አጃቢ ወይስ ተፎካካሪ?

0
102

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር ውድድር በድሬዳዋ እና አዳማ ከተማ ተደርጎ ተጠናቋል። የሁለተኛው ዙር ውድድር ደግሞ ከየካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተከናወነ ይገኛል::

ኢትዮጵያ መድን የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በበላይነት ማጠናቀቁ አይዘነጋም። ሀድያ ሆሳዕና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው መጨረሳቸው የሚታወስ ነው። ባሕር ዳር ከተማ አምስተኛ እና ፋሲል ከነማ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ነው የጨረሱት።

ባሕር ዳር ከነማ ከተመሰረተ 43 ዓመታትን ተሻግሯል። ይሁን እንጂ ለረጅም ዓመታት በታችኛው የሊግ እርከን ነበር የቆየው። ወደ ላይኛው የሊግ እርከን (ፕሪሚየር ሊጉ) ካደገ ሰባት ዓመታትን ብቻ ነው ያስቆጠረው። ቡድኑ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በደጋፊዎቹ ብዛት እና ድምቀት ከሚታወቁ ክለቦች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል።

የጣናው ሞገድ በባሕር ዳር ከተማ ስፖርት ክለብ ስር ነው የሚተዳደረው:: ክለቡ በጊዜ ሒደት እየተሻሻለ እና ለውጥ እያሳየ የሚገኝ ቡድንም ነው። በ2010 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) እየተመራ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ በማደግ የአማራ ክልል ሁለተኛው የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ መሆንም ችሏል። ባለፉት ሰባት ዓመታትም በፕሪሚየር ሊጉ እየተፎካከር ይገኛል።

ክለቡ በተለይ የ2015 ዓ.ም እስከመጨረሻው ድረስ ከአንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በመፎካከር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ውጤቱም በአፍሪካ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሳተፍ አስችሎታል።

የጣናው ሞገድ አዲሱን የያዝነውን የውድድር ዓመት ሲጀምር ሰባት ተጫዋቾችን በማዘዋወር፣ የሦስት ተጫዋቾችን ውል በማደስ እና ከሁለተኛው ቡድን በቢጫ እና በአረንጓዴ ቴሴራ ስድስት ተጫዋቾችን አሳድጎ ነው። ሀብታሙ ታደሰን፣ ያሬድ ባየን፣ ፍጹም ጥላሁንን እና ከመሳሰሉት ተጫዋቾች ጋር ደግሞ ተለያይቶ ነው የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የጀመረው::

አሰልጣኝ ደግአረገ  ይግዛው ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ  ዘንድሮ ጥሩ ተፎካካሪ እንደሆኑ ቢናገሩም የመጀመሪያው ዙር ውጤት ግን ያንን አያሳይም:: ክለቡ ልክ እንደ አምናው ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር ውድድር ደካማ ውጤት አስመዝግቦ ነው የጨረስው:: ከመሪው መድን ኢትዮጵያም በዘጠኝ ነጥብ ርቆ መጨረሱ አይዘነጋም::

ክለቡ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በ26 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። ካደረጋቸው 17 ጨዋታዎች ሰባቱን ረትቷል። አምስቱን ሲሸነፍ በተመሳሳይ በአምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።  ባሕር ዳር ከነማ ጠንካራ የኋላ ክፍል ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ ነው። ክለቡ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ቡና 11 ግቦች ብቻ ነው የተቆጠሩበት። ይህም ከኢትዮጵያ መድን ቀጥሎ በመጀመሪያው ዙር ውድድር አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት ክለብ አድርጎታል። የፊት መስመሩ ግን 17 ግቦች ብቻ ነው ያስቆጠረው። ይህም ባለፈው ዓመት የነበረበት ግብ የማስቆጠር ችግር ዘንድሮም ተስተውሎበታል::

