አዳሪ ትምህርት ቤቶች – ከውጤት እስከ ሀገር ግንባታ

0
104

መግቢያ

አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከስምንተኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ ብቁ እና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ሁሉም ተሟልቶላቸው የሚማሩባቸው ተቋማት ናቸው:: ዩናይትድ ኪንግደም፣ ህንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ አሜሪካ፣ ናይጄሪያ እና ኬንያ (በአፍሪካ) ብዛት ያላቸውን አዳሪ ትምህርት ቤቶች በመገንባት ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል:: እነዚህ ሀገራት አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የሚገነቡት ለትምህርት ጥራት ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ጠንካራ አመራር እና ማኅበራዊ ትስስር እንዲኖራቸው ለማድረግም ጭምር ነው። ናይጄሪያ እና ኬንያ ደግሞ ማዕከላቱን ለማስፋት ሲነሱ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግን ታሳቢ ያደርጋሉ::

አማራ ክልል የሠጠው ትኩረት

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የታየው የውጤት መቀነስ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን አላሳሰበም:: ይህም አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት ሁነኛ ምልክት ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው::

በአማራ ክልል የሚገኙ አዳሪ ትምህርት ቤቶችም በመደበኛ ትምህርት ተቋማት ለሚማሩ ተማሪዎች የልህቀት ማዕከል መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው:: ትምህርት ቤቶቹ በተከታታይ ዓመታት ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎቸችን በማውጣት ሀገራዊ ውክልናን ከፍ ያደረጉም ሆነው ይነሳሉ::

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በእነዚህ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እየታየ ያለውን የትምህርት ጥራት ይበልጥ ለማስፋት፣ የተማሪዎችን እና የወላጆችን የትምህርት ተነሳሽነት ማሳደግን ታሳቢ በማድረግ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን እና የልዩ ተሰጥኦ ማበልጸጊያ ማዕከላትን ተደራሽነት ለማስፋት እየሠራ ይገኛል:: በአሁኑ ወቅትም የማዕከላቱን ቁጥር ወደ ሰባት ከፍ ለማድረግ በሦስት ከተሞች ግንባታዎች በመከናወን ላይ ናቸው:: ሰቆጣ፣ ደብረ ታቦር እና ፍኖተ ሰላም ደግሞ ግንባታ የተጀመረባቸው አካባቢዎች ናቸው::

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰቆጣ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው አዳሪ ትምህርት ቤት ደግሞ በተሻለ የግንባታ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ሰማኽኝ ድጋፍ ለአሚኮ አስታውቀዋል:: ግንባታው በ2016 ዓ.ም ነው የተጀመረው:: የተያዘለት በጀትም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ነው:: ግንባታውን ለማጠናቀቅ የተያዘው ጊዜም ሁለት ዓመት ነው::

የማዕከሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ ማደሪያ ክፍሎች፣ የአሥተዳደር ሕንፃ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊ ሁለገብ ስታዲየም፣ ክሊኒክ፣ የውበት መጠበቂያ ሳሎኖች፣ ሱፐር ማርኬቶች እና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ይኖሩታል:: አሁናዊ አፈጻጸሙም 92 በመቶ መድረሱን ሥራ ተቋራጩ አስታውቋል:: ማዕከሉ የ600 ብቁ እና ተጽእኖ ፈጣሪዎች መማሪያ ማዕከል ይሆናል::

አማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያረጋገጡትም ብቁ እና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ መሆኑን ነው:: በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ የሚገኙት ሦስቱ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በ2019 ዓ.ም ወደ መማር ማስተማር ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል:: የእነዚህ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ወደ መማር ማስተማር መግባትም በክልሉ የአዳሪ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር እና የሚቀበሏቸውን ተማሪዎች ተሳትፎ ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል:: ውጤታማ ተማሪዎችን ለማውጣት የሚደረገውን ጥረትም ትርጉም ባለው ደረጃ ያሻሽላሉ ነው ያሉት::

የብቁነት ማዕከልነታቸው ምስጢራቶች

እንደ ‘ግሎባል ስኮላርስ ዶት ኮም’ የመረጃ አውታር አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ ትምህርት ቤቶች በተለየ ሁኔታ ውጤታማ የሚሆኑባቸው በርካታ ሳይንሳዊ እና አስተዳደራዊ ምክንያቶች አሏቸው። የጥናት እና የጊዜ አጠቃቀም ቁጥጥር ቀዳሚው ምክንያት ነው:: በመደበኛ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ከትምህርት መልስ ያላቸው ጊዜ ለተለያዩ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮች (ቴሌቪዥን፣ ስልክ፣ የቤት ውስጥ ሥራ) የተጋለጠ ነው። በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ግን ጥብቅ የጊዜ ሰሌዳ መኖሩ ተማሪዎች ብቁ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል::

መምህራን ወይም ተቆጣጣሪዎች ባሉበት የሚደረግ የግዴታ የማታ የጥናት ሰዓት መኖሩ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩም አድርጓል::

አዳሪ ትምህርት ቤቶች ብዙውን ጊዜ ከከተማ ጫጫታና ከማኅበራዊ ረብሻዎች ራቅ ያሉ መሆናቸው ተማሪዎች ያለምንም መረበሽ ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ማድረጉም ሌላኛው መሠረት ተደርጎ ተመላክቷል::

ሌላኛው የሥኬት ምስጢር ደግሞ የማያቋርጥ የአካዳሚክ ድጋፍ መኖሩ ነው:: ተማሪዎች ከመምህራኖቻቸው ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ ስለሚኖሩ በትምህርት ክፍለ ጊዜ ያልገባቸውን ነገር በማንኛውም ሰዓት የመጠየቅ ዕድል አላቸው። ጎበዝ ተማሪዎች ደካማ ተማሪዎችን የሚያግዙበት እና በጋራ የሚያጠኑበት ዕድል ሰፊ መሆኑም ለውጠየት አብቅቷቸዋል::

