር ይመሠረት።

ክፉ ሥራ መሥራት እየቆየ ይቆጫል

 

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጳጉሜ 3 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here