ባሕር ዳር ከነማ ባሳለፍነው ዓመት ደካማ የተባለውን የውድድር ጊዜ በማሳለፍ አራተኛ ደረጃን ይዞ ነው የጨረሰው። አምና የፊት መስመሩ ግቦችን ለማስቆጠር ይቸገር እንደነበረም አይዘነጋም። የኋላ ክፍሉ ግን በቀላሉ የማይረበሽ እና አነስተኛ ግቦች የተቆጠሩበት ሲሆን ከፕሪሚየር ሊጉ ከሀድያ ሆሳዕና ቀጥሎ  አነስተኛ ግቦች የተቆጠረበት ክለብ ነበር። ዘንደሮም ሜዳ ላይ እያሳየ ያለው አቋም ከባለፈው ዓመት ጋር ተመሳሳይ ነው::

የመጀመሪያው ዙር ውድድር በድሬድዋ የተከናወነ ሲሆን ከ13ኛ ሳምንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስቴዲየም እና የመለማመጃ ቦታ ምቹ እንዳልሆነ ተነግሯል። በተለይ የመጫወቻ ሜዳው ባሕር ዳር ከነማ ለሚጫወትበት የአጨዋወት ስልት ምቹ እንዳልሆነ አሰልጣኝ ደግአረገ ያስረዳል። ድሬዳዋ ስቴዲየም ላይ የነበራቸውን አቋም ለመድገም እየተቸገሩ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ በወጣው ፍትሐዊ የገንዘብ አጠቃቀም ስርዓት እና ደንብ መሰረት ክለቡ በርካታ ተጫወቾችን ባሳለፍነው የክረምቱ የዝውውር ወቅት ማጣቱ አይዘነጋም:: ይህም የመጀመሪያውን ዙር  ከፍተኛ ጫና  ውስጥ ገብተው እንዲጨርሱ አስገድዷቸዋል:: በርካታ ተጫዋቾችን አጥተው የውድድር ዓመቱን የጀመረው ባሕር ዳር ከነማ ቡድኑን የማዋሀድ እና የማዋቀር ሥራ በመስራት የመጀመሪያው ዙር ውድድር አልፏል።

ቡድኑ ጥሩ መንገድ እየተከተለ እና ጨዋታዎችን እያሸነፈ ባለበት ወቅት መረሀግብሮች መቆራረጣቸው የቡድኑን የአሸናፊነት መንፈስ ጎድቶታል። ያም ሆኖ ግን የመጀመሪያውን ዙር የጨረሰበት መንገድ አስከፊ እንዳልነበር አሰልጣኙ ተናግሯል።

ከወትሮው በተለየ ዘንድሮ የክለቦች ቁጥር መጨመራቸው ሁለት የእረፍት ቀናት በቻ እንዲኖር አድርጎታል:: ታዲያ ያለ በቂ እረፍት ጨዋታዎች መደረጋቸው፣ የድሬዳዋ እና የአዳማ መጫዎቻ እንዲሁም መለማመጃ ቦታዎች ምቹ አለመሆን የቡድኑን ተነሳሽነት እንዳወረደውም አሰልጣኙ ያሰረዳል::

በቀጣይ የሚደረጉ ጨዋታዎች የቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ሽፋን የማያገኙ በመሆናቸው ኃይል እና ጥፋት የበዛባቸው ጨዋታዎች ሊበዙ እንደሚችሉ የተናገሩት አሰልጣኙ ለዚህም የስነ ልቦና እና የአካል ብቃት ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ ተጫዋቾች ላይ ጥሩ መነሳሳት በመኖሩ ሁሉንም ጨዋታዎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል። ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ  ውጤታማ ለመሆን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍም የኢትዮጵያ ዋንጫ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል። ለዋንጫ ከሚደረገው ትንቅንቅ ባሻገር ላለመውረድ የሚደረገው ፉክክር ከፍተኛ እንደሚሆን ከወዲሁ ይጠበቃል።

የሁለተኛው ዙር ውድድር ጫናው እንደሚበረታ የገለጹት አሰልጣኙ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ የተሻለ ውጤት ይዘው ለመጨረስ እያንዳንዱን ጨዋታ ጥንቃቂ በተሞላበት መንገድ እንጫወታለን ብለዋል።  ባሕር ዳር ከነማ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ደረስ በሁለተኛ ዙር በ20ኛ ሳምንት አንጋፋውን ቅዱሰ ጊዮርጊስ ክለብ አራት ለአንድ ማሸነፉ የሚታወስ ነው::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የመጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም  ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here