አብዛኞቹ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የተሻሉ ቤተ -መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያዎች አሏቸው። እነዚህ ግብዓቶች ተማሪው በማንኛውም ሰዓት እንዲጠቀምባቸው ክፍት መደረጋቸው ውጤታማ እንዲሆኑ አብቅቷቸዋል::

አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከውጤት ባለፈ የተማሪውን ስብዕና በመገንባት ረገድ ከፍ ያለ ፋይዳ አላቸው:: ተማሪዎች ያለ ወላጅ እርዳታ ራሳቸውን ማስተዳደርን፣ ንጽህናቸውን መጠበቅን እና በጀት መመደብን ይለምዳሉ። ጥብቅ ደንቦች ስላሉ ተማሪዎች ሥርዓትን አክባሪ እና ኃላፊነት የሚወስዱ ሆነው ያድጋሉ።

በአጠቃላይ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪው የሚበላው፣ የሚጫወተው እና የሚያወራው ከትምህርት እና ከዕውቀት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ ብቻ በመሆኑ ሁሉም ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አግዟል::

ፋይዳቸው

አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከግል ስኬት ባለፈ በሀገር ግንባታ ላይ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ያስታወቀው ደግሞ ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት ነው:: በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚመደቡ ተማሪዎች አብዛኞቹ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው የገበሬ እና የከተማ ደሃ ቤተሰቦች የወጡ ናቸው። እነዚህ ተማሪዎች በነፃ ጥራት ያለው ትምህርት አግኝተው ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ እና ሥራ ሲይዙ ቤተሰባቸውን እና አካባቢያቸውን የመርዳት አቅም ይፈጥራሉ። ይህም ጎበዝ ተማሪ ከድህነት ይወጣል የሚለውን እውነታ ያረጋግጣል::

የልህቀት ባህል እንዲዳብርም ዕድል ይፈጥራሉ። እንደ ኢኤፍ አካዳሚ ዓለም አቀፍ የግል አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መረጃ ከሆነ ማዕከላቱ ባሉባቸው አካባቢዎች የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ይጨምራል፤ እንደ ሀገር የሚመዘገበውም ውጤት ይሻሻላል። ይህም “በትክክል ከተሠራ ውጤት ይመጣል” የሚል አስተሳሰብ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንዲሰርጽ ያደርጋል::

ኢኤፍ አካዳሚ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ለሀገራዊ አንድነት እና ማኅበራዊ ትስስር መጠናከር ያላቸውን አስተዋጽኦም አትቷል:: ይህም የሚሆነው ተማሪዎች ከተለያዩ አካባቢዎች መጥተው በአንድ ግቢ ውስጥ ለአራት ዓመታት አብረው ሲኖሩ የተለያዩ ባህሎችን እና አመለካከቶችን ማክበርን በመማራቸው ነው ይላል::

አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሴት ተማሪዎች አቅም እንዲጎለብት ተልቅ አቅም መሆናቸውንም ከአካዳሚው ገጽ የተገኘው ጽሑፍ ያስረዳል:: ሴት ተማሪዎች በአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆኑ ከቤት ሥራ እና ከባህላዊ ጫናዎች ነፃ መሆናቸውን ጽሁፉ አብነት አድርጓል::

ትምህርት ቤቶቹ የሚገነቡባቸው አካባቢዎች ከንግድ ማዕከልነት በተጨማሪ የትምህርት እና የዕውቀት ማዕከል እንዲሆኑ ዕድል የሚሰጥ መሆኑም ሌላኛው አበርክቶው ነው::

የአርአያነት ተፅዕኖም ከፍተኛ በመሆኑ የታዳጊዎች የትምህርት ፍላጎት እንዲጨምር ያግዛል:: የአዳሪ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች አልባሳት (ዩኒፎርም) ለብሰው በከተማዋ ሲታዩ ወይም ለዕረፍት ወደየቤታቸው ሲሄዱ ታናናሽ ተማሪዎች እነሱን እንደ ትልቅ ስኬት ያዩዋቸዋል። ከአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ስለ ትምህርቱ ዘዴና ዝግጅት መረጃ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።

ለውጤታማነት እና ዘላቂነት…

አንድ ሀገር የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ለማስፋት ሲነሳ ለቀጣይነታቸው እና ለውጤታማነታቸው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አጽንኦት የሰጠው ደግሞ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚከማቹበት ሪሰርች ጌት ነው:: የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ስትራቴጂካዊ አመራር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚል ርእስ በተሰራው ጥናታዊ ጽሁፍ ውስጥ እንደተመላከተው አዳሪ ትምህርት ቤቶች ውጤታማነታቸውን እንዲቀጥሉ ከፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት መጠበቅ ይገባል። ቅበላው በውጤት ላይ ብቻ የተመሰረተ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ እና ቀጣይነት ያለው በጀት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተመላክቷል:: የመንግሥት በጀት ቢቀንስ እንኳ ትምህርት ቤቶቹ በራሳቸው ገቢ የሚያመነጩበት መንገድ መፈለግ ደግሞ ቀድሞ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል::

 

ኮሮጆ

 

የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ልዩ መገለጫዎች

የተቀናጀ የመኖሪያና የመማሪያ አካባቢ

ራስን መቻል እና ነፃነት

ጠንካራ የማኅበራዊ ትስስር

የተጠናከረ የክትትል ሥርዓት

ሥርዓት እና ደንብ

ምንጭ፡- https://www.efacademy.org

 

(ስማቸው አጥናፍ)

በኲር የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here