አድዋ በዛሬ ሊገለጥ ይገባል!

0
205

ፀረ ጭቆና አስተሳሰብ፣ የነፃነት፣ የክብር፣ የሉዓላዊነት መንፈስ የወለደው አድዋ ተጨቋኞች
በጨቋኞች ላይ ድል ያደረጉበት የጦርነት አውድ ነው። ይህም ለመላው ጭቁን ሕዝቦች የነፃነት
አብነት ሆኖ በዓለም ታሪክ ውስጥ ይነሳል። ኢትዮጵያ በአድዋ ድል ማድረጓ የጨቋኞችን
ሕልም ያመከነ፣ ተጨቋኞችም ነፃነትን ፍለጋ እንዲነሱ ያፋፋመ የ19ኛው መቶ ክፍለዘመን
የዓለም ደማቁ ታሪክ ነው። ይህ የዓለምን አተያይ የቀየረ ድል ኢትዮጵያውያን የጋራ ትዝታ
እንዲኖራቸው በማድረጉ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እንደማጣበቂያ ሆኗል። የዲፕሎማሲ፣
የስልጣኔ፣ የነፃነት ምንጭም ሆኗል።
ከ128 ዓመታት በፊት በድል ለሌሎች ሀገራትም ነፃነትን ያበሰረችው ሀገር ለአፍሪካውያን
ብሎም ለጭቁን የዓለም ሕዝቦች ሁሉ አብነት መሆኗ ዛሬም በኩራት ይነሳል። ይሁን እንጂ
በአድዋ የተገኘው ነፃነት፣ ድልና ክብር ዛሬ አለ ወይ የሚል ጥያቄ ሲነሳ በልበ ሙሉነት ለመናገር
አያስደፍርም። ከአድዋ በኋላ በተበላሸ ፖለቲካ ምክንያት በኢትዮጵያ የዕርስ በዕርስ ጦርነት፣
ሙስና፣ የተበላሸ አስተዳደር፣ መከፋፈል እና መፈራረጅ ወደ ኋላ የጎተታት ሀገር ሆናለች።
የአድዋ ድል እና ነፃነት በሀገር ውስጥ ባለው ደካማ ፖለቲካ ምክንያት ሊዘልቅ አልቻለም።
ድህነት፣ ጭቆና እና ብዝበዛ ቀጥሏል። በመሆኑም አድዋ ለዛሬ ያልተሻገረ የዚያ ዘመን ድል እንጂ
ዛሬም ያስቀጠልነው የድል ውርስ ነው ብሎ ለመበየን አሁናዊ እውነታዎች አይፈቅዱም።
በአድዋ የታየው ሀገራዊ አንድነት፣ የአመራር ጥበብ እና ሥርዓት 128 ዓመታትን ተሻግሮ
በዛሬ አልተተረጎመም። በሴራ የተተበተበው በታኝ፣ ፈራጅ፣ የቂም በቀል ፖለቲካ እልባት ካላገኘ
አድዋ በዛሬ አውድ ላይ ሊተረጎም አይችልም።
በመሆኑም ʻአድዋ ዛሬ ናት፣ አድዋ ትናንትʼ እንዳለችው ተወዳጇ አቀንቃኝ እጅጋየሁ
ሽባባው፣ አድዋን በዛሬ ለመተርጎም ከሴራ ፖለቲካ ተሽሮና ከዚህ አዙሪት ወጥተን ሀገር
በጥበበኞች፣ በተስፈኞች እና በአርቆ አሳቢዎች ልትመራ ይገባል። ይህ ሲሆን ፍትሐዊነት፣ የሕግ
የበላይነት፣ ሰላም እና ዕድገት ይረጋገጣል። በአድዋ የታየው አካታች እና አሳታፊ የአመራር
ጥበብ በዛሬው አውድም ሊደገም ይገባዋል።
“አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ” መጓዝ ለዘላቂ ዕድገት እና ሰላም እንደማይሆን ከአድዋ
በላይ ምስክር የለም። ዳግማዊ ምኒልክ የጅማውን ወይም የጎጃሙን፣ የትግሬውን ወይም
የከፋውን፣ የወላይታውን ወይም የአፋሩን መሪ ወይም ንጉሥ አንዱንም ነጥለው በአድዋው
የክተት ጥሪ አልተዋቸውም።
በአድዋ ያልተሳተፈ የአካባቢ ንጉሥ አልነበረም። ይህ የአካታችነት አብነት ነው። ዳግማዊ
ምኒልክ ከጎጃሙ ንጉስ ከተክለሀይማኖት ጋር በእንባቦ ጦርነት ቢገጥሙም በእርቅ እና በይቅርታ
ችግሩ ተፈትቶ በአድዋ አንድ ላይ ተሰልፈዋል።
ከሌሎች ነገሥታት ጋርም በፈቃድ ወይም በኃይል ወደ አንድ ማዕከላዊ ዕዝ ንጉሡ
ሲያሰባስቡ በዚህ አኩርፎ በአድዋ አልዘምትም ያለ አካባቢያዊ ንጉስ አልነበረም። ሀገር ቂም
በቀልን፣ ሴራን፣ ጥላቻን ሳይሆን መተባበርን፣ አሳታፊነትን እና ጥበብ የተላበሰ አመራርን
እንደምትፈልግ የአድዋ ሁነቶች አስተማሪ ምሳሌዎች ናቸው።
ጥላቻ፣ ፍረጃ፣ ሴራ በተበተበው ፖለቲካ ውስጥ ማንም አሸናፊ ስለማይሆን አሁንም
በሀገራችን ምክንያታዊ፣ ሐሳባዊ፣ ፍትሐዊ፣ አካታች ሥርዓተ መንግሥትን ማፅናት ያስፈልጋል።
ይህ ሳይሆን ባለፈ አድዋ ታሪክ ብቻ እየተፅናኑ መኖር ራስን ከመደለል ያለፈ ትርጉም
አይኖረውም። አድዋ በዛሬ ሊገለጥ ይገባልና።
አድዋ በዛሬ ቢገለጥ የዕርስ በዕርስ ጦርነት አይኖርም፤ መለያየትም አይታሰብም ነበር።
አድዋነት በትብብር፣ በወገናዊ እና ሀገራዊ ፍቅር፣ በመሰባሰብ፣ በመረዳዳት የሚገለጥ ትናንት
የሆነ የሀገራችን አኩሪ ታሪክ ነው። አድዋ ከታሪክ ተሻግሮ በአሁናዊ ሁኔታ ይተረጎም ዘንድ
ከሴረኝነት፣ ከአስተሳሰብ ግርዶሽ እና ከጥላቻ ያመለጠ ሐሳብ እና ተግባር ያስፈልጋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here