የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ሲነሳ ባለፉት ዓመታት የሴቶችን ፕሪሚየር ሊግ የተቆጣጠሩ ስሞች አዕምሮአችን ላይ ይመላለሳሉ:: ሎዛ አበራን ስናነሳ አረጋሽ ካልሳ ትከተላለች፤ ሴናፍ ዋቁማን ስንጠራ መሳይ ተመስገን ትመጣለች፤ እሙሽ ዳንኤል እና ረድኤት አስረሳህኝም የሊጉ የደም ስሮች ሆነው ዘልቀዋል:: እነዚህ ዕንቁዎች የሊጉን የግብ ክብር እና የኮከብነት መንበር በብቸኝነት ተቆጣጥረውት ኖረዋል:: ከ2014 ዓ.ም ወዲህ ግን የታሪኩ አቅጣጫ ሲቀየር አዳዲስ የጥበብ ፈርጦች ብቅ ሲሉ እየተመለከትን ነው:: በዚህ እትማችን የምናስታውሳችሁ የእግር ኳስ ተጫዋች እነዚህን የቀድሞ ኮከቦች ፈለግ ተከትላ ነገር ግን በራሷ መንገድ አዲስ ታሪክ እየጻፈች ስላለችው የዘንድሮው ዓመት ግብ አዳኝ ነው::
ስሟ ዳግማዊት ሰለሞን ነው:: በትውልድ አካባቢዋ ቋንቋ (ወላይትኛ) “ጎልያ ማረናራ” ሲሉ ይጠሯታል:: ትርጓሜውም አይምሬዋ ግብ አዳኝ ማለት ነው:: ዳግማዊት ከአካባቢዋ ፕሮጀክት ተነስታ በብሄራዊ ቡድን እስከ መካተት የደረሰች የሜዳ ላይ ጀግና ተጫዋች ናት:: ከመዲናችን አዲስ አበባ 326 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ በምትገኘው ወላይታ ሶዶ ከተማ የተወለደችው ዳግማዊት የእግር ኳስ ጅማሮዋን ያደረገችው በ2006 ዓ.ም ነበር:: በወቅቱ በወላይታ ሶዶ ፕሮጀክት ታቅፋ ስትጫወት ገና በጠዋቱ የወደፊቷን ብሩህ ተስፋ የሚጠቁሙ ምልክቶችን ታሳይ ነበር::
እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ የዳግማዊት ወላጆችም ልጃቸው ትምህርቷ ላይ እንድታተኩር እንጂ በእግር ኳስ ጨዋታ ጊዜዋን እንድታጠፋ አይፈልጉም ነበር:: “መጫወት እፈልጋለሁ” የሚለው የዳግማዊት ጥያቄ በቤተሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት አማላጅ እስከመላክ የሚያደርስ ፈተና ነበረበት:: እኩዮቿ ሴቶች በሌሉበት በወንዶች መሀል እየገባች የምትጫወተው ዳግማዊት ከውስጥ የሚገፋፋትን ስሜት ለማስተናገድ የግድ ወደ ሰፈር ሜዳዎች መሮጥ ነበረባት::
የዳግማዊትን ተሰጥኦ ቀድመው የተረዱ፣ አቅሟን ያመኑ እና ለቤተሰቦቿም ጭምር ሀላፊነት ወስደው እዚህ እንድትደርስ መሰረት ከሆኑት መካከል አሰልጣኝ ሽመልስ ሽታ አንዱ ናቸው:: በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ የሚሳተፈውን የወላይታ ዲቻ ሴቶች ክለብ በዋና አሰልጣኝነት እየመሩ የሚገኙት እኚህ ሰው ለዳግማዊት የፕሮጀክት ቆይታ ስኬት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ::
ግብ አነፍናፊዋ ዳግማዊት ሰለሞን የወላይታ ሶዶውን የፕሮጀክት ጊዜዋን አጠናቃ የሕልሟን ርቀት ለማስፋት ወደ አዲስ አበባ የመጣችው በ2011 ዓ.ም እንደነበር ታስታውሳለች:: መዳረሻዋ ደግሞ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ቀዳሚው እና አንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆነ:: ዳግማዊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታዋን ስታስታውስ “በክለብ ደረጃ እንዴት እና ምን መሆን እንዳለብኝ የተረዳሁበት ትምህርት ቤቴ ነው” ትላለች:: ይሁን እንጂ ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረም:: ክለቡ ለተጫዋቾች ማረፊያ የሚሆን መኖሪያ (ካምፕ) ስላልነበረው ዳግማዊት እና ጓደኞቿ በግል ቤት ተከራይተው ህይወት እየኖሩ ልምምዳቸውን ለመስራት ይገደዱ ነበር::
በ2011 ዓ.ም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ብታሳይም ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየት ተስኖት ወደ ከፍተኛ ሊግ ወረደ:: ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ሊጉ ዝቅ ብላ በመጫወት ለክለቡ ያላትን ታማኝነት በተግባር አሳይታለች:: በከፍተኛ ሊጉ መጫወቷ እንደ ውድቀት ሳይሆን እራሷን ይበልጥ የምታበቃበት እድል አድርጋ ተጠቀመችበት::
