አዲስ የተገኙት

0
60

በካረቢያን ቀጣና በሚገኙ ዙሜል እና ባንኮቺንቾሮ በተሰኙ የሜክሲኮ ደሴቶች ላይ ከዚህ ቀደም የማይታወቁ ሁለት የዓዞ ዝርያዎች መገኘታቸውን  ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ባለፈው ሳምንት አስነብቧል፡፡

የካናዳ ማክጊል ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ከሜክሲኮ ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር ባዮኮታ ባህረ ገብ መሬት ያገኟቸው አዲስ የዓዞ ዝርያዎች የጥበቃ ተግባራት ማጠናከር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ብዝሃ – ህይወት በፍጥነት እየጠፋ መሆኑን የጠቆሙት የስነ ህይወት ኘሮፌሰሩ ሃንስ ላርሰን ከዙሜል ባንኮቺንቾሮ በመሰሉ ዴሴቶች የሚደረግ ምርምር እና ፍለጋ የነበረውን እና ያለውን ለማወቅ እንደሚያስችል ነው ያስረዱት፡፡

አዲስ የተገኙት ዝርያዎች በመካከለኛው አሜሪካ፣ በሜክሲኮ እና ፓሰፊክ የባህር ዳርቻ ካሉት ጋር አስደናቂ የዘረመል ልዩነት ተስተውሎባቸዋል፡፡ በመሆኑም ከነበሩበት የተለዩ መሆናቸው ሁሉንም አስማምቷል፡፡

ግኙቱ በቀጣይ ለሚደረገው ጥበቃ እንደምታው የጐላ መሆኑን ያሰመሩበት ተመራማሪዎቹ አዲሶቹ ዝርያዎች በየራሳቸው የተገለሉ እና  የእንዳንዳቸው ቁጥር ከ አንድ ሺህ በታች መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

ሁለቱም አዲስ የተገኙት ዝርያዎች አጠቃላይ ብዛት የተረጋጋ ቢመስልም ውስን ቁጥራቸው እና የመኖሪያ ቀጣናቸው መጥበብ የመጥፋት ስጋት እንዲያንዣብብባቸው አስገድዳል ነው ያሉት – ተመራማሪዎቹ፡፡ ስጋቱን ለማምከንም የከተማ መስፋፋትን መገደብ ወይም ቁጥጥር ማድረግ የሚመለከታቸው አጋር አካላት የዘወትር ተግባር ሊሆን ይገባል ሲሉ ነው ያሳሰቡት ተመራማሪዎቹ፡፡

በዓዞዎቹ ዝርያ መካከል ያለው ልዩነት የራስ ቅሎቻቸው ርዝመት እና ቅርጻቸው ዋነኛው ተጠቃሽ መሆኑን እና ይህም ከነበሩበት ሁኔታ ጋር እንደሚዛመድ አብነት ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡

አዲስ የተገኙት ዓዞዎች አናታቸው ከሾጠጡቱ ወይም የራስ ቅላቸው መቅጠን እና ማጠር በገደላገደል በሚገኝ የሌሊት ወፍ መኖሪያ ዋሻ እየገቡ ከርሳቸውን ለመሙላት ባደረጉት ዝግመተ ለውጥ የተከሰተ መሆኑን በመግለፅ ነው ያደማደሙት ተመራማሪዎቹ፡፡

 

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here