ዳግማዊት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያሳየችው ጽናትና ብቃት የሌሎች ክለቦችን ትኩረት መሳቡ አልቀረም:: የፊት መስመሯ ኮከብ አምና መዳረሻዋን ሲዳማ ቡና አደረገች:: በሲዳማ ቡና ቤት ዳግማዊት አዲስ ቅጽል ስም አገኘች – “በረሮ”:: ይህ ስም የተሰጣት በሜዳ ላይ ያላትን አስደናቂ ፍጥነት፣ ከኳስ ጋር ያላትን ምቾት እና ግብ አካባቢ ያላትን ድፍረት ለመግለጽ ነው:: ዳግማዊት ሰለሞን በ2017 ዓ.ም የውድድር ዘመን ለሲዳማ ቡና 11 ግቦችን ከመረብ በማገናኘት በሊጉ ውስጥ አስፈሪ አጥቂ መሆኗን አረጋገጠች::
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር ኢትዮ ኤሌክትሪክ አዲስ አሰልጣኝ ሾመ:: ከልደታ ክፍለ ከተማ የመጡት አሰልጣኝ ኤርሚያስ ዱባለ ወደ ክለቡ ሲመጡ አብረዋቸው እንዲሰሩ ከፈለጓቸው አራት ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዷ ዳግማዊት ሰለሞን ነበረች:: አምና በሲዳማ ቡና ቤት ያሳየችው ድንቅ ብቃት አሰልጣኙ ያለ ማመንታት ወደ ኤሌክትሪክ እንዲያመጧት ምክንያት ሆኗቸዋል::
ዳግማዊት ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ መምጣቷ ለእድገቷ ወሳኝ ምዕራፍ ነበር:: “ኤሌክትሪክ ትልልቅ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ያለፉበት፣ ያደጉበት እና ያሸነፉበት ቤት ነው፤ እንዲሁም ለሴቶች እግር ኳስ ያለው አመለካከት ምቹ ነው” ስትል ምርጫዋን ትገልጸዋለች:: በዘንድሮው የ2018 የውድድር ዓመት እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ዳግማዊት 18 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት እየመራች ትገኛለች:: የእሷ ግብ አዳኝነት ታክሎበት 1ኛው ዙር በተጠናቀቀበት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ36 ነጥቦች ሊጉን በበላይነት እንዲመራ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክታለች::
የዳግማዊት ጥንካሬ ግብ ማስቆጠሯ ብቻ እንዳልሆነ አሰልጣኝ ኤርሚያስ ይናገራል:: “የየተሰጣትን ልምምድ በአግባቡ መስራት፣ ሁሌም እራስን ለማሻሻል መጣር እና ከሁሉም በላይ የቡድን ተጫዋች መሆን መገለጫዎቿ ናቸው” ይላሉ አሰልጣኙ::
በዘመናዊ እግር ኳስ ውስጥ አጥቂዎች ብዙ ጊዜ በራስ ወዳድነት ይወቀሳሉ:: ነገር ግን ዳግማዊት “እኔ ብቻ ልታይ” የሚል የስግብግብነት ስሜት የሌለባት እና ለቡድን ውጤት ቅድሚያ የምትሰጥ ተጫዋች ናት:: ይህ ባህሪዋ ከፈጣን ሩጫዋ እና ከኳስ ቁጥጥሯ ጋር ተዳምሮ በዘንድሮው ሊግ ላይ እጅግ ተፈላጊ አጥቂ እንድትሆን አድርጓታል::
ዳግማዊት የአገር ውስጥ ስኬት የመጨረሻ ጣራዋ እንዲሆን አትፈልግም:: ህልሟ እነ ሎዛ አበራ፣ አረጋሽ ካልሳ እና አርያት ኦዶንግ የከፈቱትን በር ተከትሎ በአውሮፓ ሊጎች መጫወት ነው:: ይህንን ህልሟን ለማሳካት ደግሞ የሜዳ ላይ ጥረቷን ከመንፈሳዊ ጥንካሬዋ ጋር በማጣመር እየሰራች ትገኛለች:: አሰልጣኝ ኤርሚያስ ዱባለ በተጫዋቿ ላይ ሙሉ እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ:: “አሁን ባለችበት ሂደት ሳትኮፈስ፣ በስርዓት ሜዳ ላይ እየተጫወተች እና ልምምዷን እየሰራች ከቀጠለች የማይሳካበት ምንም ምክንያት የለም” ሲሉም ያበረታቷታል::
ከወላይታ ሶዶ አቧራማ ሜዳዎች ተነስታ በከፍተኛ ሊግ ፈተናዎች አልፋ ዛሬ በ2018ቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ መረቦችን እየወዘወዘች የምትገኘው ዳግማዊት ሰለሞን የህልሟን ግብ አድና ለኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ አዲስ ታሪክ እንድትጽፍ እኛም መልካም ምኞታችንን እንገልጻለን::
(ሐናማርያም መስፍን)
በኲር የጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


